ሊባኖስ፡ በቤሩት ወደብ አቅራቢያ በሚገኝ መገበያያ እሳት ተነሳ

የመገበያያው ዲዛይን የተሠራው በእንግሊዛዊ ኢራቃዊ አርክቴክት ዛሀ ሀዲድ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP

በሊባኖስ መዲና ቤሩት ወደብ አቅራቢያ ግንባታ ላይ የሚገኝ መገበያያ ውስጥ የእሳት አደጋ ተነሳ። ይህ በሳምንት ውስጥ በቤሩት የተከሰተ ሦስተኛ አደጋ ነው።

በመገበያያው ጣሪያ ላይ በከፊል ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ አደጋ ተከላካዮች እሳቱን በአፋጣኝ ማጥፋት ችለዋል።

እስካሁን ጉዳት የደረሰበት ሰው ሪፖርት አልተደረገም። የእሳቱ መንስኤም አልታወቀም።

የመገበያያው ዲዛይን የተሠራው በእንግሊዛዊ ኢራቃዊ አርክቴክት ዛሀ ሀዲድ ነበር። የሚገኘውም ወደብ አቅራቢያ ባለ አንድ የንግድ ማዕከል ነው።

ከስድስት ሳምንታት በፊት በወደቡ በተከሰተው ፍንዳታ ወደ 200 ሰዎች እንደሞቱና 6,000 ሰዎች እንደቆሰሉ ይታወሳል። በአካል ላይ ያስከተለው ጉዳት 4.6 ቢሊዮን ዶላር፤ ምጣኔ ሀብት ላይ የደረሰው ጉዳት ደግሞ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይገመታል።

2,750 ቶን አሞንየም ናይትሬት ፈንድቶ ስለተከሰተው ፍንዳታ አሁንም ምርመራ እየተደረገ ነው።

ባለፈው ሳምንት የተከሰቱ ሁለት እሳት አደጋዎች ነዋሪዎችን አስደንግጠዋል፤ አስቆጥተዋልም። መሪዎች በችላ ባይነትና በሙስናም እየተወቀሱ ነው።

ባለፈው ማክሰኞ መጠነኛ እሳት ተነስቶ በአፋጣኝ ጠፍቷል። ሀሙስ ደግሞ ወደቡ አቅራቢያ በሚገኝ የእርዳታ ቁሳቁስ ማቆያ ውስጥ ከፍተኛ እሳት ተቀስቅሶ ነበር።

ዛሬ ስለተነሳው እሳት የተጠየቀ ጆ ሳይግ የተባለ ግለሰብ “ያሳዝናል፤ ለማመን ይቸግራል። በየቀኑ ችግር ይገጥመናል” ሲል ለሮይተርስ ተናግሯል።

ሊባኖስ የገባችበት ቀውስ መገበያያ ገንዘቧ ዋጋ እንዲያጣ፣ ሥራ አጥነት እንዲጨምር እንዲሁም ድህነት እንዲንሰራፋ ምክንያት ሆኗል።

ከሳምንታት በፊት የተከሰተውን ፍንዳታ ተከትሎ የአገሪቱ አስተዳዳሪዎች ሥራ ለቀዋል። ተተኪው መንግሥት ከምዕራባውኑ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ለውጥ ማምጣት እንዳለበት ጫና እየተደረገ ነው።

ጆ ሳይግ የተባለው ግለሰብ ግን “ተመሳሳይ ሰዎች ከሆኑ ለውጥ አይመጣም” ብሏል።