ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጥቃት ልታጠናክር እንደምትችል ዜሌንስኪ ተናገሩ

የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ በቅርቡ የኻርኪቭ ከተማን መቆጣጠሯን ተከትሎ በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ጥቃቷን ልታጠናከር እንደምትችል አሳስበዋል።

የጦር መሣሪያ እጥረት ያጋጠማቸው የዩክሬን ወታደሮች እየገሰገሱ እየመጡ ያሉ የሩሲያ ወታደሮችን መቋቋም አቅቷቸዋል።

ዜሌንስኪ፤ የጦር ሠራዊት ሞራል እና ቁሳቁስ እንዳጠረው አምነው በርካታ ብርጌዶች አሁን ባዶ ሆነዋል ብለዋል።

ኤኤፍፒ ለተሰኘው የዜና ወኪል ድምፃቸውን የሰጡት ፕሬዝደንቱ የሀገሪቱ አየር ኃይል እንደተመናመነ አሳውቀው አጋር ሀገራት ተጨማሪ የአየር መከላከያ እና ተዋጊ ጄቶች እንዲልኩ ተማፅነዋል።

"ዩክሬንን ለመከላከል ከሚያስፈልገን አቅም አሁን ያለን 25 በመቶው ብቻ ነው" ሲሉ ስለአየር ኃይሉ ተናግረዋል።

"ሩሲያ በአየር ኃይል እንዳትበልጠን ቢያንስ 120 አሊያም 130 ዘመናዊ ጄቶች ያስፈልጉናል" ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ በቅርቡ የጦር መሣሪያ እርዳታን ጨምሮ 61 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለዩክሬን ማድረጓ ይታወሳል።

የሩሲያ ኃይሎች በቅርቡ የበጋ ወራት ጥቃት የጀመሩ ሲሆን በዩክሬን ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ የሚገኙ በርካታ ሥፍራዎችን በቁጥጥራቸው ሥር እያዋሉ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩክሬን ሁለተኛዋ ትልቋ ተከማ ኻርኪቭ በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ውላለች።

የኻርኪቭ ግዛት አስተዳዳሪ ኦሌግ ሲኔጉቦቭ በአንድ ሳምንት ብቻ 10 ሺህ ነዋሪዎች ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል ሲሉ ቅዳሜ ዕለት ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ ሀገራቸው በምስራቁ ድንበር በኩል "ጠላት" ዘልቆ እንዳይገባ 2.3 ቢሊዮን ዩሮ በጀት ለጦር ሠራዊቱ እንደሚመድቡ አስታውቀዋል።

ፖላንድ፤ ሩሲያን ጨምሮ ከቤላሩስ እና ከዩክሬን ጋር ድንበር ትጋራለች።

ዜሌንስኪ ለኤኤፍፒ ሲናገሩ ተጨማሪ ወታደሮች ወደ ጦር ግንባር መዝመት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

"አብዛኛዎቹ ከዚህ ቀደም የነበሩ ብርጌዶች አሁን ባዶ ሆነዋል። ተጨማሪ ወታደር ቢኖረን በተራ ማገልገል እንችላለን። የወታደሩም ሞራል ከፍ ይላል።"

ቅዳሜ ዕለት የወታደሩን ቁጥር ለመጨመር ያለ አዲስ የቅስቀሳ አዋጅ ይፋ ሆኗል። በአዲሱ ሕግ መሠረት ወደ ጦር ሜዳ ለመዝመት የሚያስፈልገው ዕድሜ ከ27 ወደ 25 ዝቅ ብሏል።

በአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 ሩሲያ ዩክሬንን መወረሯን ተከትሎ በርካታ ዩክሬናዊያን በነቂስ ወጥተው ሀገራቸውን ለመመከት ተመዝግበው ነበር። ይህ ቁጥር አሁን ተመናምኗል። በወቅቱ ጦር ሜዳ ከዘመተት መካከል በርካታ ወታደሮች ሞተዋል፣ ቆስለዋል አሊያም በአዲስ ምልምል ወታደሮች ለመተካት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

ባለፈው የካቲት ዜሌንስኪ በሩሲያ ወረራ ምክንያት 31 ሺህ ወታደሮች መገደላቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የቢቢሲ የሩሲያው ቢሮ እና ሚደያዞና የተሰኘው ድረ-ገፅ በጥምረት በሠሩት ምርመራ መሠረት በጦርነቱ የሞቱ ሩሲያዊያን ወታደሮች ቁጥር 50 ሺህ ገደማ እንደሆነ ቢገመትም ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ይገመታል።