ስዊዲኖች ለምን አርቲ ቡርቲ ወሬ ይጠላሉ?

አንድን ሕዝብ በተለየ የሚገልፁት ነገሮች አይጠፉም መቼም።
ኢትዮጵያዊ ሲባል ሰላምተኛ ሕዝብ ነው። የእግዜር ሰላምታ ከየቅያሱ ይዘንባል። ጠዋትም ማታም። ማኅበራዊ ሕይወት መገለጫው ነው። እንኳን በወሬ በገዛ እጅም ለብቻ መጉረስ አይቻልም። ከሆነ ቦታ ጉርሻ ይወረወራል።
ይህ ለተቀረው ዓለም አስደንጋጭ ነው።
ኢትዮጵያዊ ተግባቢ ነን ዝጋታም? ይህን ነገር "እንግዳ ተቀባይ ሆነን ዝጋታም ልንሆን አንችልም" በሚለው እንለፈው።
በየሽርፍራፊ ሴኮንዱ "ተጫወት! ተጫወቺ!" መባባሉም ለዝምታ የምንሰጠውን ቦታ እንደሌለ የሚጠቁም ይሆናል።
ስካንዲኒቪያን አካባቢ ዝጋታም ሕዝብ ይበዛዋል ይባላል። ዝጋታም ጠጠር ያለና አሉታዊ ቃል ሳይሆን አይቀርም። ምናልባት ዝም ማለት የሚወድ ሕዝብ እንበለው? ጋግርታም ሕዝብ ብንለውስ ትክክል ይሆን?
ከስካንዲኒቪያን አገሮች ደግሞ የስዊዲን ሕዝብ አለላችሁ። የባሰበት። ቢኮረኩሩት የማያወራ።
"ስዊዲኖች የባጥ የቆጡን የሚያወራ ሰው ይሸሻሉ? አርቲ ቡርቲ አይመቻቸውም። ነፍሳቸው ትጨነቃለች" ይላል የዚህ የቢቢሲ የጉዞ አምድ ጸሐፊ ዮወን ኒልሰን።
ይህ ጽሑፍም በአመዛኙ የእሱ ግላዊ ትዝብት ነው።
የንግግር ማማሟቂያ የሆኑ ቃላት፣ "እሺ፣ ሰላም ነው? አለን! አለን! ጠፋሽ? ጠፋህ?" የሚባል ነገር ያንገሸግሻቸዋል። የወሬ መንደርደርያ ጨዋታዎችን ደግሞ በፍጹም ነው የማይወዷቸው።
አንድ ሰው ማውራት ያለበት የሚያወራው ነገር እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ መረጃን ያቀፈ እንደሆነ እርግጠኛ ሲሆን ብቻ ነው ይላሉ።
አንድ አዋቂ የሆነ፣ ማገናዘብ የሚችል፣ ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን የደረሰ/የደረሰች ስዊዲናዊ/ስዊዲናዊት እንዴት ፋይዳ የሌለው ነገር፣ እንዴት ፍሬ ፍርስኪ ይዘላብዳል? ብለው ግርም ይላሉ።
የሚገረሙትም ለብቻቸው ነው። ከሰው ጋር ሆነው ቢገረሙ ምን አለ?
