ጃዋር መሐመድ፡ በአቶ ጃዋር እና በሌሎች ላይ የተፈቀደው ቀዳሚ ምርመራ ምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, Yadi Pictures, BBC, Hamza Borana/Facebook
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ ችሎት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን እንዲያሰማ ፈቅዷል።
የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለማድመጥም ፍርድ ቤቱ ለነሐሴ 4 2012 ቀጠሮ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ይህ ውሳኔ የሰጠው ተጠርጣሪዎች እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ሐሙስ፣ ሐምሌ 30 ፍርድ ቤት በቀረቡብት ወቅት ነበር።
በዚህ የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ውስጥ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሃምዛ አደን (ቦረና)፣ ጋዜጠኛ መለሰ ዲሪብሳ፣ የዓለምወርቅ አሳ፣ ጌቱ ቱዳ፣ ሸምሰዲን ጣሃን ጨምሮ በአጠቃላይ 14 ሰዎች ተካትተዋል።
ሐሙስ፣ ሐምሌ 30 በተካሄደው የችሎት ውሎ ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ናቸው ከተባሉ 15 ግለሰቦች መካከል 5 ሰዎች በዐቃቤ ሕግ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑ ተነግሯል።
እነዚህ 5 ሰዎች ማንነታቸው ሳይጠቀስ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ዐቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ለመሆኑ ቀዳሚ ምርመራ ምንድነው?
የሕግ አማካሪ እና ጠበቃው አቶ ታምራት ኪዳነማርያም በቅድሚያ አንድ ሰው ተጠርጥሮ ከተያዘ አንስቶ ብይን እስከሚሰጥበት ድረስ ያለውን የሕግ አካሄድ ያስረዳሉ።
"አንድን ሰው በወንጀል ተጠርጥሮ የሚይዘው ፖሊስ ነው። የወንጀል ምርመራው የሚያጣራው ደግሞ በፖሊስ ውስጥ ያለው ምርመራ አጣሪ ክፍሉ ነው" ይላሉ አቶ ታምራት።
ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋለውን ግለሰብ ቃል ይቀበላል። አስፈላጊ ከሆነ ተጠርጣሪውን በማረፊያ ቤት ይቆያል። ተጠርጣሪውን ማሰር ሳያስፈልግ ምርመራውን ማካሄድ የሚቻል ከሆነ ግን፤ "ተጠርጣሪው ቃሉን ሰጥቶ፣ ዋስ ጠርቶ ወደ ቤቱ ሊሄድ ይችላል" ይላሉ።
አንድ ተጠርጣሪ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ከተደረገ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንደሚኖርበት የሚያስታውሱት አቶ ታምራት፤ ፍርድ ቤትም ለመርማሪ ፖሊስ እስከ 14 ቀናት የሚረዝም የምርመራ ጊዜ ሊሰጥ እንደሚችል ይናገራሉ።
"ፍርድ ቤት ሊፈቅድ የሚችለው የምርመራ ጊዜ ቢበዛ 14 ቀናት ናቸው" የሚሉት አቶ ታምራት፤ የግድ ግን ፍርድ ቤት የሚፈቅደው 14 ቀናት እንዳልሆነ ያሳስባሉ። "3 ቀን ሊሆን ይችላል፣ 1 ቀን ሊሆን ይችላል። ፍርድ ቤት ይበቃል ብሎ የሚያምነው ጊዜ ይሰጣል" ይላሉ።
