ቻይናና ሩስያ የትራምፕን የግል ስልክ ጠልፈው ሲሰልሉ ነበር፡ ኒውዮርክ ታይምስ

ዶናልድ ትራምፕ የግል ስልካቸው በቻይናና ራሺያ ተጠልፏል የሚለው ስጋት አይሏል

የፎቶው ባለመብት, THE WHITE HOUSE

የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ የግል ስልካቸው በቻይናና ራሺያ ተጠልፏል የሚለው ስጋት አይሏል

ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የዶናልድ ትራምፕ የግል ስልክ ሳይጠለፍ አይቀርም የሚል ዘገባ ይዞ መውጣቱን ተከትሎ ጉዳዩ በስፋት መነጋገሪያ ሆኗል።

ጋዜጣው እንደሚለው ከሆነ ቻይናና ሩስያ የዶናልድ ትራምፕን አስተሳሰብ ለመረዳት እንዲያስችላቸው የፕሬዚዳንቱን የግል ተንቀሳቃሽ ስልክ ሳይጠልፉት አልቀረም።

ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ይህ ዘገባ ትንሽ ያበሳጫቸው ይመስላል።

ትናንት በትዊተር ገጻቸው ላይ በለጠፉት የመልስ ምት "ተንቀሳቃሽ ስልኬን የምጠቀመው ከስንት አንዴ ነው። እናንተ እንደሁ የውሸት ዜና ጠፍጥፋችሁ መጋገርን ታውቁበታላችሁ" ሲሉ ብስጭታቸውን ገልጸዋል።

ይህንን ዜና የሰማችው ቻይና በበኩሏ ቀልድ ቢጤ ጣል አድርጋለች፤ "ክቡር ፕሬዝዳንት፣ ስለምን አይፎንዎን ጥለው የኛ ምርት የሆነውን ሁዋዌን አይጠቀሙም?" ስትል።

ዘገባው እንደሚለው የትራምፕ ረዳቶች ፕሬዝዳንቱ የግል ስልካቸውን እንዳይጠቀሙ በተደጋጋሚ መክረዋቸዋል፤ አሻፈረኝ ቢሉም።

የቻይናው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሕዝብ ግንኙነት አለቃ ሁዌ ቺኒዪንግ ሐሙስ ዕለት እንዲህ ሲሉ ቀለዱ፤ "ዛሬ ስለ ትራምፕ ስልክ የተባለውን ስሰማ ኦስካርን ለማሸነፍ ጥሩ የፊልም ስክሪፕት መጻፍ የሚችሉ ትጉሃን እንዳሉ ነው የተረዳሁት።''

ወይዘሮዋ ጨምረው እንደቀለዱት "ይህን ያህል ነገሩ ካስጨነቃቸው ፕሬዝዳንቱ አፕል ስልክን መጠቀም ማቆም ይኖርባቸዋል፤ ህዋዌ አለላቸው" ብለዋል።

ወይዘሮዋ በዚህም አላበቁም፤ " ወይ ደግሞ ህዋዌንም መጠቀም ካሰጋቸው፣ ለምን ስልክ የሚባል ነገር አይቀርባቸውም? እስከናካቴው ከተቀረው ዓለም ጋር መገናኘት ቢያቆሙስ?" ብለዋል።

ሩስያም የፕሬዝዳንቱን ስልክ ጠልፈሻል መባሏን አስተባብላለች።

የፕሬዝዳንት ፑቲን ቃል አቀባይ ሲናገሩ "እኛኮ እንዲህ ዓይነት ዘገባዎችን ከመጤፍም አንቆጥራቸው፤ እንደ ፌዝ ነው የምንመለከታቸው" ብለዋል።

ኒውዯርክ ታይምስ በዚህ ዘገባው አረጋገጥኩ እንደሚለው ከሆነ ቻይናም ሩስያም የዶናልድ ትራምፕን የግል የስልክ ንግግሮች ጠልፈው ያዳምጣሉ። ይህም ፕሬዝዳንቱ በቁልፍ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግላዊ አስተያየት እንዲረዱ አግዟቸዋል። ይህ ደግሞ በድርድር ጊዜ የፕሬዝዳንቱን አስተሳሰባን በቀላሉ ለመግራት ይረዳቸዋል።

ሁለቱ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች የሆኑት ቻይናና አሜሪካ በቅርቡ በከፈቱት የንግድ ጦርነት የዓለምን ምጣኔ ሐብት እያመሱት ይገኛሉ።

የቻይናው ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች የሆኑት ህዋዌና ዜድቲኢ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ለአሜሪካ ደኅንነት ስጋት ናቸው በሚል ሲብጠለጠሉ ቆይተዋል።

በ2012፤ እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ፤ የአሜሪካ ኮንግረስ ፓናል ሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች ለአገሪቱ ስጋት ስለሆኑ አሜሪካ ውስጥ ከማንኛውም ውጤታማ የንብረት ቁጥጥር እንዲገለሉ ሐሳብ ማቅረቡ ይታወሳል።