ማሌዢያ፡ ዝንጀሮዎች የተማሪውን ስልክ ሰርቀው ፎቶ ተነስተው መለሱለት

በተማሪው ተንቀሳቃሽ ስልክ ዝንጀሮዎቹ የተነሱት ምስል

የፎቶው ባለመብት, ZACKRYDZ RODZI

ታሪኩ ትንሽ አስገራሚ ነው፡፡ ማሊዤያዊ ውስጥ ነው የሆነው፡፡ አንድ ተማሪ ስልኩ ተሰረቀ፡፡

መሰረቁ ግን አልተዋጠለትም፡፡ ምክንያቱም ቅዳሜ ከቤት አልወጣም፡፡ ቅዳሜ ስልኩን ይዞት ነበር፡፡ ቤት ውስጥ ደግሞ እሱ አባቱና አጎቱ ናቸው የሚኖሩት፡፡ አባትና አጎቱ ደግሞ ስልክ አይሰርቁም፡፡

ስልኩን ማን ሰረቀው?

ሶፋ ሥር ቢፈለግ፣ ሱሪ ኪሶች ውስጥ፤ ላፕቶፕ ቦርሳ ውስጥ…ህምጥ ይግባ ስምጥ አልታወቀም፡፡ የተማሪው ስልክ ጠፋ ጠፋ፡፡ በኋላ ስልኩ ተገኘ፡፡ ማን ሰረቀው፡፡ አሁንስ ከየት ተገኘ፤ ግራ ገባው፡፡

ቅዳሜ የተሰረቀ ስልክ እሁድ ከሰዓት ተገኘ፡፡ አጎትየው ሲቀልድ ‹‹እስኪ የፎቶ አልበሙን ክፈተው፤ ሌባው ምናልባት ፎቶ ተነስቶ ልኮልህ ይሆናል›› ብሎ አሾፈበት፡፡ አብረው ሳቁ፡፡ ወጣቱ ተማሪ ግን እንደ ቀልድ የተባለውን አደረገ፤ ያገኘው ነገር አስደነገጠው፡፡

ዝንጀሮዎች ፈገግ እያሉ ሰልፊ (ምሥለ ራስ) ተነስተው አስቀምጠውለታል፡፡ ለዚያም በርከት ያሉ ፎቶዎችን አገኘ፡፡ በስልኩ ፎቶ ሲንበሻበሹበት ነበር ለካ፡፡

ፎቶ ብቻ አይደለም ታዲያ፤ ቪዲዮ አልቀራቸውም፡፡ስልኩ አንድ ቀን ከጠፋ በኋላ ነው በሚቀጥለው ቀን የተመለሰለት፡፡

እርግጥ ማሌዢያዊው ተማሪ ሮድዚ መኖርያ ቤቱ ጫካ አጠገብ ነው፡፡ ሆኖም ዝንጀሮዎች እቃ ሰርቀው አያውቁም፡፡

በተማሪው ተንቀሳቃሽ ስልክ ዝንጀሮዎቹ የተነሱት ምስል

የፎቶው ባለመብት, ZACKRYDZ RODZI

ለምን ስልኩን ፈለጉት?

በአንደኛው ቪዲዮ ላይ አንደኛው ዝንጀሮው ስልኩን ለመብላት ሲሞክር ይታያል፡፡

ተማሪው ይህንን ቪዲዮ በትዊተር ሰሌዳው ካጋራ በኋላ ነው የሮድዚ ታሪክ ዓለምን ጉድ ያሰኘው፡፡ ማሌዢያዊው ተማሪ ስልኩ እንዴት እንደተሰረቀ፣ መቼ ተሰረቀ፣ ለምን ተሰረቀ ግራ ገብቶት ለ24 ሰዓት ያህል ሲደነቅ እንደቆየ ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡ ምክንያቱም ያን ቀን ከቤት አልወጣም፡፡ ከቤት ውጭ እንዳልተሰረቀ ደግሞ ያውቃል፡፡

ይህ ታሪክ የተፈጸመበት ማሌዢያውው ተማሪ ገና 20 ዓመቱ ነው፡፡

‹‹ቅዳሜ ለታ ማልጄ 11፡00 ሰዓት ነበር የተነሳሁት፤ ያን ጊዜ ስልኬን አጣሁት፡፡ ብሏል ለቢቢሲ፡፡ ‹‹ቤታችን ውስጥ ምንም ነገር አልተሰረቀም፡፡ ሌላ ሰው እንዳልገባ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ታዲያ ስልኬ የት ሄደ፤ ይሄ የሆነ ዓይነት ድግምት መሆን አለበት አልኩ ለራሴ›› ይላል በወቅቱ የተፈጠረበትን ሁኔታ ሲያስረዳ፡፡

ተማሪው በኋላ ላይ ስልኩን ያገኘው እሑድ ከሰዓት ላይ ነበር፡፡ ስልኩም ቤቱ ደጅ ላይ ከሚገኘው ጫካ ተቀምጦለት ነው በክብር ያገኘው፡፡

በተማሪው ተንቀሳቃሽ ስልክ ዝንጀሮዎቹ የተነሱት ምስል

የፎቶው ባለመብት, Zackrydz Rodzi

‹‹ስልኬ ላይ ስደውል ድምጹን ቤታችን ደጅ ላይ ሰማሁት፤ ከቴምር ዛፍ ስር፣ በቅጠል ተሸፍኖ አገኘሁት›› ይላል፡፡

ቢቢሲ በኋላ ላይ ማረጋገጥ እንደቻለው ጠፍቶ በተገኘው ስልኩ ዝንጀሮዎች ፎቶ ሲነሱበት ቆይተዋል፡፡ ጫካ ውስጥ ወፎች ሲበሩ፣ ቅጠል ሲንኮሻኮሽ ዝንጀሮዎች ፎቶ ሲነሱ በተለያየ ምሥሎች ተደግፎ ይገኛል፡፡ አነሳሳቸውም ጥሩ የሚባል ነው፡፡

‹‹እስከዛሬ ዝንጀሮዎች ከቤታችን እቃ ሰርቀው አያውቁም ነበር ይላል፡፡›› ይላል ተማሪው፡፡

ለምን ቅዳሜ ለታ ሰረቁት? ምናልባት የማይቀርበት ሰርግ ኖሮባቸው ካሜራው በጣም አስፈልጓቸው ይሆን? ማን ያውቃል!