ቤላሩስ፡ ፕሬዚዳንቱን ለማውረድ ተጣምረው እየተፋለሙ ያሉት ሶስቱ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Viktor Babaryko Media Team
በፕሬዚዳንትነት ለመመረጥ በሁሉም ነገር መስዋዕትነት ለመክፈል የቆረጡ ሦስት ሴቶችን እናስተዋውቃችሁ።
ስቬትላና ቲካኖቭስካያ፣ ቬሮኒካ ትሴፕካሎ እና ማሪያ ኮሌስኒኮቫ የተባሉት የቤላሩስ ሴቶች በመጣመር ታሪክ ለመስራት እየጣሩ ነው።
በሚቀጥለው ወር በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም ለማሸነፍ ቆርጠው ተነስተዋል።
የእነሱ ዘመቻም ከተሳካ ስቬትላና ቲካኖቭስካያ ቀጣይዋ ፕሬዚዳንት ትሆናለች።
ስቬትላና ቲካኖቭስካያ የባለቤቷንም ዘመቻ በማስቀጠልም ስፍራውንም ወስዳለች። ባለቤቷ ሰርጌይ ቲካኖቭስካያ ፖለቲከኛና ፀሐፊ ሲሆን ለእስር ተዳርጎ ነበር፤ ለምርጫም ሆነ በፕሬዚዳንትነት እንዳይወዳደር ተከልክሏል።
እሷም ብትሆን ከፕሬዚዳንትነት ምርጫ ዘመቻው እንድትታቀብና ልጆቿን ይዛ ወደሌላ አገር እንድትሄድ የአገሪቱ ባለስልጣናት ቢያስፈራሯትም እሷ ግን ከቁብ የቆጠረችው አትመስልም። በእምቢተኝነቷ በመቀጠልም ለመወዳደር ወስናለች።
የስቬትላና ባለቤት ብቻ ሳይሆን የቬሮኒካ ትሴፕካሎ ባለቤትም እንዲሁ በፕሬዚዳንትነት ምርጫ እንዳይሳተፍ እግድ ተጥሎበታል።
ማሪያ ኮሎስኒኮቫ ደግሞ በእስር ላይ ያለው ፖለቲከኛና እጩ ተወዳዳሪ ቪክቶር ባባርይኮ ቃለ አቀባይ ናት።
ተልዕኳቸው ምንድነው ብትሉ? ነሐሴ 3/2012 ዓ.ም በሚደረገው ምርጫ ማሸነፍና፤ በዚህም ለ26 ዓመታት ያህል በስልጣን ላይ የቆየቱን የፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮን የስልጣን ማብቂያን ማብሰር ነው።
'ሚስቶች፣ እናቶችና የቤት አስተዳዳሪዎች'
የሦስቱን ሴቶች ጅማሮ አዲስና አስደናቂ የሚያደርገው ዋናው ነገር በወንዶች በከፍተኛ የበላይነት በተያዘው የቤላሩስ ፖለቲካ ውስጥ ሰብረው ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት እንደሆነ የቢቢሲ ሞኒተሪንግ ተንታኝ የሆኑት ያና ልዩሽኔቭስካያ ያስረዳሉ።
ለሦስት አስርታት ያህል በስልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር በተደጋጋሚም በቤላሩስ የሴቶች ሚና "ሚስትነት፣ እናትነትና የቤተሰብ አስተዳዳሪነት" ብቻ ነው በማለት የበላይነት መልዕክትን ሲያስተላልፉም ተሰምተዋል።
በጎርጎሳውያኑ 1994 መንበረ ስልጣኑን የተቆጣጠሩት ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ለስድስተኛ ጊዜም ለመመረጥ አኮብኩበዋል። የቤላሩስ ዜጎች "ሴቶችን ለመምረጥ ዝግጁ አይደሉም"፣ "ሕገ መንግሥቱ ለሴቶች አይደለም" እያሉም እየቀሰቀሱ ነው።
ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ ለአስርት ዓመታት የመሩትን ሕዝብ የሚያውቁት አይመስልም ምክንያቱም ይህ አስተያየታቸው በበርካቶች ዘንድ ውግዘት እንዲደርስባቸው አድርጓቸዋል።
በኋላም ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን ለማረም በሚመስል መልኩ "ፆተኛ ለመሆንና የሴቶችን ክብር ዝቅ ለማድረግ" ያለመ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
"ሕገ መንግሥታችን የተፃፈበት መንገድ ለወንድም ቢሆን ሸክሙ ከባድ ነው። እዚህ ቦታ ላይ ሴትን ብናስቀምጣት፤ ከብዷት ትወድቃለች፤ ምስኪን" በማለት ፕሬዚዳንቱ ለማብራራት ሞክረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለቤላሩስ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ይሆን?
