የሆንግ ኮንግ የሕዝብ እንደራሴዎች ተቧቀሱ

የሕጉ ነቃፊዎችና ደጋፊዎች በሕግ መወሰኛ ምክርቤቱ ውስጥ ተጋጭተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሆንግ ኮንግ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በወንጀል የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች ለቻይና ተላልፈው እንዲሰጡ የሚፈቅደውን ሕግ ለመቀየር በሚደረግ ክርክር ላይ በተፈጠረ አለመግባባት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የቡጢ ሜዳ ሆኗል።

በርካታ የምክር ቤቱ አባላት የተጎዱ ሲሆን አንድ ፖለቲከኛ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

ውጥረቱ የተባባሰው ፖለቲከኞች መሳደብና ከጠረጴዛ ጠረጴዛ መዝለል ሲጀምሩ እንደሆነ ተገልጿል።

ሆንግ ኮንግ 'ዋን ካንትሪ ቱ ሲስተም' (አንድ ሀገር ሁለት ስርአት እንደማለት) በሚለው ፖሊሲ መሰረት ከቻይና የተለየ ሕግ ያላት ግዛት ነች።

ቤይጂንግ ከቅኝ ገዢ እንግሊዝ ሆንግ ኮንግን የተረከበችው እ.ኤ.አ በ1997 ሲሆን፤ በወቅቱም ግዛቲቱ ከውጭ ግንኙነትና ከመከላከያ በስተቀር ራሷን የቻለች ግዛት ሆና ለ50 ዓመት እንድትቀጥል ተስማምታ ነበር።

ነገር ግን የቤይጂንግ መንግሥት አፍቃሪ ናቸው የሚባሉት ኬሪ ላም፤ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ወንጀል የሰሩ ግለሰቦች እንደየጉዳያቸው አይነት ወደታይዋን፣ ቻይና እና ማካኡ ተላልፈው እንዲሰጡ የሚፈቅደውን ሕግ አቀርበዋል።

ፖለቲከኛው ለዚህ ሕግ መነሻ የሆናቸው የ19 ዓመት ሆንግ ኮንጓዊ ከነፍሰ ጡር ፍቅረኛው ጋር በታይዋን እየተዝናኑ ሳሉ ፍቅረኛውን በመግደሉ ነው።

በወቅቱ ታይዋን ተጠርጣሪውን አሳልፋ መስጠት ብትፈልግም፤ የሆንግ ኮንግ ባለስልጣናት ግን በሁለቱ ሀገራት መካከል ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት አለመኖሩን በመጥቀስ አሻፈረኝ አሉ።

የሕጉ ተቺዎች እንደሚሉት፤ ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ የሚሰጠውን ሕግ መቀየር የሆንግ ኮንግን ነፃነትን ይጋፋል።

ይህንን ረቂቅ ሕግ በመቃወምም በሆንግ ኮንግ ትልቅ የሕዝባዊ ሰልፍ ተደርጎም ነበር።

ባለስልጣናት እንደሚሉት፤ ለውጡን ማድረግ ያስፈለጋቸው በነፍስ ማጥፋት የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን ወደታይዋን ለመውሰድ እንዲያስችላቸው ነው።

አንድ የቤይጂንግ ደጋፊ የሆኑ ፓለቲከኛ "ለሆንግ ኮንግ የሐዘን ቀን ነው"ሲሉ ተደምጠዋል።