ጣሊያን፡ ለ7ኛ ጊዜ ከእስር ቤት ያመለጠው ነፍሰ ገዳይ የከብት ጋጣ ውስጥ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, STATE POLICE
በጣሊያን ውስጥ 7 ጊዜ ከእስር አምልጧል፡፡ በመጨረሻ በበጎች ጋጣ ውስጥ ተሸሽጎ ተገኝቷል፡፡ ጁሴፔ ማስቲኒ ይባላል፡፡
በዋና ስሙ የሚያውቀው ግን ብዙም ሰው የለም፡፡ ቅጸል ስሙ ዝነኛ ነው፡፡ ጆኒ ዘ ጂብሲ ይባላል፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ ከእስር ቤት ሲያመልጥ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት ሳርዲኒያ እስር ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ሴፕቴምበር 6 ነው ከዚህ እስር ቤት ባልታወቀ ሁኔታ ያመለጠው፡፡
በስንትና ስንት አሰሳ በሰሜን ምዕራብ ትንሽ ከተማ ሳሳሪ ውስጥ በከብቶች ጋጣ ውስጥ ቁጢጥ ብሎ ተገኝቷል፡፡ ጆኒ ዘ ጂፕሲ ለመጀመርያ ጊዜ ከእስር ቤት ያመለጠው በ1987 (እንደ ፈረንጆቹ) ገና በ11 ዓመቱ ነበር፡፡
ያን ጊዜ ገና ለመጀመርያ ጊዜ ነበር ከእስር ያመለጠው፡፡ ፖሊስ ለ2 ዓመታት ድረስ ሲያፈላልገው ቆይቶ በመጨረሻም አግኝቶታል፡፡
ከእስር ቤት አምልጦ 2 ዓመታት ሙሉ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም፡፡ በ2ቱ ዓመታት ውስጥ አንድ ፖሊስ ገድሏል፣ አንዲት ሴት ልጅ አግቷል፡፡ በርካታ ማጅራቶችን መቷል፡፡
ማክሰኞ ዕለት በከብቶች ጋጣ ውስጥ ሲያዝ ከሳሳሪ፣ ከቻገሊያሪ እና ከሮም የተውጣጡ ፖሊሶች በቅንጅት ሰርተዋል፡፡ ጆኒ ዘ ጂፕሲ ማንነቱ እንዳይታወቅ ጸጉሩን ቀለም ቀብቶት ነበር ብሏል ፖሊስ፡፡
ጆኒ በዚህን ጊዜ ከእስር ቤት ያመለጠው ፍቅር ይዞት ነው ቢባልም ዝርዝሩ አልታወቀም፡፡ ይህ ነፍሰ ገዳይ በቁጥጥር ሥር ሲውል መሣሪያ አልታጠቀም ነበር፡፡ ከፖሊሶችም ጋር ግብግብ አልፈጠረም፡፡ ሲደረስበት በሰላም እጁን ሰጥቷል፡፡
የከብቶቹ ጋጣ ባለቤት የ51 ዓመቱ ወርቅና ብር ሰሪ ሎሬንዞ ፓኒ ከጆኒ ጋር ወደ እስር ቤት ተወስዷል፡፡ ምክንያቱም እውቅ ነፍሰ ገዳይ በጋጣህ ውስጥ ደብቀሀል በሚል ተከሶ ነው፡፡
ጆኒ ዘ ጂፕሲ በሰሜን ጣሊያን ጥብቅ ጥበቃ ከሚደረግላቸው እስር ቤቶች ሳይቀር በተደጋጋሚ ማምለጡ ይነገርለታል፡፡












