"ሰልፊ" ፎቶ እና የሞራል መላሸቅ

የራሱን ምስል በባቡር ከተገጨች ሴት ጋር ለማንሳት የሚጣጣር ወጣት

የፎቶው ባለመብት, ANSA/GIORGIO LAMBRI/QUOTIDIANO LIBERTA

አፍቅሮተ-ራስ ጣሪያ የነካበት ዘመን ላይ ሳንሆን አንቀርም።

ሰዎች የሌሎችን ትኩረት ለማግኘት ብዙ ርቀት ይጓዛሉ።

በሞት አፋፍ ላይ ያለን ሰው ከመርዳት ይልቅ የራሳቸውን ምስል ለማስቀረት የሚሟሟቱ ምን ተብለው ይጠራሉ?

ጣሊያን ውስጥ አንድ ወጣት በዚህ ድርጊቱ ቁጣን ቀስቅሷል።

በባቡር ተገጭታ በሞት አፋፍ ላይ ትገኝ ከነበረች ካናዳዊት ጎን በመቆም የራሱን ምስል ሲቀርጽ ድርጊቱ በሌላ ፎቶግራፈር እጅ ከፍንጅ ተይዟል።

በራስ ምስል አፍቅሮት የሰከረው ይህ ወጣት የሞራል ልዕልናችን መላሸቅ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

ይኸው ጎረምሳ በባቡር ተገጭታ ክፉኛ ከተጎዳች ሴት ጎን ፎቶ ሲነሳ ፎቶ ያነሳው አንድ የዜና ወኪል ባልደረባ ሲሆን "ሥነ ምግባር እያጣን ነው" ሲል በክስተቱ ማፈሩን ተናግሯል።

ፖሊስ የራስ ምስል ወሳጁን ወጣት በቁጥጥር ሥር አውሎ ፎቶዎቹን ከስልኩ እንዲሰርዛቸው አስገድዶታል። ይህ ብቻም ሳይሆን ምርመራም ጀምሮበት ነበር። ነገሩ የሞራል እንጂ የሕግ ጉዳይ ባለመሆኑ ግን ምርመራው ተቋርጧል።

ካናዳዊቷ ሴት ከአደጋው በኋላ ወደ ሆስፒታል ብትወሰድም አንድ እግሯን አጥታለች።

ምናልባት በአግባቡ ካልተዘጋ የባቡር በር አፈትልካ ወጥታ አደጋ እንደደረሰባት ተገምቷል።

ፓይሴንዛ በተባለ ባቡር ጣቢያ የመሳፈሪያ ወለል ላይ ሆኖ የራሱን ምስል እየወሰደ የነበረው ይህ ወጣት ድርጊቱን ሲፈጽም የሚያሳየው ምስል በጣሊያን ሚዲያ በመበተኑና ድርጊቱም በመገናኛ ብዙኃን መናኘቱ በሞራል ጉዳይ አዲስ የውይይት በር ከፍቷል።

የሚደንቀው ግለሰቡ ከተጎጂዋ በቅርብ ርቀት ሆኖ የራሱን ምስል ሲወስድ የእናሸንፋለን ምልክት ወይም "V" በማሳየትና በቅንጦት ኾኖ ነበር።

ላ ስታምፓ የተባለው የጣሊያን ዕለታዊ ጋዜጣ በአስተያየት ገጹ ስለጉዳዩ በታተመ አንድ ጽሑፍ ግለሰቡን ክፉኛ ወርፎታል።

"ይህ ወጣት መጥፎ ሰው አይደለም፤ ምክንያቱም የልቡን ባልቦላ አጥፍቶታል፤ የኢንተርኔት ባሪያ ነው። አትፍረዱበት" ሲል አንድ አምደኛ በጋዜጣው ላይ ጽፏል።

ኒኮላ ሳቪኖ የተባለ የሬዲዮ አሰናጅ በበኩሉ "ሰብአዊነት በፍጥነት አየተሸረሸረ ስለሆነ የሰው ዘር መጥፊያ የደረሰ ይመስለኛል።" ብሏል።

ሌላ የትዊተር ተጠቃሚ በገጹ ላይ "ከእንግዲህ ምንም ነገር እየረገመኝ አይደለም" ሲል በሰው ልጅ ላይ እየታየ ያለው የሞራል ዝቅጠት እንዳሳሰበው በተመጠነ ቋንቋ ስሜቱን አንጸባርቋል።