ቻይና ዩናይትድ ኪንግደምን 'ጣልቃ አትግቢ' ስትል አስጠነቀቀች

አምባሳደር ሉ ዢያሚንግ
የምስሉ መግለጫ, አምባሳደር ሉ ዢያሚንግ

ቻይን ከሆንግ ኮንግ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዩናይትድ ኪንግደም ጣልቃ እንዳትገባ አስጠነቀቀች።

ቻይና አዲስ ብሔራዊ የደኅንነት ሕግ ማውጣቷን ተከትሎ አንድ የሆንግ ኮንግ የዴሞክራሲ ተሟጋች ዓለም አቀፍ ኃይሎች ጣልቃ እንዲገቡ በመጠየቁ ነው ማስጠንቀቂያው የመጣው።

የቻይናው አምባሳደር ሊው ዢአዎሚንግ፤ ዩናይትድ ኪንግደም ወደ ሦስት ሚሊዮን ለሚሆኑ የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ዜግነት ለመስጠት ተነሳሽነት ማሳየቷ "ጣልቃ ገብነት ነው" ብለዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ዜግነት የመስጠት ተነሳሽነት ያሳየችው ቻይና አዲሱን አነጋጋሪ ሕግ ካረቀቀች በኋላ ነው።

ተቃዋሚዎች ውሳኔው የሆንግ ኮንግን ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር የሚጋፋ ነው ብለዋል።

የመብት ተሟጋቹ ጆሽዋ ዎንግ፤ የሆንክ ኮንግ ነዋሪዎችና የዓለም ሕዝብም ለቻይና "ማጎብደድ" የለበትም ብሏል።

የቻይናው አምባሳደር በበኩላቸው ዩናይትድ ኪንግደም ዜግነት የመስጠት ሂደት የመጀመር ሐሳቧን መልሳ እንድታጤን አሳስበዋል።

"የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በሆንግ ኮንግ ጉዳዮች ዙርያ ኃላፊነት የጎደለው ንግግር እያሰማ ነው" ብለዋል።

የናይትድ ኪንግደም እንደምትለው፤ ቻይና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1997 የተደረሰውን ስምምነት እያከበረች አይደለም። ስምምነቱ ሆንግ ኮንግ ወደ ቻይና እስክትጠቃለል ባለው 50 ዓመት በተወሰነ ደረጃ ነፃነት ይሰጣታል።

የዩናይትድ ኪንግደም ቃል አቀባይ፤ ቻይና በሆንግ ኮንግ ጣልቃ መግባቷን ታቁም ብለዋል።

"ቻይና ዓለም አቀፍ ሕግን ማክበር ያለውን ጠቀሜታ ትረዳለች ብለን እናምናለን" ብለዋል።

አዲስ የተረቀቀውን ሕግ በተመለከተ ቃል አቀባዩ፤ "እስረኞችን ከሆንግ ኮንግ አሳልፎ በመስጠት ረገድ ብሔራዊውን የደኅንነት ሕግ እየገመገምን ነው" ብለዋል።

የአንድ እስረኛን ሰብዓዊ መብት የሚጋፋ ወይም ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ያለው ጉዳይ ከሆነ፤ እስረኛው ተላልፎ እንደማይሰጥም ተናግረዋል።

አሁን ላይ በቻይናና በዩናይትድ ኪንግደም መካከል ያለው አነጋጋሪ ጉዳይ የሆንግ ኮንግ ነባራዊ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የሁዋዌ እጣ ፈንታ ጭምርም ነው።

በ1.4 ቢሊዮን ቻይናውያን ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረገው ጥረት እንደሚከሽፍ ሊው ዢአዎሚንግ ተናግረዋል። ጣልቃ ገብነት የአገራቱን ግንኙነት እንደሚያሻክርም አክለዋል።

ባለፈው ሳምንት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ሁዋዌን በተመለከተ፤ ቻይናን "አደገኛ" ሲሉ ጠቅሰዋል። አምባሳደሩ በበኩላቸው ቻይና ዩናይትድ ኪንግደምን በዚህ መንገድ አትጠቅስም ብለዋል።

አዲሱ ሆንግ ኮንግን የተመለከተው የቻይና ሕግ፤ መገንጠል ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በሽብርተኛነት የሚከሰስ ሰው እድሜ ልክ ሊታሰርም ይችላል።

እንደ ጆሽዋ ዎንግ ያሉ ተቃዋሚዎች፤ ሕጉ የንግግር ነፃነትን ይገድባል ቢሉም ቻይና ግን ይህን አትቀበልም።

ጆሽዋ ዎንግ "ትግላችን ከባድ እንደሆነ እናውቃለን። ምንም ቢሆን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ያሉ ወዳጆቻችን ትግላችንን ይደግፋሉ" ይላሉ።