ፖሊስ በተደጋጋሚ ምን ያክል ጊዜ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት መጠየቅ ይችላል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ "እሱ ሕጋችን ላይ ክፍተት አለው። ፖሊስ እየደጋገመ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ ይችላል። ፍርድ ቤት ግን የፖሊስን ጥያቄ የመቀበል ሕጋዊ ግዴታ የለበትም። እንደውም የፖሊስን ጥያቄ መርምሮ ካላመነበት አለመቀበል ይጠበቅበታል" ይላሉ።
የፖሊስ የምርመራ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ጉዳዩ ወደ ዐቃቤ ሕግ እንደሚያመራ እና ዐቃቤ ሕግ ሶስት ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችል አቶ ታምራት ያስረዳሉ።
"የፖሊስ ምርመራ ሲጠናቀቅ ጉዳዩ ወደ ዐቃቤ ሕግ ያመራል። ምርመራው በተጠናቀቀ 15 ቀናት ውስጥ ክስ ሊመሰርት ይችላል። ወይም የተሰበሰበው ማስረጃ በቂ ካልሆነ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ሊወስን ይችላል። አልያም ደግሞ የተሰበሰበው ማስረጃ ተጠርጣሪው ወንጀሉን ስለመፈጸሙ የሚያመላክት ነገር ከሌለበት ዐቃቤ ሕግ ተጠርጣሪውን በነጻ ሊያሰናብተው ይችላል" ሲሉ ያብራራሉ።
ቀዳሚ ምርመራ በኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ ያለ መሆኑን በመጥቀስም፣ ከዚህ ቀደም በነበሩት የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ እንጂ በአሁኑ ወቅት ብዙ ጊዜ ሥራ ላይ ሲውል እንደማይታይ አቶ ታምራት ይናገራሉ።
የቀዳሚ ምርመራ ዋና ዓላማም ምስክሮች ወደፊት ፍርድ ቤት ቀርበው ምስክርነታቸውን የማይሰጡበት አንዳች ምክንያት የሚኖር ከሆነ፤ ቀድመው ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ማስደረግ እና የተሰጠው ምስክርነትን ክስ ከተመሰረተ በኋላ ትክክለኛውን ብይን ለመስጠት እንዲረዳ እንደሆነ የሕግ ባለሙያው ይናገራሉ።
"በተለይ በደርግ እና አጼ ኃይለስላሴ ጊዜ ሩቅ ቦታዎች ላይ ቀዳሚ ምርመራ ይሰራበት ነበር። በድሮ ጊዜ ራቅ ባለ ወረዳ ላይ ከባድ ወንጀል ከተፈጸመ ፖሊስ ወንጀሉን ይመረምር እና የፍርድ ሂደቱ የሚታየው ክፍተኛ ፍርድ ቤት በሚባለው የክፍለ ሃገር ዋና ከተማ በሚገኝበት ከተማ ላይ ነው። ይህ ማለት ምርመራው የተከናወነው በወረዳ ሲሆን፣ የፍርድ ሂደቱ የሚታየው ደግሞ ሌላ ከተማ ላይ ነው። በእንደዚህ ሁኔታዎች ላይ የቀዳሚ ምርመራ ይከናወናል" ይላሉ።
አቶ ታምራት ይህንን በዝርዝር ሲያስረዱ፤ "ምስክሮች ክፍተኛው ፍርድ ቤት ተገኝተው ምስክርነታቸውን ከመስጠታቸው በፊት ሊሰወሩ ይችላሉ፤ ከአገር ሊሰደዱ ይችላሉ፣ ሞት ሊያጋጥም ይችላል የሚሉ ሌሎች አሳማኝ ምክንያቶች ሲያጋጥሙ፤ በዛው በወረዳው ፍርድ ቤት ቀርበው ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። ክስ ሳይቀርብ ክስ የቀረበ በሚመስል ሁኔታ ምስክሮቹ ቃላቸውን በፍርድ ቤት እንዲሰጡ ይደረጋል።"
ከዚያም በከፍተኛው ፍርድ ቤት ክስ ሲመሰረት በወረዳው ፍርድ ቤት የተሰጠው ምስክርነት እንዲቀርብ ይደረጋል፤ በዚህም ምክንያት በምስክር እጦት ባክኖ ሊቀር የሚችል የወንጀል ድርጊት ብይን ያገኛል ሲሉ ያስረዳሉ።
ቀዳሚ ምርመራን የሚያካሂደው ማነው?
