ሆንግ ኮንግ አገር ጥለው የጠፉ የመብት ተሟጋቾች ይታሰሩልኝ አለች

የፎቶው ባለመብት, EPA/REUTERS
የሆንግ ኮንግ ፖሊስ ወደ ምዕራቡ የዓለም አገራት የሸሹ ስድስት የዴሞክራሲ አቀንቃኞች እንዲታሰሩ ጠየቀ።
ከመብት ተሟጋቾቹ መካከል ሳይመን ቺንግ፣ ናታን ሎው እና የአሜሪካ ዜግነት ያለው ሳሙኤል ቹ ይገኙበታል።
ሆንግ ኮንግ አዲስ ያወጀችውን የብሔራዊ ደኅንነት ሕግ ተላልፈዋል በሚል ነው ግለሰቦቹ እንዲታሰሩ የተፈለገው። በቤይጂንግ የቴሌቭዥን ጣቢያ “ችግር ፈጣሪዎች” ተብለዋል የመብት ተሟጋቾቹ።
የሆንግ ኮንግ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም።
የግዛቱ ምክር ቤት ምርጫ በኮሮናቫይረስ መራዘሙ ከተሰማ በኋላ ነበር ይህ ዜና የወጣው።
ተቃዋሚዎች ወረርሽኙ እንደ ምክንያት ቅርቦ ምርጫው መራዘሙን አይቀበሉም።
ቀድሞ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የነበረችው ሆንግ ኮንግ እስከ ጎርጎሮሳውያኑ 2047 ድረስ በቻይና ስር እንድትተዳደር ስምምነት አለ።
ነገር ግን ከዚህ ጊዜ ቀድሞ የመብት ጥሰት እየተፈጸመ ነው የሚሉ በርካታ ተቃዋሚዎች አሉ። ሆንግ ኮንግ አወዛጋቢውን የብሔራዊ ደኅንነት ሕግ ካወጣች ወዲህም ተቃውሞው ቀጥሏል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን እና አውስትራሊያ ለሆንግ ኮንግ እስረኛ አሳልፎ የመስጠት ስምምነታቸውን ከሻሩ አገሮች መካከል ናቸው።
የሚፈለጉት እነማን ናቸው?
የቻይና ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ እንደሚለው ስድስቱ ተጠርጣሪዎች የመገንጠል ሐሳብን በማቀንቀን እና ከውጪ ኃይሎች ጋር በመመሳጠር ወንጀለኛ ተብለዋል።
እነዚህ ወንጀሎች በአዲሱ ሕግ መሠረት፤ የእድሜ ልክ እስራት ያስቀጣሉ።
ሳይመን ቼንግ
በቀድሞው በዩናይትድ ኪንግደም የሆንግ ኮንግ ቆንስላ ይሠራ ነበር። በቅርቡም እዚያው ጥገኝነት አግኝቷል።
ባለፈው ነሐሴ ቻይና ለሥራ ሲሄድ በቁጥጥር ስር ውሎ ሆንግ ኮንግ ውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በመፍጠር ተከሷል።
በቻይና ቁጥጥር ስር ሳለ ተደብድቦ ሐሰተኛ ሰነድ ለመፈረም እንደተገደደ ይናገራል።
በድጋሚ የእስር ማዘዣ ሲወጣበት “አምባገነኑ መንግሥት ሊወነጅለኝ ይፈልጋል። ይሄ ለእኔ የሚያሳፍር ሳይሆን የሚያኮራ ነው” ብሏል።
ናታን ሎው
27 ዓመቱ ነው። የመብት ተሟጋች ሲሆን፤ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሸሽቷል። “ወንጀሌ ምን እንደሆነ አላውቅም። ምናልባትም ሆንግ ኮንግን በጣም ስለምወዳት ይሆናል” ይላል።
ሳሙኤል ቹዋ
የአሜሪካ ዜጋ ሲሆን፤ ሦስተኛው ተጠርጣሪ ነው።
የቤተ ክርስቲያን አገልጋዩ ሳሙኤል፤ 2014 ላይ የተነሳው ‘አምብሬላ ሙቭመንት’ [የዣንጥላ ንቅናቄ] በመባል የመታወቀውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከመሠረቱት አንዱ ነው።
“ኢላማ የተደረግኩ ብቸኛው ቻይናዊ ያልሆንኩ ሰው ሳልሆን አልቀርም። የመጨረሻው ግን አልሆንም። ስለ ሆንግ ኮንግ የሚቆረቆር ማንኛውም አሜሪካዊም ይሁን የሌላ አገር ዜጋም ኢላማ መደረጉ አይቀርም” ብሏል።
በአዲሱ የብሔራዊ ደኅንነት ሕግ መሠረት የሆንግ ኮንግ ነዋሪ ያልሆነ ሰውም ሊከሰስ ይችላል። ቻይና መረጋጋት እንዲሰፍን ሕጉ አስፈላጊ ነው ትላለች።
ሬይ ዎንግ
የመብት ተሟጋቹ ወደ ጀርመን የሸሸው 2017 ላይ ነበር።
የሚፈለጉ ሰዎች ዝርዝር የወጣው የዴሞክራሲ አርበኞችን ለማስፈራራት ነው ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
የመብት ተሟጋቾቹ ደጋፊዎች ለማሰባሰብ እየሞከሩ በመሆኑ ኢላማ እንደተደረጉም ያስረዳል።
ሎው ሆንግ
18 ዓመቱ ሲሆን፤ አሁን ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ይገኛል።
ወደዚያ የሄደው 2017 ላይ የነፃነት ምልክት የሆነ መግለጫ አርማን የሆንግ ኮንግ መሪ ከሆኑት ከካሪ ላም ፊት ለፊት ማውለብለቡን ተከትሎ ነበር።
ዌይን ቻን
ትላንት ከጋዜጠኞች ጋር ባደረገው ቆይታ “ዩናይትድ ኪንግደም መጥታችሁ እሰሩኝ” ሲል ተደምጧል። የዴሞክራሲ አቀንቃኙ ዌይን “ከእኔ በላይ ችግር ውስጥ ያሉት የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ናቸው። ስለራሴ ደኅንነት አላስብም” ብሏል ለሮይተርስ።