ስቬትላና ቲካኖቭስካያ፣ ቬሮኒካ ትሴፕካሎ፣ ማሪያ ኮሌስኒኮቫ በጥምረት የሚያደርጓቸው የምረጡኝ ቅስቀሳዎች በቤላሩስ በታሪክ ሰሪነት እንዲመዘገቡ አድርጓቸዋል።
ሦስቱ ሴቶች ዘመቻቸውን ሲያካሂዱ የተነሱዋቸው ፎቶዎችም ፕሬዚዳንት አሌክሳንደርን የሚፋለም አዲስ መንፈስ ምልክትም ተደርጎ እየተወሰደ መሆኑንም ተንታኝዋ ያና ይናገራሉ።
ምንም እንኳን በጥምረት መምጣታቸው እንደ መጤ ቢያስቆጥራቸውም፤ የሦስቱንም ህይወት በምናጤንበት ወቅት ለዓመታት ያህል በፖለቲካው ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸውና በተለያዩ ተቋማትም ያገለገሉ ናቸው።
"ባለቤቴ ሰርጌይ ቲካኖቭስካያ ሕዝቡን ወደ አንድ ማምጣት ችሎ ነበር እኛም ሕዝባችንን በማስተባበር አንድነትን መፍጠር ዋና አላማችን ነው" በማለት ስቬትላና የመጀመሪያ የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ተናግራለች።
ሰርጌይ ታዋቂ ፀሐፊና ፖለቲከኛ ሲሆን ከፍተኛ ሁከት በማነሳሳት ለእስር ተዳርጓል፤ በፕሬዚዳንትነት እንዳይወዳደርም እገዳ ተጥሎበታል።
ስቬትላና ፍትሃዊና ሚዛናዊ ምርጫ ተደርጎ ካሸነፈችም ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ ቃል የገባች ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ የፕሬዚዳንት ስልጣንና የስልጣን ዘመኑን የሚገድብ ሕገ መንግሥታዊ ለውጥ አመጣለሁ ብላለች።
የወደፊቱ ተስፋ
ቬሮኒካ ትሴፕካሎም በስቬትላና ሃሳብ ትስማማለች።
የእሷም ባለቤት ቫለሪ ትሴፕካሎ በአሜሪካ አምባሳደርነት አገልግሏል፤ በአንድ ወቅትም በፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ቀንደኛ ጠላት ተደርጎ ነበር።
በቤላሩስ ማዕከላዊ የምርጫ ኮሚሽንም ለፕሬዚንዳንትነት አይመጥኑም ተብለው ከተገለሉ ዘጠኝ እጩዎችም አንዱ ነው።
ሚንስክ በተባለችው ከተማም ቬሮኒካ ባደረገችው የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደርን የሕዝቡን ቁጥር በመቀነስ ወንጅላቸዋለች።
"ወጣቱ ክፍል አንዳንዴም መላው ቤተሰብ ለተሻለ ህይወት እየተሰደደ ነው። ቤላሩስ ነፃነታቸውን ስለገፈፋቻቸው ነው መሸሽን የመረጡት" ብላለች።
"የመናገር ነፃነት፣ የተሻለ ገቢ፣ ከዚህም በላይ ተስፋን ቤላሩሳውያን ቢፈልጉትም የላቸውም። እነዚህን ሁኔታዎች መቀየር እንፈልጋለን" በማለት ቬሮኒካ ትናገራለች።
የማሪያ ኮሌስኒኮቫ ልምድ ከእነሱ ትንሽ ለየት ይላል።
የፕሬዚዳንትነት እጩ ለነበረው ቪክቶር ባባርያኮ ቃለ አቀባይ ነበረች። በባንኩ ዘርፍ ስመ ጥር ሲሆን የፕሬዚዳንቱም ቀንደኛ ተፎካካሪ ነበር።
እጩው ፕሬዚዳንት ገንዘብ በመመዝበርና በማጭበርበር ለእስር የተዳረገ ሲሆን ከውድድሩም እንዲወጣ ተገዷል።
ይህንንም ተከትሎ ነው ማሪያ በሴቶች ብቻ የሚመራውን ዘመቻ የተቀላቀለችው።
የቪክቶር ከምርጫው መወገድን ተከትሎ የአውሮፓ ሕብረት መልዕክተኞች የምርጫ ኮሚሽኑ ውሳኔ የአገሪቱን የዲሞክራሲ ሂደትን የሚቀለብስና ምርጫውንም ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው በማለት አስጠንቅቀዋል።
ሦስቱ ሴቶች ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ ሲሆን ሁሉም ቢሆን ቁልፍ በሚባሉት ፖሊሲዎች፣ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች፣ ፀረ-ሙስናና የንግግር ነፃነትን በተመለከተ ተመሳሳይ አቋም አላቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከባድ ፈተና
የቢቢሲ ሞኒተሪንግ ባልደረባ ያና ልዩሽኔቭስካያ እንደሚሉት የሦስቱ ሴቶች ጥምረት ፖለቲካው ላይ የነበረውን ድባብ በመለወጥ በርካቶች እንዲነሳሱ አድርጓል።
በአስርት ዓመታት ውስጥ በነበረው የምርጫ ማጭበርበርና ለውጥ አያመጣምም በሚል በርካታው ሕዝብ ተሰላችቶ ነበር።
"ይህ የጨለምተኝነት ስሜት የመጣው ዝም ብሎ አይደለም አገሪቱ ስታካሂደው በነበረው ኢ-ዲሞክራሲያዊ የምርጫ ውጤት ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዚዳንቱ በተቀናቃኞቻቸው ላይ የሚያደርጉት ጫና ነው" ትላለች ያና።
ከዚህም በተጨማሪ ለዋናው ተፎካካሪ ፓርቲም የሴቶቹ አንድ ላይ መምጣት እንደ አደጋም መታየቱን ያና ያስረዳሉ።
የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን የሦስቱ ሴቶች ጥምረት በቤላሩስ ፖለቲካ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ አንድነትን ማምጣት ችሏል።
ፕሬዚዳንት አሌክሳንደርም በበላይነት አሸንፍበታለሁ ብለው እንዳሰቡት ምርጫም እንዳልሆነም እየታየ ነው።