በተቀረው ዓለም ግን ሰዎች ጨዋታ ሲጀምሩ ዘለው ወደ ጉዳዩ አይገቡም። የወግ መዳረሻ የሚባል ነገር አለ። ፈረንጆቹ "ስሞልቶክ" የሚሉት።
ብዙም ረብ የሌላቸው የሚመስሉ ነገር ግን ተግባቦትን የሚያሳልጡ ቃላት አሉ። የወሬ ማሟሻዎች። የወግ ዳርዳርታዎች።
እነዚህን ነው የማይወዱት ስዊዲኖች።ስለ ሀብት ማውራት ነውር የሆነባት አገር
"እሺ! እንዴት ነው ታዲያ? ኑሮ እንዴት ይዞሻል? ዛሬ ትንሽ አየሩ ቀዝቀዝ አለ ልበል? እስኪ እሱን መስኮት ዝጉት…ማነህ ረዳት!" ብሎ መዘባረቅ፣ ለወሬ መንደርደር ነውር ነው።
እነሱ ግን እንዲህ የሚል ሰው ሲያጋጥማቸው ሀፍረት ይሰማቸዋል እንጂ አይጠሉትም፡፡ ነፍሳቸው ትጨነቃለች እንጂ ወዳጅነትን አይገፉም።
ስዊዲኖች ቀና ናቸው። ደግም ናቸው። ጥሩ ወዳጆች መሆን የሚችሉም ናቸው። የማይችሉት ረብ የለሽ ወሬን ነው።
ስለዚህ የሚያውቁትም ሰው ቢሆን አርቲ ቡርቲ እንዳያወራባቸው ፈርተው መንገድ እስከመቀየር ይደርሳሉ ይባላል።
ኮሪደር ላይ ሰው አግኝተው፣ ወይም ጎረቤት ሰላም ላለማለት ሲሉ ብቻ ከአፓርትመንታቸው ከመውጣታቸው በፊት በበራቸው ቀዳዳ ማን አለ ብለው አጮልቀው ጭምር ይመለከታሉ ይባላል። ክፋት አይደለም ነገሩ።
በቃ የጨዋታ መንደርደርያ ያሳፍራቸዋል። የእግዜር ሰላምታ ትርጉሙ አይገባቸውም።
የማኅበራዊ ተግባቦት ባለሙያዎች ግን የጨዋታ መንደርደሪያ ተራ ጉዳይ አይደለም ይላሉ።
ማኅበረሰብ እርስ በርሱ እንዲግባባና መተማመን እንዲፈጥር ወሳኝ ድልድይ እንደሆነ ነው የሚገለጹት።
ጨዋታ በዓይን ይገባል እንዲሉ የማይተዋወቁ ሰዎች ዘለው ጥልቀት ወዳለው የወግ ባሕር ውስጥ ሊሰጥሙ አይችሉም።
ሰዎች በወግ መንደርደሪያ ላይ ማሟሟቅ አለባቸው። በወግ ጎዳና ላይ ለወጉ ያህል ጎርደድ ጎርደድ ማለት አለባቸው። አለበለዚያ አቀበቱ ከየት ተገፍቶ።
ሰዎች እምብዛምም ትርጉም በሌላቸው የወግ ልውውጦች ውስጥ ይገማገማሉ፣ ይግባባሉ፣ በዚያው ቅጽበትም መተማመንን ይገነባሉ።
ስዊዲኖች ግን ይሄ ትንታኔ አይዋጥላቸውም። "የሰው ልጅ የተመጠነ ዘመን ነው በዚህ ምድር ላይ የሚኖረው። ማስመሰል የለበትም። አርቲ ቡርቲ ማውራት የለበትም። የባጥ የቆጡን መዘባረቅ ምን ይፈይዳል፤ ጊዜ ማቃጠል ነው ትርፉ፤ ሰው ዝም ይበል በቃ" ይላሉ ኮስተርተር ብለው።
ነገሩን ከጥቅምና ጉዳት አንጻር ብቻ ሳይሆን የሚመለከቱት ስለሚያሳፍራቸውም ጭምር ነው። "ሰው እንዴት ሆዱ እያወቀ ትርጉም የሌለው ነገር እየተጠያየቀ የልብ ካውያ ይሆናል" ብለው ግርም ነው የሚላቸው።
ፈረንጆች ስሞልቶክ የሚሉት የወግ መዳረሻ ጨዋታን እነሱ በስዊዲሽ ቋንቋ ካልፕራት (kallprat) ይሉታል። ቀዝቃዛ ወሬ እንደማለት ነው። ከልብ ያልሆነ ጨዋታ እንደማለት ነው። ካንጀት ጠብ የማይል ወግ እንደማለት ነው።
ሌሎች ስዊዲሾች ደግሞ የተቀረው ዓለም "ስሞልቶክ" የሚለውን ጨዋታ ማሟሟቂያ እነሱ ዶድፕራት (dödprat) ብለው ነው የሚጠሩት። የሞተ፣ የቸከ ወሬ እንደማለት ነው። ለዛው በፍጹም አይታያቸውም። ሰው ዝም ቢል ምናለ? የሚሉትም ለዚሁ ነው።
ከእንዲህ ዓይነት ረብ የለሽ፣ ለዛ ቢስ፣ እንቶ ፈንቶ ወሬ ለመራቅ ስዊዲኖች የማያውቁትን ሰው ዓይን ይሸሻሉ።
