የስዊድን የናጠጡ ሃብታሞች

ኮናርድ ቤርግስቶርም

የፎቶው ባለመብት, Maddy Savage

የምስሉ መግለጫ, ኮናርድ ቤርግስቶርም

ስዊድን ከፍተኛ ግብር በመጣል ትታወቃለች። በማኅበረሰቡ መካከል እኩልነትን ለማስፈን በሚደረግ ጥረትም ስሟ ይነሳል።

አሁን ደግሞ የአውሮፓ የሃብታሞች ሃብታም መዳረሻ ሆናለች።

ተራራማው የሊዲንጎ ደሴት በትልልቅ ቀይና ቢጫ ቤቶች የተሞላ ነው።

ከስቶኮልም ጥቂት አለፍ ብሎ የሚገኘው ደሴት ከስዊድን ቅንጡ መንደሮች አንዱ ነው።

ነጋዴው ኮናርድ ቤርግስቶርም በወይን ማቆያ ክፍሉ 3,000 የወይን ጠርሙስ ስብስብ አለው።

“የምወደው የፈረንሳይ ወይን ነው” ይላል።

ሰፊ መዋኛ ገንዳ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥሪያና የምሽት ክበብ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ይገኛሉ።

“ብዙ ሙዚቃ ወዳጅ ጓደኞች ስላሉኝ ሙዚቃ እንጫወታለን” ይላል።

ሄድፎን እና ስፒከር በመሸጥ ነው ሃብታም ነጋዴ የሆነው። ስዊድን እና ስፔን ውስጥ አራት ቤቶች አሉት።

በግራ ዘመም ፖለቲካ በምትታወቀው ስዊድን ውስጥ ልክ እንደሱ ሃብታም የሆኑ ተበራክተዋል።

አሁን ሥልጣን ላይ ያለው ቀኝ ዘመም መንግሥት ቢሆንም አገሪቱ በአብዛኛው የተመራችው በዴሞክራቶች ነው።

እኩል ተደራሽነትን ባማከለ መልኩ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግና ከከፍተኛ ግብር በሚገኝ ገንዘብ የተሻለ ማኅበራዊ አገልግሎት ለማቅረብ ቃል በመግባት ነው መንግሥታቱ የተመረጡት።

ባለፉት ሦስት አሠርታት የስዊድን የሃብታሞች ቁጥር ጨምሯል።

እአአ በ1996 በቢሊዮን ክሮነር (የስዊድን ገንዘብ) የሚቆጠር ገንዘብ ያላቸው ሰዎች 28 ብቻ ነበሩ። አብዛኞቹም ከሃብታም ቤተሰብ የተገኙ ናቸው።

በ2021 ግን 542 ቢሊየነሮች ተመዝግበዋል።

የእነዚህ ቢልየነሮች የሃብት ጥርቅም ከስዊድን የአገር ውስጥ ገቢ ወደ 70 በመቶውን ያህላል።

የስዊድን የሕዝብ ቁጥር 10 ሚሊዮን ነው። ከአጠቃላይ የሕዝብ ብዛት አንጻር የሃብታሞችን ቁጥጥር በንጽጽር ብንወስድ በአሜሪካ ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች ሁለቱ ብቻ ሃብታም ሲሆኑ፣ በስዊድን ግን አራቱ ሃብታም ናቸው።

ጋዜጠኛው አንድሬስ ሴርቫካ እንደሚለው፣ ስቶኮልም ውስጥ ሰዎች ወደ ሃብት ማማ ሲወጡ መመልከት ይቻላል።

አንደኛው ለሃብታሞች ቁጥር ምክንያት የሆነው የቴክኖሎጂ ዘርፍ ማደግ ነው።

 ኒካስ አብላርት

የፎቶው ባለመብት, Maddy Savage

የምስሉ መግለጫ, ኒካስ አብላርት

ስካይፕ እና ስፖቲፋይ የተፈጠሩት ስዊድን ነው።

ኪንግ እና ሞጃንግ የተባሉት የጌም ድርጅቶች መነሻም ከዚያው ነው።

ቪዛ በሁለት ቢሊዮን ዶላር የገዛው የፋይናንስ ተቋም ቲንክ የተመሠረተው ስዊድን ነው።

ኦላ አህላቫርሰን ታዋቂ ነጋዴ ነው። ከ1990ዎቹ አንስቶ በስኬት ጎዳና ላይ ይገኛል።

የስዊድን የግብር ሥርዓት ከሌሎች አገራት የተለየ እንደሆነ ያስረዳል።

ሊዲንጎ ደሴት

የፎቶው ባለመብት, Maddy Savage

የምስሉ መግለጫ, ሊዲንጎ ደሴት

“ስዊድን ውስጥ የመተባበር ባህል አለ። ነጋዴዎች በቴክኖሎጂ ተቋማት ኢንቨስት ያደርጋሉ። አርዓያም ናቸው” ይላል።

በስዊድን አንድ ምርት ምን ያህል ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ በውስን አካባቢ መሞከር የተለመ መሆኑን ይገልጻል።

