የ17 ዓመቱ ወጣት በዓለም ዙርያ ብቻውን አውሮፕላን በማብረር ክብረ ወሰን ሰበረ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/STOYAN NENOV
ወጣቱ ማክ ሩተረፎርድ ትንሽዬ አውሮፕላን በዓለም ዙርያ በማብረር ክብረ ወሰን ሰበረ።
በዩኬ ተወልዶ በቤልጂየም ያደገው ማክ ዓለምን የዞረባት ትንሽዬ አውሮፕላን ሻርክ ትባላለች።
ማክ በዚህች አነስተኛ አወሮፕላን ብቻውን 52 አገራትን አዳርሶ በሰላም ተመልሷል።
ወጣቱ ማክ በነዚህ አገራት አውሮፕላኑን ሲያበር በርካታ ያልተጠበቁ አደጋዎች ተደቅነውበት እንደነበረ አውስቷል።
በሱዳን የአሸዋ አውሎ ንፋስ እንዳጋጠመውና በፓስፊክ ውቅያኖስ ደግሞ አንድ ሌሊት በሰው አልባ ስፍራ እንዳሳለፈ ታነግሯል።
የማክ እህት ዛራ ትባላለች። እሷም በተመሳሳይ ዓለምን የብቻ አውሮፕላን እያበረረች ለመዞር የመጀመርያዋ ወጣት ሴት ናት።
ይህንን የብቻ ጉዞዋን ያጠናቀቀችው ባለፈው ጥር ወር ላይ ነበር።
ከልምዷ በመነሳትም ለወንድሟ ማክ ጠቃሚ ምክሮችን እንደሰጠችው ተናግራለች።
ከዚህ ቀደም ይህ ክብረ ወሰን ተይዞ የነበረው ትራቪሰ ሉድሎው በሚባል የ18 ዓመት የብሪታኒያ ወጣት ነበር።
አሁን አዲስ ታሪክ የጻፈው ወጣቱ ማክ ይህን ክብረ ወሰን ከሰበረ ወዲህ ባደረገው ንግግር፣ “ምንም ያህል ወጣት ብትሆኑ ሕልማችሁን ምንም ነገር ሊያስቆመው አይገባም” ብሏል።
ማክ በዚህ የብቻ የበረራ ጉዞው አፍሪካን አሜሪካን አውሮፓንና ኢሲያን እንዲሁም ሁሉት ውቅያኖሶችን አዳርሷል።

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/STOYAN NENOV
የወጣቱ ማክ ቤተሰቦች የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ናቸው።
ማክ ይህን የብቻ የበረራ ጉዞ ለማድረግ የተነሳው ባለፈው መጋቢት ከቡልጋሪያ ነበር።
ማክ በዚህ በረራው ውስጥ ውብ ሥፍራዎች ብሎ ከጠቀሳቸው ቦታዎች መሀል የኬንያ ብሔራዊ ፓርክ እና የኒውዮርክ ከተማን ሰማይ ነው።
ዝቅ ብሎ በአነስተኛ ከፍታ መብረር የሰጠኝ ዕድል በንቃትና በትኩረት እንዳበር አስችሎኛል ብሏል ለሲኤንኤን።
ወጣቱ ማክ ወደፊትም አውሮፕላን ማብረሩን እንደሚገፋበት፣ ኤይርፎርስን ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳለውና ነገር ግን ገና በእርግጠኝነት እንዳልወሰነ ተናግሯል።
ከዚህ በኋላም ወደ ትምህርቱ በመመለስ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚሻም ገልጧል።
ማክ በዚህ ጉዞው ሁለት የጊነስ ክብረ ወሰኖችን በእጁ ያስገባ ሲሆን አንዱ በወጣትነቱ የብቻ በረራ በማድረግ ዓለምን መዞሩ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በትንሽ አውሮፕላን ዓለምን ማካለሉ ነው።
ወጣቱ የብቻ በረራ ያደረገባት አውሮፕላን ሻርክ በሰዓት 300 ኪሎ ሜትር የመክነፍ አቅም አላት።
እህቱ ዛራ ወንድሟ ማክ በአየር ላይ ሳለም በተከታታይ ድጋፍና ምክር ስትሰጠው እንደነበረ ተናግራለች።
ወላጆቻችን በየቀኑ ይደውሉለት ነበር፤ እኔም አነጋግረው፥ አበረታታው ነበር ብላለች።
ማክ ገና ከሦስት ዓመቱ ጀምሮ አውሮፕላን አብራሪ መሆን ይፈልግ እንደነበረና በ15ቱ ሕልሙን በማሳካት የአብራሪነት ፍቃድ ማግኘቱን አውስቷል።
የማክ አባት ሚስተር ሩተርፎርድ ፕሮፌሽናል አብራሪ ሲሆን እናቱ ቢያትሪስ ደግሞ የግል አውሮፕላን አብራሪ ናት።
የማክ ቅድመ አያቶችም በተመሳሳይ አውሮፕላን አብራሪዎች ነበሩ።
ማክ የብሪታኒያና የቤልጂየም ዜግነት አለው።
ወጣቱ ማክ "ትልቅ ነገር ለማከናወን ትልቅ ሰው መሆን የለብንም" የሚል ፍልስፍና አለው።












