ሊባኖስ፡ በቤይሩት የነፍስ አድን ሰራተኞች "በፍርስራሽ ውስጥ የልብ ምት " መስማታቸውን ገለፁ

በቤይሩት የነፍስ አድን ሰራተኞች በሊባኖስ ዋና ከተማ የደረሰው ከባድ ፍንዳታ አንድ ወር ከሞላው በኋላ በህንጻዎች ፍርስራሽ ውስጥ ህይወት መኖሩ የሚያሳይ ምልክት በመታየቱ ፍለጋ መጀመራቸው ተገለፀ።
ማር ሚካዔል በመባል በሚታወቀው ስፍራ በሚገኘው ህንጻ ፍርስራሽ ውስጥ የልብ ምት ተሰምቷል የሚለው ያልተረጋገጠ ዜና ከተሰማ በኋላ በህይወት ያለን ነገር የሚለይ መሳሪያ ወደ አካባቢው መላኩ ተገልጿል።
ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፍለጋው ምሽት ላይ የተቋረጠ ቢሆንም በጎ ፈቃደኞች ግን በእጃቸው ፍለጋውን መቀጠላቸው ተሰምቷል።
በሊባኖሱ ፍንዳታ 2 ሺህ 750 ቶን አሞኒየም ናይትሬት ሲፈነዳ ከ200 በላይ ሰዎች ሲሞቱ 300 ሺህ ያህል የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቤት አልባ መሆናቸው ተገልጿል።
በከተማዋ ወደብ፣ በርካታ የመኖሪያ ቤቶች የሚገኙበት አቅራብያ፣ በርካታ ለአደጋ የሚያጋልጡ ቁሳቁሶች ያለ ተገቢው ጥንቃቄ ተቀምጠዋል በሚል ተቃውሞ ተነስቶ ነበር።
ተቃዋሚዎችን ማረጋጋት ያልቻለው መንግሥት፣ በከተማዋ በርካታ ምሽቶች ተቃዋሚ ሰልፈኞች ከፖሊስ ጋር ከተጋጩ በኋላ ስልጣኑን ለቅቋል።
በተያያዘ ዜና ከቤሩት የባህር ወደብ ውጪ በሚገኝ ስፍራ ሐሙስ እለት አራት ኮንቴይነር (ማከማቻ) ውስጥ የተቀመጠ 4.3 ቶን አሞኒየም ናይትሬት መገኘቱን የወታደራዊ ኃይሉ አስታውቋል።
ባለሙያዎች ኮንቴይነሮቹን (ማከማቻዎቻቸውን) መመርመራቸው የተገለፀ ቢሆንም ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።

ሐሙስ እለት በአንድ በፈራረሰ ህንጻ አካባቢ የተሰባሰቡ ከቺሊ የመጡ የህይወት አድን ሰራተኞች ፍለጋ ሲጀምሩ በርካቶች የሚፈጠረውን ተዓምር ለማየት ተሰባስበው ነበር።
በፍርስራሹ ውስጥ በህይወት ያለ ሰው መኖር አለመኖሩ አሁንም አልተረጋገጠም።
የነፍስ አድን ሰራተኞች ፍርስራሹን የሚያነሳላቸው ክሬን ማግኘት ስላልቻሉ እንዲሁም ህንጻው ሊደረመስ ይችላል የሚል ስጋት በመፈጠሩ ምሽት ላይ ፍላጋቸውን አቋርጠዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ግን በእጃቸው ፍለጋቸውን ለማካሄድ ቆርጠው እየፈለጉ የነበረ ሲሆን ግለሰቦች ክሬን በማምጣት ፍለጋው እንዲቀጥል መደረጉን በአካባቢው ያለ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ተመልክቷል።
ከዚህ በኋላም ከቺሊ የመጡ የነፍስ አድን ሰራተኞችም ወደ ስፍራው መመለሳቸው ታውቋል።
ረቡዕ እለት በፍርስራሹ አጠገብ አነፍናፊ ውሻ ይዘው የሚያልፉ የነፍስ አድን ሰራተኞች፣ ውሻው በህይወት ያለ ሰው መኖሩን ምልክት እንደሰጣቸው ተናግረዋል።
ሐሙስ እለት በድጋሜ ውሻው በተመሳሳይ ስፍራ በህይወት ያለ ሰው መኖሩን ምልክት ሰጥቷል። ቡድኑ ፍለጋውን ለማካሄድ የልብ ምት ወይንም ትንፋሽ መኖሩን ለማረጋገጥ ስካነር (መመርመሪያ) ከተጠቀመ በኋላ ፍርስራሹን ለማንሳት መሳሪያዎችን ይዞ መጥቷል።

የነፍስ አድን ሰራተኞቹ በሰባት ቡድን በመከፋፈል ህንጻው ዳግም እንዳይደረመስ በመስጋት ፍርስራሹን አንድ በአንድ ማንሳት ጀምረዋል። በስፍራው የነበረው የቢቢሲ ጋዜጠኛ እንደተመለከተው በህይወት ያለ ሰው ለመፈለግ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግም ምንም ምላሽ የሚሰጥ አካል የለም።
የቀይ መስቀል ባልደረቦች፣ የመከላከያ ኃይሉ፣ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እንዲሁም የበጎ ፈቃደኛ ሰራተኞች በስፍራው ተገኝተዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ

የቺሊ የነፍስ አድን ሰራተኞች ሊባኖስ የደረሱት ከሶስት ቀን በፊት ነው። እንደ መረጃ ምንጮች ከሆነ ፍርስራሽ ውስጥ 15 ሜትር ድረስ ጠልቆ ትንፋሽን የሚያደምጥ መሳሪያ ይዘው መጥተዋል።
እስካሁን ድረስ በፍርስራሹ ውስጥ በህይወት ያለ ሰው መኖሩ አልተረጋገጠም። ነገር ግን በስፍራው የተሰባሰቡ ሰዎች በህይወት በተአምር ተርፎ የሚወጣ ሰው ለማየት ጓጉተዋል።
የአልጀዚራ ባልደረባ በበኩሉ በትዊተር ገፁ ላይ ፍለጋውን እያካሄደ የሚገኘው ቡድን የሰው አካል ማግኘታቸውን ጠቅሶ " በፍርስራሽ ውስጥ የልብ ምቱ የተሰማው ሰው ይሆናል" ብሏል።
ማር ሚካዔል በፍንዳታው ክፉኛ ከተጎዱ ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው።
ከፍንዳታው በፊት ወደቡ ፊት ለፊት በሚገኝ ስፍራ ደማቅ የምሽት ህይወት ይታይ ነበር።

















