አሜሪካ በሆንግ ኮንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ላይ ማዕቀብ ጣለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የገንዘብ ሚንስቴር በሆንግ ኮንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኬሪ ላም እና 10 የሆንግ ኮንግ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ጣለ።
የገንዘብ ሚንስትሩ ስቲቨን ሙንሽን ማዕቀቡ ትኩረት ያደረገው የሆንግ ኮንግ ሉዓላዊነት ላይ ጫና የሚያሳድሩት ላይ ነው ብለዋል።
"ዩናይትድ ስቴትስ ከሆንግ ኮንግ ህዝብ ጎን ናት” ብለዋል ስቲቨን ሙንሽን።
ይህ የአሜሪካ ውሳኔ የመጣው ቻይና በሆንግ ኮንግ ላይ ብሄራዊ የደህንነት ሕግ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች በኋላ ነው።
በርካቶች ቻይና በሆንግ ኮንግ ላይ የጣለችውን ሕግ የሆንግ ኮንግን ነጻነት የሚጋፋ ነው ይላሉ።
ማዕቀብ ከተጣለባቸው መካከል የሆንግ ኮንግ ፖሊስ ኮሚሽነር እና በርካታ ፖለቲከኞች ይገኙበታል።
አሜሪካ፤ የሆንግ ኮንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ኬሪ ላም “ነጻነትን እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱን የሚጎዱ የቤይጂግ ፖሊሲዎችን ሆንግ ኮንግ ላይ ያስፈጽማሉ” ስትል ትተቻለች።
ቻይና በሆንግ ኮንግ ላይ የጣለችውን ብሄራዊ የደህንነት ሕግ ከአሜሪካ በተጨማሪ ሌሎች ምዕራባውያን አገራት አጥብቃ ይቃወሙታል። የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ማይክ ፖምፔዮ፤ ሕጉ የሆንግ ኮንግ ሕዝብ መብት እና ነጻነትን የሚጥስ ነው ብለውታል።
ቻይና በበኩሏ አጨቃጫቂ ሕጓ በሆንግ ኮንግ የውጪ ጣልቃ ገብነትን ለማስቆም አስፈላጊ ነው ስትል ትከራከራለች።
የቀድሞ የሲአይኤ አለቃ የአሁኑ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ በግለሰቦቹ ላይ አሜሪካ የጣለችውን ማዕቀብ ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ “የቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ የሆንግ ኮንግ ህዝብ ሉዓላዊነት እንደማያከብር አስመስክሯል” ብለዋል።
“ፕሬዝደንት ትራምፕ ግልጽ እንዳደረጉት፤ አሜሪካ ሆንግ ኮንግን እንደ ‘አንድ አገር፤ አንድ ስርዓት’ አድርጋ ነው የምትመለከታት። የሆንግ ኮንግ ህዝብ ነጻነትን የሚጋፉ ግለሰቦች ላይም እርምጃ ይወሰዳል” ብለዋል።
ማዕቀቡ የተጣለባቸው 11 ግለሰቦች በአሜሪካ የሚኖራቸው ንብረት የሚወረስ ሲሆን ገንዘባቸው ደግሞ እንዳይንቀሳቀስ ይደረጋል ተብሏል።
ማዕቀቡ የተጣለባቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ከአንድ ወር በፊት አሜሪካ ማዕቀብ ልትጥልባቸው እንደምትችል በጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “በአሜሪካ ምንም አይነት ንብረት የለኝም። አሜሪካ ሄዶ የመኖር ሃሳብም የለኝም” ብለው ነበር።
ከዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በተጨማሪ የሆንግ ኮንግ ፖሊስ ኮሚሽነር የሆኑት ክሪስ ታንግ፣ እስከ እአአ 2019 ድረስ የሆንግ ኮንግ ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት ስቴጸን ሎ፣ የሆንግ ኮንግ ፍትህ ጸሃፊ ቴሬሳ ቼንግ እንዲሁም የደህንነት ጸሃፊ ጆን ሊ ማዕቀቡ ከተጣለባቸው 11 ግለቦች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።














