እስራኤል በሂዝቦላህ "የተቃጣብኝን ጥቃት መከትኩ" አለች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከሰሞኑ በአገሬው ተቃውሞ የበረታባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ 'ጽንፈኛው' ሂዝቦላህ በድንበር በኩል ጥቃት ቢከፍትም አከርካሪውን ብለን መልሰነዋል' ብለዋል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ አራት የሚሆኑ ሚሊሺያዎች በሰሜን እስራኤል፣ የጎላን ኮረብቶች አቅጣጫ፣ በዶቭ ተራራ በኩል ወደ እስራኤል ክልል ድንበር ጥሰው ሲገቡ አግኝተን መክተናቸዋል ብሏል፡፡
ሂዝቦላህ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ወደዚያ ድንበር ዝርም አላልንም፤ የእስራኤል መከላከያ ተደናግጦ ነው "የሚዘባርቀው" ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ከሰሞኑ አንድ የሂዝቦላህ ከፍተኛ መሪ በእስራኤል የአየር ጥቃት ከተገደለ ወዲህ ይህ ሰሜናዊ እስራኤል ድንበር ከፍተኛ ውጥረት ነግሶበት ቆይቷል፡፡
እስራኤል ባለፈው ሰኞ ነበር ይህን ከፍተኛ የሂዝቦላህ ወታደራዊ መሪ በአየር ጥቃት የገደለችው፡፡ ኾኖም እስራኤል ስለ ጥቃቱ ማረጋገጥም ሆነ ማስተባበል አልፈለገችም፡፡ ነገር ግን ሂዝቦላህ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ እጁን እንዳያነሳ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እንዳለው ትናንት የሂዝቦላህ ጦር ወደ እስራኤል ድንበር ለመሻገር ከሞከረ በኋላ ጠንካራ መከላከል ስለገጠመው እግሬ አውጭኝ ብሎ ፈርጥጧል፡፡
ናታንያሁ በቴሌቪዥን ቀርበው ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር የሒዝቦላህን የድንበር ጥቃት ሙከራ በዋዛ እንደማይመለከቱት አረጋግጠዋል፡፡
ናታንያሁ በዚህ ንግግር ጨምረው እንዳሉት በድንበር አካባቢ ለሚመጣው ጦስ ተጠያቂዎቹ ሂዝቦላህና የሊባኖስ መንግሥት ይሆናሉ፡፡ ሂዝቦላህ 'ከእሳት ጋር እየተጫወተ እንደሆነ ሊያውቀው ይገባል'፡፡
የእስራኤል ሚዲያ የመከላከያ ሰራዊት ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ አንዲት የሂዝቦላህ ጋንታ በድንበር አካባቢ በሚገኝ አንድ የእስራኤል ወታደሮች ካምፕ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ተንቀሳቅሶ ነበር፡፡
እስራኤል ግን ገና ብሉናይል ተብሎ የሚጠራውን ድንበር ከማለፋቸው በፊት ጥቃት ሰንዝራ አስቁማዋለች፡፡ ብሉናይል ድንበር የተባበሩት መንግሥታት የእሰራኤልና የሊባኖስ ድንበር ብሎ የሚያውቀው መስመር ነው፡፡
ሂዝቦላህ በሊባኖስ ፖለቲካ ውስጥ ሁነኛ ሚናን የሚጫወትና በኢራን የሚደገፍ እስከ አፍንጫው የታጠቀ ኃይል ሲሆን በእስራኤል እንደ አሸባሪ ቡድን ይታያል፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚንቀሳቀሰው በደቡብ ሊባኖስ ድንበር አካባቢ ነው፤ ሂዝቦላህ ከሊባኖስ ጦር ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ይሰራል፡፡
ሂዝቦላህ ስለትናንቱ ክስተት ባወጣው መግለጫ ወታደሮቹ ምንም ዓይነት ጥቃት አለማድረሳቸውን፣ በድንበር አካባቢ እስራኤል ተከሰተ የምትለው ነገር ሁሉ ከፍርሃት የመነጨ ፈጠራ መሆኑን ተንትኗል፡፡
ሆኖም በመግለጫው በእስራኤል የአየር ጥቃት ባለፈው ሰኞ የተገደለበትን መሪውን ለመበቀል መዘጋጀቱንና በቀሉም በቅርቡ እንደሚፈጸም ዝቷል፡፡
እስራኤልና ሂዝቦላህ በነፍስ የሚፈላለጉ ባላንጣዎች ሲሆኑ በጎርጎሳውያኑ 2006 ዓ.ም አንድ ወር የፈጀ መራር ጦርነት አድርገው ሂዝቦላህ 8 የእስራኤል ወታደሮችን ገድሎ ሁለቱን ጠልፎ መውሰዱና ያልተጠበቀ ድል ማስመዝገቡ አይዘነጋም፡፡
እስከዛሬም እየቀጠለ ባለው የሂዝቦላህና የእስራኤል ግጭት ከ1ሺህ 191 ሊባኖሳዊያን በላይ የተገደሉ ሲሆን ብዙዎቹ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው፡፡ በእስራኤል በኩል ደግሞ ግጭቱ አንድ መቶ ሃያ አንድ ወታደሮችና 44 ሰላማዊ ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡












