የሱዳኗ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር በግድቡ ዙሪያ የአፍሪካ መሪዎችን እያነጋገሩ ነው

የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር መሪያም አልሳዲቅ አልመሐዲ (ዶ/ር) እና የኬንያ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ምስል

የፎቶው ባለመብት, @StateHouseKenya

የምስሉ መግለጫ, የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር መሪያም አልሳዲቅ አልመሐዲ (ዶ/ር) እና የኬንያ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ

የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር መሪያም አልሳዲቅ አልመሐዲ (ዶ/ር) በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የአፍሪካ አገራት መሪዎችን እያነጋገሩ ይገኛሉ።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሯ የጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃመዶክ መልዕክትን ይዘው የኬንያ እና የሩዋንዳ ፕሬዝደንቶችን አግኝተው አነጋግረዋል።

መሪያም በቅድሚያ ጉዟቸውን ያደረጉት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ወደሆነችው ኬንያ ነው።

በኬንያ ቆይታቸውም ከፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ከኬንያ የውጪ ጉዳይ ሚንሰትር ራይቼል ኦማሞ እና በናይሮቢ ከሚኖሩ የሱዳን ኮሚኒቲ አባላት ጋር መወያየታቸውን የውጪ ጉዳይ ሚንስትሯ ገልጸዋል።

ከፕሬዝደንት ኡሁሩ ጋር በነበራቸው ውይይት ከግድቡ ጋር በተያያዘ ሶስቱንም አገራት የሚያስማም ስምምነት መደረስ አለበት የሚል አቋም ሱዳን እንዳላት አንጸባርቂያለሁ ብለዋል የውጪ ጉዳይ ሚንስትሯ በትዊተር ገጻቸው ላይ።

የኡሁሩ ኬንያታ ቤተ-መንግሥት፤ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ከሱዳኗ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጋር መገናኘታቸውን እና ከጠቅላይ ሚንስትር ሃምዶክ የተላከ መልዕክት መቀበላቸውን አስታውቋል።

የውጪ ጉዳይ ሚንሰትሯ ቀጣይ መዳረሻቸውን ያደረጉት ወደ ሩዋንዳ ነበር። በኪጋሊ ከፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ጋር ተገናኝተው የታለቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተ የተደረጉ ድርድሮችን እና ሁሉን አቃፊ የሆነ ስምምነት እንዲደረስ ሱዳን ስታደርግ የነበረችውን ጥረት ለፕሬዝደንቱ ማብራሪያ መስጠታቸውን ሚንስትሯ ገልጸዋል።

line

በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚንሰትር ሳሚ ሽኩሪ የግድቡ ድርድርን በተመለከተ የአገራቸውን አቋም ለማንጸባረቅ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጉዞ አድርገው ነበር።

ሳሚ ሽኩሪ ከሳምንታት በፊት በነበራቸው ጉዞ ወደ ወደ ኬንያ፣ ኮሞሮስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴኔጋል፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ እና ቱኒዚያ ተጉዘው ነበር።

ሶስቱ አገራት ለዓመታት በሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ጋር በተያያዘ ሲያደርጉት የነበረው ድርድር ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳያመጣ እስካሁን ቆይቷል።

ኢትዮጵያ የሶስትዮሽ ድርድሩን በአፍሪካ ሕብረት በአደራዳሪነት እንዲቀጥል ፍላጎት አላት። በቀጣይ የክረምቱ ወራት ሁለተኛው የግድቡ ውሃ ሙሌት እንደምታካሂድ ይፋ ያደረገችው ኢትዮጵያ፤ በአፍሪካ ሕብረት የሚመራውን አደራዳሪ ቡድን ወደ ጎን ማድረግ፤ በሦስቱ አገራት መካከል አለመተማመንን ይፈጥራል ትላለች።

ግብጽ እና ሱዳን በበኩላቸው ሶስቱ አገራት ከስምምነት ሳይደርሱ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መካሄድ የለበትም ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት በአደራዳሪነት እንዲመሩ ፍላጎት አላቸው።