የሆንግ ኮንግ 'የተቃውሞ' ኬክ ከውድድር ታገደ

የፎቶው ባለመብት, 3rd Space
የሆንግ ኮንግ ተቃውሞን የሚገልጽ ኬክ ከእንግሊዝ የኬክ ጋጋሪዎች ውድድር ውጪ መደረጉ "ፖለቲካዊ ማዕቀብ" ነው ተብሏል።
ኬኩ የሆንግ ኮንግ ተቃውሞ ምልክት በሆነው ጃንጥላ እና ጭንብል ያጌጠ ነው።
ኬኩን የጋገረው ድርጅት ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ ከቻይናውያን ተወዳዳሪዎች የቀረበውን ቅሬታ ተከትሎ ኬኩ ከውድድር ውጪ መደረጉን ያምናሉ። አወዳዳሪው አካል በበኩሉ፤ ኬኩ ከውድድር እንዲወጣ የተወሰነው አንድ የኬኩ ክፍል ገዝፎ በመገኘቱ ነው ይላል።
ባለፉት አምስት ወራት ሆንክ ኮንግ ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲካሄድ መሰንበቱ ይታወሳል።
እንግሊዝ፣ በርሚንግሀም ውስጥ እየተካሄደ ባለው የኬክ ውድድር ከመላው ዓለም የተውጣጡ ጋጋሪዎች ተሳትፈዋል።
ሆንግ ኮንግ ውስጥ የሚገኘው 'ሰርድ ስፔስ' ካፍቴርያ ኬክ ጋጋሪ ለውድድር ያስገቡት ኬክ በተቃውሞ ምልክቶች የተሞላ ነው። ጥቁር የለበሰ ተቃዋሚ እና የአስለቃሽ ጭስ ምልክትን መጥቀስ ይቻላል።
ኬኩ የሆንግ ኮንግ ተቃውሞን የሚያስተጋባ 'ግሎሪ ቱ ሆንግ ኮንግ' የተሰኘ ሙዚቃም ያጫውታል።

የፎቶው ባለመብት, 3rd Space
የካፌው ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ኬኩ የሆንግ ኮንግን ተቃውሞ ተመርኩዞ የተጋገረ ነው።
"የኬኩ ዲዛይን ሆንግ ኮንግ ውስጥ ምን እተከናወነ እንደሆነ ያሳያል" ብለዋል።
የቻይና ተወዳዳሪዎች ኬኩ፤ "አስከፊ ይዘት ያለውና የሆንግ ኮንግን ነጻ አስተዳደር የሚያሳይ ነው" ብለው ቅሬታ ማሰማታቸውንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, 3rd Space
አወዳዳሪዎቹ መጀመሪያ ላይ ኬኩ የሚያጫውተውን ሙዚቃ ካገዱ በኋላ ኬኩን ከውድድር ውጪ አድርገዋል። የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች አወዳዳሪዎቹ "ፖለቲካዊ ማዕቀብ ጥለዋል" ሲሉ እየከሰሱ ይገኛሉ።
የውድድሩ አዘጋጆች በበኩላቸው "ኬኩ ከውድድር ውጪ የተደረገው ከመጠን በላይ ስለሆነ እንጂ ከፖለቲካዊ ይዘቱ ጋር አይገኛኝም" ብለው በፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።












