በትግራይ ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥና የኮሮናቫይረስ ሚሊዮኖችን ለከፋ አደጋ ጥሏል- ኦክስፋም

የትግራይ ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, OXFAM

በትግራይ ክልል በቅርቡ የተከሰተው ወታደራዊ ግጭት፣የአየር ንብረት ካስከተለው ከአንበጣ ወረራና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተደራርቦ ሚሊዮኖችን ለከፋ አደጋ እንደጣላቸው ኦክስፋም አስታውቋል።

የክልሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ቢያስፈልጋቸውም ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለው ገደብ የቀጠለ መሆኑንም አሳሳቢነቱን በመጥቀስ ድርጅቱ በዛሬው ዕለት፣ ጥር 14/ 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በቅርቡ በምዕራባዊና ደቡባዊ ትግራይ እንዲሁም በክልሉ አጎራባች ባሉ የሰሜን አማራ አካባቢዎች ላይ ግምገማዎችን አካሂጃለሁ ያለው ድርጅቱ ወታደራዊው ግጭት ከመፈጠሩ፣ ጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም በፊት ቢሆንም ማህበረሰቡ በምግብ እጦት ሲሰቃዩ እንደነበረና በግጭቱ ሁኔታም ተባብሷል ብሏል።

መግለጫው የኦከስፋም የኢትዮጵያ ተወካይ ገዛኸኝ ከበደ ገብረሃናን ጠቅሶ እንዳሰፈረው

"ሶስቱ ገዳይ የምንላቸው፤ ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ነዋሪዎችን የከፋ አደጋ ላይ ጥሏቸዋል። ከግጭቱ በፊትም ቢሆን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በተነሳው የአንበጣ መንጋ በርካቶች ግማሽ የሚሆነው ምርታቸው ወድሞ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው የጤናና ምጣኔ ኃብታዊ ቀውስ ማህበረሰቡ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነበር" ብለዋል።

ግጭቱ የተነሳበት ወቅት የምርት መሰብሰቢያ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ በርካቶች ምርታቸውን እንዳይሰበስቡ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።

በክልሉ ውስጥ ያለው ሁኔታ አስከፊ እንደሆነና "በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ" አንድ የመንግሥት ባለስልጣን መናገራቸውን ከእርዳታ ሠራተኞች ጋር ከተደረገ ስብሰባ ላይ ሾልኮ የወጣ ማስታወሻ ላይ የሰፈረ ጽሁፍ ማመልከቱ የሚታወስ ነው።

በደቡብ ትግራይ የሚገኙ ቤተሰቦችም ለኦክስፋም እንደተናገሩት ግጭቱን ፈርተው አካባቢያቸው ወደሚገኙ መንደሮችና ጫካዎች ያገኟትን ውሃና ምግብ እየተቋደሱ ህይወታቸው ማትረፍ እንደቻሉ ነው።

ነገር ግን ወደቀያቸው በተመለሱበት ወቅት ቤታቸውና ንብረታቸው ወድሞ ወይም ተዘርፎ ነው ያገኙት።

በትግራይ የሚገኙ ተስፋይ ጌታቸው የሚባሉ አርሶ አደር "እህላችን፣ ምርታችን ተቃጥሏል የኔንም ጭምር ወድሟል። በአጠቃላይ ያጣሁት 1.5 ቶን (13.6 ኩንታል) ይገመታል። ይህ ሰባት ቤተሰቤን ለአስር ወራት ይመግብ ነበር" በማለት ለኦክስፋም ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ በግጭቱ ከደረሰባቸው የእህል ውድመት በተጨማሪ በርካታ አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም በአንበጣ መንጋው ከፍተኛ ምርታቸውን እንዳጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ጠንክሮ የተስተዋለው የአንበጣ መንጋ ብርቱ ጉዳት ካደረሰባቸው ክልሎችም አንዷ ናት ትግራይ። በተለይም በትግራይ ክልል ማዕከላዊና፣ ሰሜን ምዕራብ በሚገኙ አካቢዎች መንጋው የከፋ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል።

ከነበረው የአንበጣ መንጋና የሰብል ጉዳትም ጋር ተያይዞ ከ600 ሺህ የሚበልጡ የክልሉ ነዋሪዎች ለእርዳታ ጥገኛ ሆነው ነበር ይላል ኦክስፋም በመግለጫው።

እርዳታ ለመቀበል የተሰለፉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአሁኑ ወቅት ጦርነት ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልልና አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ደኅንነትና ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንና የሰብአዊ ቀውስን ሊያስከትል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መግለፁ የሚታወስ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት በቅርቡ ባወጣውና የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል እንደሚለው በትግራይ ክልል 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ነው።

