ከፍተኛ ገንዘብ በቤታቸው ለማስቀመጥ የተገደዱት የሆንግ ኮንግ አስተዳዳሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለችን ከፍተኛ ደሞዝ ከሚያገኙ መሪዎች መካከል አንዷ የሆኑት የሆንግ ኮንጓ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካሪ ላም የባንክ አካውንተ ስለሌላቸው ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ በቤታቸው እንደሚያስቀምጡ ተናገሩ።
ካሪ ላም በአስተዳዳሪነታቸው የሚያገኙትን ገንዘብ በቤታቸው ውስጥ ለማከማቸት የተገደዱት በአሜሪካ መንግሥት በተጣለባቸው ዕገዳ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
በዋና አስተዳዳሪዋና በሌሎች የሆንግ ኮንግ ግዛት ባለስልጣናት ላይ የተጣለው ማዕቀብ ቻይና በግዛቲቱ ላይ ባወጣችው አዲስ የደኅንነት ሕግ ምክንያት ነው።
አስተዳዳሪዋ ይህንን ከተናገሩ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ቻይና የምትከፍላቸውን ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ እንዲት አድርጋ በማጓጓዝ ቤታቸው ድረስ እንደምታቀርብ ሽሙጦች እየወጡ ነው።
አስተዳዳሪዋ ካሪ ላም አርብ ምሽት በተላላፈው ቃለ ምልልሳቸው ላይ እንደተናገሩት "ለሁሉም ነገር ክፍያ ለመፈጸም ጥሬ ገንዘብ" እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።
በእንግሊዝኛ በቴሌቪዥን በቀረበው ቃለ ምልልስ ላይ "የባንክ አገልግሎት ማግኘት ያልቻለችውን የሆንግ ኮንግ ልዩ አስተዳደር ክልል ዋና አስፈጻሚን ነው የምትመለከቱት" ሲሊ ተናግረዋል።
"ቤቴ ውስጥ የገንዘብ ክምር አለ። መንግሥትም ደሞዜን በጥሬ ገንዘብ ነው የሚከፍለኝ" ሲሉም አክለዋል።
ዋና አስተዳዳሪዋ የባንክ አገልግሎት እንዳያገኙ በአሜሪካ መንግሥት "አላግባብ" ስለተጣለባቸውን ዕቀባ "ኩራት ይሰማኛል" ብለዋል።
የሆንግ ኮንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካሪ ላም በዓለም ላይ ካሉ ከፍተኛ ክፍያን ከሚያገኙ መሪዎች መካከል አንዷ መሆናቸው ይነገራል።














