ሊባኖስ ፡ በቤይሩት ወደብ ላይ ከባድ የእሳት አደጋ አጋጠመ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ከአንድ ወር በፊት በተከሰተ ከባድ ፍንዳታ ቢያንስ 190 ሰዎች በሞቱባት በሊባኖሷ ዋና ከተማ ቤይሩት በሚገኘው ወደብ ላይ ከባድ የእሳት ቃጠሎ ተነሳ።
እሳቱ የተቀሰቀሰው በወደቡ የቀረጥ ነጻ ክልል ውስጥ በሚገኝ ዘይትና ጎማ በተከማቸበት መጋዘን ላይ ሲሆን፤ ባለስልጣናት የእሳት አደጋውን በዚያው ቦታ ላይ ለመቆጣጠር ተችሏል ብለዋል።
እስካሁን በእሳቱ ሳቢያ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ የተነገረ ሲሆን፤ የአደጋው መነሻ አልታወቀም። በከቃጠሎው የሚወጣው ጥቁር ጭስም በከተማዋ ሰማይ ላይ ይታያል።
የእሳት አደጋ ሠራተኞች በአደጋው ቦታ እሳቱን ለመቆጣጠር እየጣሩ ሲሆን የአገሪቱ ሠራዊትም ሄሊኮፕተሮችን በመጠቀም እሳቱን ለማጥፋት እየጣረ መሆኑን አመልክቷል።
የሊባኖስ ቀይ መስቀል ኃላፊ ጆርጅ ካታኒሐ እንዳሉት በአደጋው ምክንያት አንዳንድ ሰዎች ለመተንፈስ የመቸገር ሁኔታ እንዳጋጠቸው ቢገልጹም ይፋ የሆነ ጉዳት ግን እስካሁን እንዳልደረሰ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ኃላፊ ጨምረውም ባለፈው ጊዜ እንዳጋጠመው በእሳቱ የተነሳ ፍንዳታ ሊያጋጥም ይችላል የሚል ስጋት እንደሌለ ተናግረዋል። ቢሆንም ግን በአደጋው ሳቢያ አንዳንድ ነዋሪዎች ፍርሃት እንደተፈጠረባቸው ገልጸዋል።
ያለፈው ወር ፍንዳታ የተከሰተው በወደቡ ላይ ተከማችቶ የነበረ 2,750 ቶን የሚሆን አሞኒየም ናይትሬት የተባለ ኬሚካል በእሳት ተያይዞ ሲሆን በአደጋውም ሳቢያ በአገሪቱ ከባድ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራቸውን ለመልቅ ተገደው ነበር።
በኬሚካሉ ፍንዳታ ሳቢያ በከተማዋ ላይ ከባድ ውድመት የደረሰ ሲሆን በርካታ ቤቶችና ሕንጻዎች ፈራርሰዋል።
በዚህም ምክንያት ከሞቱት ከ190 በላይ ሰዎች በተጨማሪ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመቁሰል አደጋ ሲደርስባቸው 300 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቤት አልባ ሆነዋል።
