የቀዳሚ ምርመራውን ፍርድ ቤት እንደሚያከናውን አቶ ታምራት ይናራሉ። "ቀዳሚ ምርመራውን የሚያካሄደው በፍርድ ቤት ነው። የቀዳሚ ምርመራ ፋይል ይከፈታል። ፖሊስ ከአቃቤ ሕግ ጋር አብሮ ይቀርባል። ተከሳሹም በጠበቃ ተወክሎ ልክ ክስ እንደቀረበ ተደርጎ ምስክሩ ቃሉን ይሰጣል።"
በቀዳሚ ምርመራ ወቅት ክስ ሳይመሰረት ምስክሮች በፍርድ ቤት ተገኝተው ቃላቸውን ሲሰጡ፤ መርማሪ ፖሊስ፣ አቃቤ ሕግ፣ ተከሳሾች እና የተከሳሾች ጠበቆች እንደሚገኙ አቶ ታምራት ያብራራሉ።
በቀዳሚ ምርመራ ወቅት ምስክሮች በፍርድ ቤት ቀርበው ምስክርነታቸውን ሲሰጡ በተጠርጣሪዎች እና በጠበቆች አማካኝነት መስቀለኛ ጥያቄዎች ሊቀርቡላቸው እንደሚችልም አቶ ታምራት ይናገራሉ።
ቀዳሚ ምርመራ የፍርድ ሂደትን ሊያጓትት ይችላል?
"በእርግጥ ትንሽ ሊያጓትት ይችላል። ወደ ቀዳሚ ምርመራ ከሚገባ ምርመራው በፖሊስ ተጠናቆ፤ ጉዳዩ ወደ ዐቃቢ ሕግ በቀጥታ ቢሄድ ሊያጥር ይችላል። ግን ክስ ከተመሰረተም በኋላ ምስክርነት ስለሚሰጥ ቀዳሚ ምርመራ ያን ያክል የፍርድ ሂደትን በጣም ያጓትታል ማለት አይደለም" ይላሉ የሕግ ባለሙያው።
አቶ ታምራት ቀዳሚ ምርመራ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ እንደሚያመዝን ይናገራሉ። ለዚህም ምክንያቱን ሲያስረዱ፤ ምስክሮች በፍጥነት ጫና ሳይደርስባቸው ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ያደርጋል፣ ከአቅም በላይ በሆነ ጉዳይ ወደፊት ምስክርነታቸውን መስጠት የማይችሉት ቀድመው ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ያደርጋል።
ከመጋረጃ በተስተጀርባ የሚሰጥ ምስክርነት
ለምስክር፣ ለግለሰቦች ወይም ለአገር ደህንነት ሲባል ፍርድ ቤት ዝግ ችሎት ሊያካሂድ እንደሚችል አቶ ታምራት ያስታውሳሉ። በዚህ ወቅት ምስክሩ ከመጋረጃ ጀርባ ሆኖ ሳይሆን በግልጽ ከተከሳሽ፣ ጠበቆች እና ዐቃቤ ሕግ ፊት ሆኖ ምስክርነቱን ይሰጣል።
በአንዳንድ አዋጆች ላይ ከመጋረጃ በስተጀርባ የምስክር ቃል የሚወሰድበት አስራር እንዳለ አቶ ታምራት ይጠቁማሉ። በአንዳንድ አገራትም ለምስክሮች ደህንነት ሲባል ምስክሮች በሌላ ክፍል ውስጥ ሆነው ወይም ማንነታቸውን በሚሸፍን መስታወት ተከልለው ምስክርነት የሚሰጡበት አሰራር እንዳለ ይናገራሉ።
"ወደፊት ጥቃት እንዳይደርስባቸው ሲባል በሚስጥር ምስክርነት የሚሰጡበት ሰርዓት ተግባራዊ ሊደረግ የሚችለው አሳማኝ ምክንያት ሲኖር ብቻ ነው" ይላሉ።
ለዚህም ምክንያታቸው ተከሳሹ ምስክርነት የሚሰጥበትን ሰው ማንነት የማወቅ መብት አለው በማለት ነው።
















