በቤተ ሙከራ ስሚሠራው ስጋ ምን ያህል ያውቃሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስጋ አፍቃሪ ቢሆኑም በተለያየ ምክንያት ስጋ ላይመገቡ ይችላሉ። ነገር ግን እንደ ስጋ ያለ ሲጎርሱት አፍ የሚሞላ፣ ሆድ ላይ ቁጭ ሲልም አንጀት የሚያርስ ደግሞም አምሮት የሚቆርጥ ነገር ቢፈልጉ ምን ይመገባሉ?
ሀሳብ አይግባዎ። ተፈጥሯዊውን ስጋ የሚመስል ነገር ግን ከስጋ ነፃ የሆነ ምርት መጥቷል። ምርቱ የስጋ በርገር ወይም ደግሞ የቋሊማ ተመጋቢዎችን ፍላጎት ያረካል ተብሎ ይታሰባል።
አትክልት ተመጋቢዎች ስጋ በጤና ላይ ከሚያስከትለውን ጉዳት ለመዳንና ለአካባቢ ጥበቃ ሲሉ ከስጋ ጋር ተለያይተዋል።
የአትክልት ተመጋቢዎች ምርጫ በምግብ ምርት ዘርፍ ውስጥ ስማቸውን ለተከሉ ድርጅቶች ጥሩ የገበያ እድል ፈጥሯል።
ስጋን ተክቶ የመጣው ስጋ መሰል ምርት የትክክለኛው ስጋ መአዛ፣ መልክና ይዘት አለው።
ተፈጥሯዊውን ስጋ ይተካል የተባለው ሰው ሰራሽ ስጋ የተሠራው ከአትክልት ምርቶች ነው። በአትክልት ውስጥ ያሉ ፕሮቲኖች ያሉት ሲሆን፤ ቀይ ስር ተጨምቆ የሚወጣው ፈሳሽ እንደ ደም ሆኖ ጥቅም ላይ ይውላል።
ቤተ ሙከራ ውስጥ ሰው ሰራሽ ስጋ ከእንስሳት ህዋስ የሚሠሩ ድርጅቶችም አሉ። ሰው ሰራሽ ስጋው በቅርቡ ገበያ ላይ ይውላል ተብሎም ይጠበቃል።
'ጀስት' የተባለ የአሜሪካ ድርጅት በቤተ ሙከራ የተዘጋጀ የዶሮ ስጋ ምርቱን በዚህ ዓመት መጨረሻ ለሽያጭ ያቀርባል ተብሎ ያጠበቃል።
እነዚህ ምርቶች ታሳቢ ያደረጉት አትክልት ተመጋቢዎችን ብቻ ሳይሆን ስጋ የሚበሉ ሰዎችን ጭምርም ነው።
መሰል ምርቶች ገበያ ላይ ከመዋላቸው በፊት ጤናማ ስለመሆናቸው ምርመራ ይደረግባቸዋል። አውሮፓ ውሰጥ የምርምር ሂደቱ እስከ ሁለት ዓመት ሊወስድ ይችላል።
ሰው ሰራሽ ስጋ አምራቾች ተመጋቢዎችን ያሳምኑ ይሆን?
ብዙዎች ቤተ ሙከራ ውስጥ የሚሠራ ስጋ ለመመገብ ፍቃደኛ አይደሉም። በተቃራኒው የስጋው አሠራር ሂደት በግልጽ ከተነገራቸው ሰው ሰራሽ ስጋ መመገብ የሚሹ ሰዎች አሉ።
ሰው ሰራሽ ስጋ ከተፈጥሯዊ ስጋ ጋር ተመሳሳይ ስም ሊኖረው ይገባል ወይ? ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው።
'ካትል አሶሴሽን' የተባለ የአሜሪካ ድርጅት ስጋ የሚለው ቃል የተፈጥሯዊ ስጋ ብቻ መጠሪያ መሆን አለበት ሲል ይከራከራል።
አውሮፓ ውስጥ ሰው ሰራሽ ስጋ ተጠቅመው በሚዘጋጁ ምግቦች በሰው ሰራሹ መካከል የመጠሪያ ልዩነት እንዲኖር የማድርግ እቅድ አለ።
ፈረንሳይ ተጠቃሚዎችን ግራ ያጋባሉ ያለቻቸውን የሰው ሰራሽ ስጋ ስያሜዎች ለማገድ ወስናለች።
ሰው ሰራሽ ስጋ አምራቾች ምርታቸው የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ላለው ተጽዕኖ መፍትሄ እንደሚሰጥ ያምናሉ።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት ተፈጥሯዊው ስጋ ለ 'ግሪን ሀውስ' ጋዝ ልቀት ምክንያት ነው። ተመራማሪዎቹ ተፈጥሯዊ ስጋ መመገብ ከሚያስከትለው ተጽእኖ ለመዳን ሰው ሰራሽ ስጋ መመገብን ቢደግፉም፤ ሰው ሰራሽ ስጋ በቤተ ሙከራ ውስጥ ለመሥራት የሚያስፈልገው ሀይል ጥያቄ ያስነሳል።
ሰው ሰራሽ ስጋ የአርብቶ አደሮች ሕይወት ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖ ሌላው ጥያቄ ነው።