ጋዜጠኛው አንድሬስ በበኩሉ አገሪቱ የተለወጠችውና ለናጠጡ ሃብታሞች ገነት የሆነችው በገንዘብ ፖሊሲው ምክንያት ነው ሲል ይከራከራል።

አንድሬስ ሴርቫካ

የፎቶው ባለመብት, Miriam Preis

የምስሉ መግለጫ, አንድሬስ ሴርቫካ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከ2010 ጀምሮ የወለድ መጠን አነስተኛ የሆነበት አገር ነው። ስለዚህ ብዙ ስዊድናውያን በቀላሉ ገንዘብ ይበደራሉ። ኢንቨስትም ያደርጋሉ።

ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ ሰዎች ከፍተኛ ግብር ይከፍላሉ።

ከግል ገቢያቸው ከ50 በመቶው በላይ ለግብር ይውላል። ይህም ከአውሮፓ አገራት ትልቁ ግብር ነው።

የሃብትና ውርስ ግብር በአገሪቱ የለም። ከድርሻ ገበያ የሚገኝ ገቢ ላይ የተጣለው ግብር ደመወዝ ላይ ከተጣለው ግብር ያንሳል።

“ሃብታሞች ከስዊድን መውጣት አይጠበቅባቸውም። እንዲያውም ወደ ስዊድን ነው የሚመጡት” ይላል ጋዜጠኛው።

በሃብታሞች ደሴት ላይ የሚኖረው ኮናርድ እንደሚለው፣ የግብር ሁኔታው ለሃብታሞች ምቹ ነው።

ሃብታሞች ከሚቀጥሯቸው ሠራተኞች በተጨማሪ በጀማሪ ድርጅቶች ላይም ሃብት ፈሰስ በማድረግ ምጣኔ ሀብቱን ያነቃቃሉ።

በኢንቨስትመንት ጥሩ ስም ካላቸው አንዱ ኒካስ አብላርት ነው።

በ2017 ዩኒኮርን የተባለ ተቋም በ130 ሚሊዮን ዶላር ጀምሯል።

“እንደ ሌሎች ሃብታሞች መርከብ ወይም ጀት የመግዛት ልማድ የለኝም” ይላል። የሚያስደስተው ገንዘቡን ኢንቨስት ማድረግ እንደሆነ ይናገራል።

ሆኖም ግን ስዊድናውያን ሃብታሞች ገንዘባቸውን እንዴት ይጠቀሙበታል የሚለው ላይ የተለያየ አቋም የሚያንጸባርቁ አሉ።

ኦርቤሮ ዩኒቨርስቲ የሠራው ጥናት እንደሚያሳየው፣ የስዊድን መገናኛ ብዙኃን ለሃብታሞች አወንታዊ ሽፋን ይሰጣል።

የመገናኛ ብዙኃን አጥኚው አክሰል ቪክስቶርም “የናጠጡ ሃብታሞች እንደ ታታሪና ነጻ ተደርገው ሲቀርቡ ከጀርባው ያለውን እኩልነት ማጣት ያስቸግራል” ይላል።

“ምን ማድረግ ያለባቸው ሰዎች ቢልየነር መሆን ይችላሉ የሚል ስዊድናዊ አስተሳሰብ አለ” ይላል ጋዜጠኛው አንድሬስ።

የስዊድን ሃብት በአብዛኛው በነጭ ወንዶች የተያዘ ነው። ይህም ከዘርና ጾታ እኩልነት አንጻር ጥያቄ ያጭራል።

ናይጄሪያዊቷ ሎላ አኪናማዴ “ሰዎች ሃብት መፍጠር የሚችሉበት አገር ቢሆንም ማን መነሻ ገንዘብ ያገኛል? የሚለው እኩልነት አለመስፈን የሚታይበት ነው” ስትል ትተቻለች።

ስዊድን የተሻለች አገር ተብላ ብትሞካሽም የአገሪቱ ሥርዓት ያገለላቸው እንዳሉ ትገልጻለች።