በጂቡቲ የኮቪድ-19 መጨመር ለአፋር ክልል ስጋት መሆኑ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Eric Lafforgue/Art in All of Us
በጂቡቲ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር ለአፋር ክልል ስጋት መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ በተለይ ለቢቢሲ እንደተናግሩት "ስጋቱ በጣም ከባድ ነው ምከንያቱም ጂቡቲ ውስጥ በርካታ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ተገኝተዋል። ከክልሉ ሕዝብ ጋር ተመሳሳይ ባሕልና አኗኗር ስላለ ወረርሽኙ ድንበር ሊሻገር የሚችልበት ሰፊ ዕድል አለ" በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አስካሁን ድረስ አንድ ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ ባላት በጂቡቲ ውስጥ ከ1100 በላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፤ የህሙማኑ ቁጥርም በየዕለቱ እየጨመረ እንደሚሄድ የአገሪቱ መንግሥት የሚያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ ለገቢና ወጪ ንግዷበዋነኝነት ከምትጠቀምበት የጂቡቲ ወደብን ሲሆን ሁለቱን አገራት የሚያገናኘው ዋና መንገድም በአፋር ክልል የሚያልፍ ከመሆኑ በተጨማሪ ክልሉ ከጂቡቲ ጋር ይዋሰናል።
በአሁኑ ወቅት ከጂቡቲ በተለያየ ምክንያቶች ወደ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሰዎች 510 በአፋር ክልል በተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ትላንት ብቻ "በተለያዩ መንገዶች ከጂቡቲ ወደ ክልሉ የገቡ 130 ሰዎች አሉ። ይህ ቁጥር በለይቶ ማቆያ ከሚገኙ 485 ሰዎች በተጨማሪ ማለት ነው። ከጂቡቲ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው" ብለዋል አቶ ያሲን።
ከጂቡቲ ተመልሰው በለይቶ ማቆያ ከሚገኙ እና በጥቆማ እና ቤት ለቤት በተደረጉ ቅኝቶች 296 ናሙናዎች ወደ አዲስ አበባ ተልከው 273ቱ ነጻ መሆናቸው ሲታወቅ የሌሎቹ ውጤት እየተጠበቀ እንደሚገኝም ኃላፊው አመልክተዋል።
በአፋር ክልል እስካሁን አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ መያዙ ተረጋግጧል። በገዋኔ ነዋሪ ከነበረው ግለሰብ ጋር በቅርብ ንክክኪ የነበራት ግለሰብ በተደረገላት ምርመራ ከበሽታው ነጻ ሆና ተገኝታለች።
ከጂቡቲ የሚገቡ ሰዎች በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ይደረግና ቁጥራቸው ሲጨምር ናሙናዎች ተሰብስበው ወደ አዲስ አበባ ይላኩ ነበር። "ውጤቱን መጠበቅ ትንሽ ጊዜ ይፈጅ ነበር። ውጤቱ በተቻለ መጠን በየሁለት ቀኑ ወይም በ24 ሰዓት ይመጣል። ሆኖም ናሙናዎቹ ወደተለያዩ ቤተ-ሙከራዎች ስለሚላኩ ውጤቱ አንድ ላይ አይመጣም" ሲሉ ያለውን አካሄድ ገልጸዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት እና ከጤና ጥበቃ ሚንስትር ጋር በመሆን ያዘጋጀው ቤተ-ሙከራ ዛሬ ሥራ መጀመሩን አቶ ያሲን ገልጸው፤ ቤተ-ሙከራው "ለሕዝቡም ለእኛም ትልቅ እፎይታ ነው" ብለዋል።
በሰመራ ከተማ ውስጥ በአፋር ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚገኘው ቤተ ሙከራ "ከ160 እስከ 200" ናሙናዎችን በየቀኑ መመርመር ይችላል ብለዋል።
ክልሉ የቤት ለቤት ትምህርት እና ልየታም እያካሄደ ይገኛል። እስካሁን በ29,578 እማወራና አባወራዎች ላይ ቅኝት እንደተደረገ ያመለከቱት ምክት የጤና ቢሮ ኃላፊው ትኩሳትና ሌሎች ምልክቶች ያላቸው እየተለዩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
"ሰዉ መረጃ ቢኖረውም መጠንቀቅ ላይ አሁንም ክፍፈተት አለ። የእምነት አባቶችና ሽማግሌዎችም ከፍ ያለ ርብርብ እያደረጉ ነው። መስጅዶች ላይ ጸሎት የለም አዛን ብቻ ነው፤ ለውጥ አለ። ሥራዎች ግን ይቀሩናል" ሲሉ ገልጸዋል።
በክልሉ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ የነበሩ እና ለ14 ቀናት የቆዩ 143 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸው ነጻ በመሆናቸው ወደ ቀዬአቸው እንደሚመለሱ አቶ ያሲን ተናግረዋል።














