በኬንያ ሐሰተኛ የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤት ያቀረቡ መንገደኞች ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከኬንያ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሊጓዙ ከነበሩ መንገደኞች መካከል 21ዱ ሐሰተኛ የኮቪድ-19 ምርመራ መረጃ ማቅረባቸውን ተከትሎ ለእስር መዳረጋቸው ተገልጿል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከዚህ ቀደምም ከኬንያ የሚገቡ መንገደኞች ሐሰተኛ የኮቪድ-19 መረጃ አቅርበዋል በሚል የቪዛ እገዳ ጥላለች።
ተጠርጣሪዎቹ በዛሬው እለት ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡም የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በተወሰነ መልኩ መቀነስ አሳይቶ የነበረው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለሁለተኛ ዙር ማገርሸቱን ተከትሎ ኬንያ በርካታ ሕዝብ የሚሰባሰብባቸው ሁነቶች ላይ ገደብ ጥላለች።
በሳምንቱ መጀመሪያ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ ቱኒዝያና አልጀሪያን ጨምሮ 13 አገራት ላይ የቪዛ እገዳ ጥላለች።
በትናንትናው ዕለት፣ ኅዳር 17/ 2013 ዓ.ም በቁጥጥር ስር የዋሉት 21 መንገደኞች መነሻቸውን ከኬንያዋ መዲና ናይሮቢ አድርገው ወደ ዱባይ ለመሄድ ሲሉ የተያዙትም በኬንያ አየር ማረፊያ ነው።
የተያዙት ሐሰተኛ የህክምና ማስረጃ ከኮቪድ- 19 ነፃ መሆናቸውን ያሳያል።
በቅርቡም በተመሳሳይ ከኬንያ ወደ ዱባይ ከበረሩ መንገደኞች መካከል 100 የሚሆኑ ኬንያውያን ሐሰተኛ መረጃ ይዘው የነበሩ ሲሆን አየር ማረፊያው ላይ በተደረገላቸውም ምርመራ ግማሹ ቫይረሱ እንደተገኘባቸውም ናይሮቢ ኒውስ የተባለው የኬንያ ድረ ገፅ ዘግቧል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮም ኬንያ 80 ሺህ 102 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን 1 ሺህ 427 ግለሰቦችም በቫይረሱ ህይወታቸውን አጥተዋል።
በትናንትናው ዕለት ተጨማሪ 780 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ የኬንያ ጤና ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን ይህንን ተከትሎም በርካታ ሰዎች በሚታደሙባቸው ሥነ ሥርቶች ላይ አዲስ እገዳ ወጥቷል።
በሠርግ ላይ መገኘት የሚችሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 50 የቀነሰ ሲሆን በቀብር ላይም 100 ሰዎች ብቻ እንዲታደሙ ታዟል። አብያተ ክርስቲያናትም የአገልግሎት ሰዓታቸውን ወደ 90 ደቂቃ እንዲቀንሱ ተደርገዋል።