ባቡር ውስጥ ወንበር መጋራት አይወዱም። አንድ ሰው በጋቢና ፉርጎ ላይ ከተቀመጠ እነሱ ከሰውየው በጣም ርቆ ወደሚገኘው የባቡር ፉርጎ ሄደው ጥጋቸውን ይዘው ይቀመጣሉ።
አንድ በጨዋታና ሳቅ ያደገ አፍሪካዊ ባቡሩ ባዶ መሆኑን አይቶ ሰው ወዳለበት ፉርጎ ሄዶ ክፍት ወንበር እያለ ከአንድ ስዊዲናዊ ጋር ቁጭ ብሎ ጨዋታ ሊጀምር ቢል ከፍተኛ ድንጋጤ ሊፈጠር ይችላል።
ስዊዲኖች የግድ ወንበር መጋራት ካለባቸውም ፊታቸውን ያዞራሉ። እንግዳው ሰው ደረቅ፣ ለዛ የሌለው ጨዋታ እንዳይጀምርባቸው ስለሚፈሩ ጭንቅ በጭንቅ ይሆናሉ።
ይህ በየካፌው፣ በትራንስፖርት፣ በቢሮዎችና መኖሪያ አፓርትመንቶች ጭምር የሚያሳዩት ባህሪ ነው።
አንድ ስዊዲናዊት አብሯት ኮሌጅ የተማረ ሰው በአንድ አቅጣጫ ሲመጣ ብታይ በፍጥነት ወደ ገበያ ማዕከል ዘላ ልትገባ ትችላለች። ወይም ደግሞ በመስኮት ሽንቁር ልብስ እየመረጠች ለማስመሰል ፊቷን ታዞራለች።
ባቡር ጣቢያ ያለ አንድ ስዊዲናዊ እንግዳው ሰው ያናግረኛል ብሎ ካሰበ ያን ለማስወገድ ቶሎ ብሎ ስልኩን ይበረብራል። ወይም ደግሞ በሚያነበው ጋዜጣ ፊቱን ይሸፍናል።
ለየትኛውም ስዊድናዊ ንግግር አስፈላጊነቱ መረጃ ለመቀባበል ወይም ትርጉም ያለው ነገር ለመጫወት ነው። የባጥ የቆጡን ማውራት ምን ይፈይዳል።
ስዊዲኖች ገበያ ማዕከል ገብተው አስተናጋጁን የተለመደውን ሄይ "hey" የሚለውን ሰላምታ ለባለሱቁ ካቀረቡለት በኋላ ቶሎ ወደሚገዙት እቃ ነው የሚዞሩት። ተጨማሪ ወሬ መምዘዝ ነውር ሆኖ ይታያቸዋል። ነውር ባይሆን እንኳ የሆነ ትክክል ያልሆነ ነገር እንደተፈጠረ ያስባሉ።
"እስኪ ያቺን አሳየኝ? ሄዶብሻል…! ውይ ይሄ ጫማ ሲያምር? ዛሬ በረዶው ብሶበታል ልበል?" ብለው ጨዋታ ሊጀምሩ ቢሞክሩ በዚያ ወገን ያለው ሰው በድንጋጤ ሊፈጥ ይችላል።
የተግባቦትና ማኅበራዊ ግንኙነት አዋቂዎች ይህ ነገር ለምን ስዊዲኖች በተለየ ሊሳያፍራቸው ቻለ የሚለውን አጥንተዋል።
አንዳንዶቹ ምናልባት ስዊዲን ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላት አገር ሆና ነዋሪዎቿ ግን በቁጥር ትንሽ መሆናቸው የፈጠረው ሊሆን ይችላል ይላሉ።
በሰፊ መሬት ላይ ተነጣጥለውና ተራርቀው የሚኖሩ ሕዝቦች ስለሆኑ ሁሉም ሰው በዝምታ ውስጥ በራሱ ዓለም መኖርን ለምዶ ይሆናል።
ስዊዲኖች ለመቶ ዓመታት ዝም እንዳሉ፣ ተራርቀው እንደኖሩ ነው ወደዚህኛው ክፍለ ዘመን የተሸጋገሩት። ስለዚህ የማያውቁትን ሰው ሄዶ በጨዋታ መጥመድን አያውቁበትም። ትክክልም አይመስላቸውም።
ሌላው መላምት ስዊዲን እስከ 60ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ከውጭ የሚመጣ ስደተኛ አይታ አለማወቋ ነው።
የራሳቸውን ዝም የማለት ባሕል የሚቀይጥባቸው ሌላ ሕዝብ መጥቶባቸው ወይም ሄዶባቸው አያውቅም ነበር።
አሁን እንኳ በርካታ ሰዎች በተለይም ከአፍሪካ ወደ አገራቸው በስደት መጉረፋቸው ዝምታቸውን ሳይረብሽባቸው አልቀረም።
ያም ይሄም አፍሪካዊ በየመንደሩ በእግዜር ሰላምታ ሲያጣድፋቸው ስዊድኖች ምን ይውጣቸው?













