በትግራይ ክልል ስለሚያስፈልገው ሰብአዊ እርዳታ ምን ተባለ?

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልግ መግለጫ ካወጡ ተቋሞች መካከል ይጠቀሳሉ

የፎቶው ባለመብት, ASHRAF SHAZLY

በትግራይ ክልል ምግብ እና መድኃኒትን ጨምሮ የተለያዩ ሰብአዊ እርዳታዎች በአፋጣኝ እንደሚያስፈልጉ የአገር ውስጥና የውጪም የተራድኦ ድርጅቶች አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ኦክስፋም እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልግ መግለጫ ካወጡ ተቋሞች መካከል ይጠቀሳሉ።

በክልሉ ውስጥ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ እርዳታ እንደሚያሻቸውና በተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙት ዜጎች ላይ ወሲባዊ ጥቃት እየደረሰ መሆኑ ሪፖርት እንደተደረገም ተመልክቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ ከትግራይ ክልል እየደረሱኝ ያሉት ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እጅጉን አሳስቦኛል ብሏል።

ዓለም አቀፉ የግብረ ሰናይ ድርጅት ኦክስፋም በበኩሉ ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ በትግራይ ክልል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብሏል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልልና አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ደህንነትና ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንና ሰብአዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችልም አሳሰቧል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ በግጭት ወቅት የሚደርስ ወሲባዊ ጥቃትን የሚከታተሉ ትፕርሚላ ፓተን፤ "የቤተሰብ አባላቸውን ተገደው እንዲደፍሩ የተደረጉ ግለሰቦች ስለመኖራቸው የሚረብሹ ሪፖርቶች ደርሰውናል" ብለዋል።

ፕራሚላ፤ መሠረታዊ ቁሶችን ለማግኘት ሲባል ከወታደሮች ጋር ወሲብ ለመፈጸም የሚገደዱ ሴቶች ስለመኖራቸው፣ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ መድኃኒቶችን የሚፈልጉ ሴቶች ቁጥር ስለመጨመሩ እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያዎችም በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን የሚያትቱ ሪፖርቶች ስለመናራቸው ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ የመንግሥት ባለሥልጣናት ምላሽ እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ዓለም አቀፉ የግብረ ሰናይ ድርጅት ኦክስፋም በትግራይ ክልል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል ትናንት መግለጫ አውጥቷል።

በትግራይ ክልል ስለሚያስፈልገው ሰብአዊ እርዳታ ምን ተባለ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኦክስፋም በመግለጫው፤ በትግራይ የተከሰተው ግጭት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ከአንበጣ መንጋ ወረራ ጋር ተያይዞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ብሏል።

ኦክስፋም ከግጭቱም በፊት ቢሆን በደቡብ እና ምዕራብ ትግራይ እንዲሁም በሰሜን አማራ ክልል የሚኖሩ ሰዎች ድጋፍ ይሹ ነበር ብሏል።

የኦክስፋም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገዛኀኝ ከበደ፤ "በደቡብ ትግራይ የሚኖሩ ነዋሪዎች ግጭቱን በመሸሽ ወደ ሌሎች ስፍራዎች ሸሽተው ሲመለሱ ቀያቸው ወድሞ አልያም ተዘርፎ እንደጠበቃቸው ነግረውናል" ብለዋል።

ኦክስፋም ከግጭቱ በፊትም በትግራይ ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እርዳታ ጠባቂ ነበር ብሏል። በግጭቱ ወቅት በርካታ ሰዎች በቋሚነት ያገኙ የነበረውን የምግብ እርዳታ መቀበል ሳይችሉ ቀርተዋል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት አሐዝ ከሆነ፤ በትግራይ ከ4.5 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ አስቸኳይ ሰብአዊ አርዳታ ያስፈልጋቸዋል። የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ግን የተመድ አሐዝ የተጋነነ ነው ብሏል።

የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፤ "በትግራይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 4.5 ሚሊዮን ሳይሆን 2.5 ሚሊዮን ነው" ብለዋል።

ኮሚሽነሩ፤ 2.5 ሚሊዮን ሕዝብ ለመርዳት መንግሥት በቂ ዝግጅት አድርጓልም ብለዋል።

ለትግራይ ክልል 311 ሺህ 526 ኩንታል እንደቀረበና ይህም ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን መመገብ እንደሚችል አቶ ምትኩ ገልጸዋል።

"በአቅርቦት ረገድ ክፍተት የለብንም። በአሁን ሰዓት ከ20 በላይ የጭነት መኪናዎች አቅርቦቱን እያደረሱ ይገኛሉ" ሲሉም አክለዋል።

እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር ወደ 4.5 ሚሊዮን ገደማ እንደሆነ የሚጠቁም መረጃ መውጣቱን በተመለከተ፤ ይህንን አሐዝ "የፌደራል መንግሥት አላጸደቀውም" ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዶ/ር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው፤ የሰብአዊ እርዳታ እንዳልቀረበ ተደርጎ የሚነገረው የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት በሚፈልጉ አካላት ነው ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ዶ/ር ሙሉ፤ "ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር፤ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲሰጥ በመንግሥት በኩል ምንም ወደኋላ የተባለበት ጊዜ የለም" ብለዋል።

ጉዳዩን "ለፖለቲካ ፍጆታ" የሚያውሉ መገናኛ ብዙሀን እንዳሉ ጠቅሰውም "የተዛባ መረጃ እያሰራጩ ነው። ይህ ትክክል አይደለም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

መንግሥት የሚፈናቀል ሰው ሊኖር እንደሚችልና ሰብአዊ እርዳታ ሊያስፈልግ እንደሚችል ከመጀመሪያውም እንደተገነዘበ ጠቅሰው፤ "ከመጀመሪያው ጀምሮ ይህ ታሳቢ ተደርጎ ሥራ ተጀምሯል" በማለት ገልጸዋል።

አቶ ምትኩ አሁን ላይ 1.8 ሚሊዮን ዜጎች እርዳታ እየቀረበላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል። ይህ ቁጥር መንግሥት ሕግ የማስከበር እርምጃ ካለው በኋላ ሳይሆን ቀድሞውንም የነበረ መሆኑን አክለዋል።

"700 ሺህ ተጨማሪ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ብለን ግምት ወስደን በአሁን ሰዓት ለ2.5 ሚሊዮን ዜጎቻችን እርዳታ ለማቅረብ በቂ ዝግጅት አድርገናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ የችግሩ ተጎጂዎች በቂ ያልሆነ ወይም ምንም እርዳታ እንዳላገኙ በማስታወቅ፤ "በአካባቢዎቹና በሠላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛና አፋጣኝ ርብርብ የሚጠይቅ ነው" በማለት መግለጻቸው ይታወሳል።

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት በመሸሽ ወደ ሱዳን የሄዱ ዜጎች ከ55 ሺህ በላይ ሲሆኑ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ደግሞ 2 ሚሊዮን እንደሚጠጉ መረጃዎች ያሳያሉ።