በሆንግ ኮንግ የተነሳው ተቃውሞ በውጭ ኃይሎችን የታገዘ ነው ሲል የመንግሥት ሚድያ ወቅሷል

Hong Kong protest

የፎቶው ባለመብት, Reuters

'የውጭ ኃይሎች' ሆንግ ኮንግ ውስጥ ብጥብጥ በመፍጠር ቻይናን ለመጉዳት እየሞከሩ ነው ሲል የቻይና መንግሥት ጋዜጣ ቅሬታ አሰምቷል።

ዕለተ ሰንበት ሺዎች አደባባይ ወጥተው የሃገሪቱ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሊያፀድቀው ያሰበውን አዋጅ አውግዘዋል፤ ረቂቁ የሆንግ ኮንግ ተቃዋሚዎችን አአከርካሪ ለመስበር ያለመ ነው በማለት።

በፖሊስ እና ተቃዋሚዎች መካከል ግጭት መፈጠሩ አልቀረም። ቢያንስ ሶስት ፖሊሶች እና አንድ ጋዜጠኛ ተጎድቷል ይላል የፖሊስ ዘገባ።

የቻይና መንግሥት ግን ረቂቁ በእቅዱ መሠረት መሄዱን ይቀጥላል ሲል ተደምጧል።

የተቃውሞ ሰልፉ አዘጋጆች አንድ ሚሊዮን ሰው ወጥቷል ሲሉ ፖሊስ 240 ሺህ ብቻ ነው ያየሁት ሲል አስተባብሏል።

'ቻይና ደይሊ' የተሰኘው ጋዜጣ በርዕሰ አንቀፁ 'አንዳንድ የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች በተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በውጭ አጋሮቻቸው ምላስ ተታለው ረቂቅ አዋጁን ሊቃወሙ ወጥተዋል' ሲል አትቷል።

ጋዜጣው አክሎም 'መቼም በጤናው ያለው ሰው ይህን በጉጉት የተጠበቀ አዋጅ አይቃወምም' በማለት የሰልፈኞቹን አእምሮ ጤና ተጠራጥሯል።

ተቺዎች አዲሱ ሕግ በልዩ አስተዳድር የምትመራው ሆንግ ኮንግ ያላትን አንፃራዊ ነፃነት የሚቀማ ነው ባይ ናቸው።

ረቂቁ ዜጎች ወንጀል ሠርተው ታይዋን ወይንም ሆንግ ኮንግ ውስጥ ቢደበቁ እንኳ ከእሥር አያመልጡም የሚል አንቀፅ አዝሏል።

ከዚህ በፊት በታይዋን እና ሆንግ ኮንግ መካከል እሥረኛ አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ባለመኖሩ ቻይናውያንን ይህንን ቀዳዳ ይጠቀሙበት እንደነበር ተነግሯል።

ሆንግ ኮንግ የቻይና ግዛት ብትሆንም በልዩ አስተዳደር የምትመራ መሆኗ ለዒ ሺን ፒንግ መንግሥት ነገሮችን ያወሳሰበ ይመስላል።