ቤይሩት፡ በሊባኖስ የሰብዓዊ ቀውስ እንደሚያጋጥም የተባበሩት መንግሥታት አስጠነቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ድርጅቶች በሊባኖስ ወደብ የተከሰተውን ፍንዳታ ተከትሎ የምግብ አቅርቦት ሊቋረጥ እንደሚችልና የምግብ ፍጆታም ዋጋው ሊንር እንደሚችል በመግለፅ፤ የሰብዓዊ ቀውስ እንደሚያጋጥም አስጠነቀቁ።
በጀኔቫ የዓለም ምግብ ድርጅት ቃል አቀባይ እንዳሉት ሊባኖስ 85 በመቶ የሚሆነውን የምግብ ፍጆታዋን የምታገኘው ከውጭ በማስገባት ነው።
በመሆኑም ድርጅቱ 5 ሺህ እሽግ የምግብ ፍጆታዎች ወደ ሊባኖስ እየላከ ሲሆን እያንዳንዱ እሽግ አምስት አባላት ላሉት ቤተሰብ ለአንድ ወር እንዲበቃ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ሊባኖስ ደካማ የጤና ሥርዓት እንደነበራት የጠቀሰው የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ አሁን በተከሰተው ፍንዳታ ሦስት ሆስፒታሎች መውደማቸውን ገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ ድርጅቱ ከፍተኛ ጉዳትና ቃጠሎ ያጋጠማቸውን ሰዎች ለመርዳት የሚያስችል 1 ሺህ የህክምና ቁሳቁስ (ትራውማ ኪት) እየላከ መሆኑን ገልጿል።
ሆኖም ሊባኖስ የኮቪድ-19ን ወረርሽኝ ለመዋጋት ተብሎ በቤይሩት በሚገኘው የዓለም ጤና ድርጅት መጋዘን የተቀመጠ 17 ኮንቴይነር የበሽታ መከላከያ የህክምና መሳሪያዎች በፍንዳታው ሳቢያ ወድሟል።
ይህም የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ወደ ኋላ እንደሚጎትተው ተነግሯል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት የስደተኛ ድርጅት - ዩኤንኤችሲአር ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ ለመስራት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ድጋፍ እያደረገ ነው።
የኤጀንሲው ቃል አቀባይ በአገሪቷ በርካታ ሊባኖሳዊያንና ስደተኞችን ለከፋ ድህነት በዳረገው የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ድጋፍ ከሚሹ ስደተኞች የሶሪያ ስደተኞች ይበልጥ ተጋላጭ እንደነበሩ አስታውሰው፤ አሁን ያጋጠመው ፍንዳታ ደግሞ ሁኔታውን 'በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ' አድርጎታል ሲሉ አሳስበዋል።
በከተማዋ ላይ ባጋጠመው ከባድ ፍንዳታ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል።
ፕሬዝዳንት ማይክል አኑን ፍንዳታው ባገጠመበት ቦታ ላይ 2 ሺህ 750 ቶን የሚመዝን አልሙኒየም ናይትሬት ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ለስድስት ዓመታት ተከማችቶ ነበር ማለታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ ከትናንት በስቲያ አስቸኳይ የካቢኔ ሰብሰባ ጠርተው ለሁለት ሳምንታት የሚዘልቅም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።
ሊባኖስ ለሦስት ቀናትም የብሔራዊ የሃዘን ቀን አውጃለች። ከዚህ በተጨማሪ ፕሬዝደንቱ 66 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ እንዲመደብ ማዘዛቸው ተነግሯል።