ግጭቱ ያስከተለውን መሰረታዊ ነገሮች የዳሰሰው መግለጫው መሰረታዊ የሚባሉ የውሃ፣ጤና አገልግሎቶች፣ ትምህርት እንደተቋረጡም ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የመንግሥት ተቋማት ሰራተኞች ለሶስት ወራት ያህል ባለመከፈላቸውም ኑሯቸውን አዳጋች እንዳደረገው፣

የገንዘብ እጥረቱና ካለው የፀጥታ ችግር ጋርም ተደራረርቦ መሰረታዊ የሚባሉ ሸቀጦችን መሸመት አዳጋች እንዳደረገው የጠቆመው መግለጫው የምርቶች ዋጋ ንሯል ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታትም እንዲሁ በሪፖርቱ "ምግብ አለመኖር ወይም በገበያዎች ላይ ያለው አቅርቦት ውስን መሆን እየባሰ የሚሄድ የምግብ እጥረት አደጋን እየፈጠረ መሆኑን ሪፖርቶች እያመለከቱ ነው" ብሏል።

ነዋሪዎች ከጤና አገልግሎት እጥረት ጋር በተያያዘ እየሞቱ እንደሆነና በምግብና ውሃ እጥረትም በከፍተኛ ሁኔታም መጎዳታቸውን ሮይተርስ በአዲግራትና አክሱም እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ የገጠር አካባቢዎችን የጎበኘው ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን(MSF) ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

በጎበኙባቸውም አካባቢዎች የምግብ እጥረት፣ ውሃ፣ የጤና አገልግሎት ችግርና በፍራቻ የተዋጡ ሰዎችን ያገኙ ሲሆን "ሁሉም ምግብ ነው" የሚጠይቁት በማለት የቡድኑ ድንገተኛ ፕሮግራም ኃላፊ ማሪ ካርመን ቪኖሌስን ጠቅሶ ሮይተርስ አስነብቧል።

የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በዚህ ሳምንት ሰኞ እለት ባወጣው መግለጫ በሽረ ባሉ ክሊኒኮች በርካቶችን እየገደለ ያለው የምግብ እጥረት እንዳለ ያሳወቀ ሲሆን ሁኔታውንም የከፋ ነው ብሎታል።

ኦክስፋም በክልሉ ባለው አስቸኳይ የምግብ፣ መጠለያና ነዋሪዎች ኑሯቸውን እንዲያቋቁሙ ለማስቻል ካለው የሰብዓዊ ድርጅቶች ጥረት ጋር ተያይዞ በክልሉ ባለው ግጭትና የደህንነት ስጋት፤ የቢሮክራሲ ሁኔታና የኮሚዩኒኬሽን መቋረጥ ፈታኝ እንዳዳረገው ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ እርዳታ እያደረሰ እንደሆነ ይናገራል፤ ከሰሞኑ እንዲሁ በክልሉ ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችና የሕክም አቅርቦቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ለ1.8 ሚሊዮን ሰዎች መድረሱን የሠላም ሚኒስቴር ገልጿል።

ሚኒስቴሩ ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች እየቀረበ ያለውን እርዳታ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ ከተጠቀሱት ሰዎች በተጨማሪ በክልሉ 2.5 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አመልክቷል።

ሮይተርስ በተጨማሪ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሙሉ ነጋን (ዶ/ር) ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ባለስልጣኑ ተራራማ የሆኑ የክልሉ ገጠራማ ቦታዎች እርዳታ ለማድረስ የመጓጓዣ እጥረት የነበረ ቢሆንም፣ እርዳታ ማድረስ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

በትግራይ ክልል ግጭት የተቀሰቀሰው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በወቅቱ ክልሉን ያስተዳድር የነበረው ሕወሓት የሰሜን ዕዝን ማጥቃቱ ከተገለፀ በኋላ ነበር።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን መግለጹ ይታወሳል።

ነገር ግን አልፎ አልፎ ውጊያ እንደሚካሄድ የተነገረ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በክልሉ ያለውን የሰብአዊ ሁኔታ "የከፋ" ሲል ገልጾታል።

ኦክስፋም እንዲሁ ግጭቱ እንዳልቆመ በገለፀበት መግለጫው ሁለቱም ወገኖች ከግጭቱ እንዲታቀቡና ቀውሱንም ለመፍታት ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጡ ጥሪ አድርጓል።

ከዚህም በተጨማሪ ለአለም አቀፉ የበጎ አድራጎትና የሰብዓዊ መብቶች እንዲገዙና እርዳታ ድርጅቶችም በአስቸኳይ እርዳታ እንዲያደርሱ ደህንነቱ የተጠበቀ ሁኔታ እንዲያመቻቹ ለሁለቱም ወገኖች ጥሪ አቅርቧል።