በ'ሰልፊ' ምክንያት ሳይጀመር የተቋጨው ትዳር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሕንድ አዲስ ሙሽሮች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ሰልፊ ሲነሱ ውሃ ውስጥ ገብተው መሞታቸው ተሰማ።
ከሞቱት መካከል ሙሽሪት እና ሶስት ቤተሰቦቿ እንደሚገኙበት የምዕራብ ኢንዲያና ግዛት ፖሊስ አስታወቋል።
ስድስት ሰዎች እጅ ለእጅ ተያይዘው በግድቡ ዳርቻ ፎቶ እየተነሱ ሳለ አንዳቸው በመንሸራተታቸውና ቀሪዎቹን ይዘው ወደ ግድቡ መውደቃቸውን የፖሊስ ሪፖርት ያሳያል።
የሙሽሪት ባል እህቱን ማዳን የቻለ ሲሆን ሌሎቹ ግን መትረፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ሕንድ ሰልፊ ሲነሱ በሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ቀዳሚውን ተርታ ይዛለች።
ከጎርጎሳውያኑ ከ2011 እስከ 2017 ሰልፊ ሲነሱ ከሞቱ ሰዎች መካከል 259ኙ በሕንድ ሲሆን፤ ሩሲያ፣ አሜሪካና ፓኪስታን በተከታይነት ይገኛሉ።
አዲሶቹ ሙሽሮች እሁድ ዕለት ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ እህቶቻቸውን ወንድሞቻቸውን ይዘው ወደ ቤተሰቦቻቸው ዘንድ እየሄዱ ነበር።
በዚህ መካከል ውሃው ወዳለበት ፎቶ ለመነሳት ይቆማሉ። አንድ የ14 ዓመት ልጅ ግን አዳልጦት ሊወድቅ ሲል የያዛቸውን ላለመልቀቅ ሲውተረተር ሁለት ዕድሜያቸው 18ና 19 የሆነ እህቶቹን፣ ሙሽሪትን እና የሙሽሪትን እህት ይዞ ውሃ ውስጥ ይወድቃል ።
ልጁ ግን መትረፍ አልቻለም። አዳልጦት ውሃ ውስጥ ወደቀ። ወዲያው ሙሽራው እህቱን ለማውጣት ቢችልም አራቱ ግን የገቡበት ሰምጠው ቀርተዋል። ፖሊስ እንዳስታወቀው በኋላ ላይ አስክሬናቸው ወጥቷል።
በግንቦት ወር በሐራያና ግዛት ሶስት ታዳጊዎች በባቡር መንገድ ላይ ሰልፊ ሲነሱ ከሚመጣ ባቡር ለማምለጥ ዘልለው በሌላ የባቡር መስመር ላይ በመግባታቸው ከሌላ አቅጣጫ በመጣ ባቡር ተገጭተው ሕይወታቸው አልፏል።
እአአ በ2017 አራት ተማሪዎች ሰልፊ ሲነሱ ከሞቱ በኋላ በአንድ ግዛት አነሳሽነት " ሰልፊ ይገላል" የሚል ዘመቻ ተጀምሮ ነበር።
በተመሳሳይ ዓመት ከዝሆን ጋር ሰልፊ ለመነሳት የሞከረ ግለሰብ ዙሆኑ በኩንቢው ጠቅልሎ በማፈን ገሎታል።















