የፌደራሉ መንግሥት ዛሬ ማለዳ ጥቃት የከፈተው ህወሓት ነው አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፌደራሉ መንግሥት በአማራ እና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ጥቃት የከፈተው ህወሓት ነው በማለት የትግራይ ኃይሎችን ተጠያቂ አደረገ።
ከሰዓታት በፊት የትግራይ ኃይሎች በደቡባዊ ትግራይ አቅጣጫ በፌደራል መንግሥት እና በአማራ ኃይሎች ጥቃት ተከፍቶብናል ብለው ነበር።
“ከትግራይ ሠራዊት ወታድራዊ ኮማንድ” ተሰጠ የተባለው መግለጫ ዛሬ ረቡዕ፣ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ንጋት 11 ሰዓት ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት በፌደራል መንግሥቱ እና በአማራ ኃይሎች ጥምር ኃይል ጥቃት ተከፍቷል ብሎ ነበር።
የፌደራል መንግሥት ኮሚኒኬሽን በበኩሉ “ዛሬ (ነሐሴ 18/2014) ንጋት ላይ በምስራቅ ግንባር በቢሶበር፣ በዞብል እና በተኩለሽ አቅጣጫዎች ከለሊቱ 11 ሰአት ጀምሮ ጥቃት ፈጽሟል” ብሏል።
ሁለቱ አካላት አንዳቸው ሌላኛውን ለጥቃት ተጠያቂ ማድረጋቸው በአዋሳኝ የድንበር አካባቢዎቹ አዲስ ግጭት መከሰቱን ያረጋግጣል።
ቢቢሲ እና ሮይተርስ የዜና ወኪል ቀደም ሲል ያነጋገሯቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የከባድ ጦር መሳሪያ ድምጽ እንደሰሙ ተናግረው ነበር።
በትግራይ ቴሌቪዥን በተነገረው የትግራይ ኃይሎች መግለጫ፤ የአማራ ሚሊሻ እና ፋኖ እና የአገር መከላከያ ሠራዊት ጥምር ኃይል በትግራይ ደቡብ አቅጣጫ መጠነ ሰፊ ጥቃት ጀምረዋል ብሏል።
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ ንጋት ላይ በትዊተር ገጻቸው “ከሳምንት ትንኮሳ በኋላ የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአማራ ሚሊሻ እና የወሎ ፋኖ እንዲሁም [የመከላከያ] 6ኛ ኮማንድ ጥቃት ከፍተዋል” ብለዋል።
በመግለጫው የፌደራል እና የክልል ኃይሎች የጀመሩት ዘመቻ ዋነኛው ዓላማ "ከምዕራብ ትግራይ እና ምዕራብ ጎንደር ወደ አዲአቦ፣ አስገዲ እና ጸለምቲ እንደሆነ ግልጽ ነው" ብሏል።
በመግለጫው ላይ የትግራይ ኃይሎች “ጥቃቱን ለመመከት” እና “ወደ ጸረ ማጥቃት ለመሸጋገር” ሙሉ አቋም ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ከጥቂት ቀናት በፊት የትግራይ ኃይሎች በሰሜን ምዕራብ በኩል የፌደራል መንግሥት ኃይሎች የከባድ መሳርያ ድብደባ መፈፀማቸውን ጠቅሰው ነበር።
ይሁን እንጂ መንግሥት ይህንን ውንጀላ አስተባብሎ፣ "ከሰላም ድርድሩ ለመሸሽ የሚቀርብ ሰበብ ነው" ብሎ ነበር።
ይህንን ተከትሎም የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ እስካሁን የነበረው የተኩስ አቁም በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ "ፈርሷል" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር።
'ህወሓት ለትንኮሳው ሲዘጋጅ ነበር'
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች በበኩሉ ህወሓት ከዚህ ቀደም በሁለቱ ተዋጊዎች መካከል ተደርሶ የነበረው “የተኩስ አቁሙ በይፋ ፈርሷል” ማለቱ እና ይህን ተከትሎ ያወጣው መግለጫ አሰቀድሞ ለትንኮሳው ሲዘጋጅ እንደነበር ግልጽ ማሳያ ነው ብሏል።
“ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የትግራይን ወጣት ለማስጨረስ ህወሓት የሚያደርገውን የጦርነት ጉሰማ እንዲያቆም ጠንካራ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል” ብሏል የፌደራል መንግሥቱ።
የፌደራሉ መንግሥት የትግራይ ኃይሎች የሚሰነዝሩት ጥቃት ለመመከት ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪውን አስተላልፏል።
ጨምሮም ህወሓት “በትንኮሳው ከገፋበት፤ መንግሥት አገር የማዳን ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታ ስላለበት እንዲሁም የሽብር ቡድኑ ወደደም ጠላም ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ለማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ይወስዳል” ሲል የፀጥታ ኃይሉ “ከነሙሉ ብቃትና ቁመናቸዉ በተጠንቀቅ ላይ ናቸው” ብሏል።
ድርድር
ይህ የትግራይ ኃይሎች መግለጫ የተሰማው ላለፉት 21 ወራት ገደማ በጦርነት ውስጥ የቆዩት ተዋጊ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር በውይይት እንዲፈቱ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ባሉበት ወቅት ነው።
ባለፉት ጥቂት ወራት የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ እና ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች እና አምባሳደሮች በመቀለ እና አዲስ አበባ ባለሥልጣናትን ማነጋገራቸውን ተከትሎ በበርካቶች ዘንድ የሰላም ተስፋ መኖሩን ገልጸው ነበር።
ይሁን እንጂ ምዕራባውያኑ ዲፕሎማቶች እና አምባሳደሮች ወደ መቀለ ከተጓዙ ከሳምንታት በኋላ የህወሓት ኃይሎች በፌደራል መንግሥቱ በተለያዩ አቅጣጫ ጥቃት እንደተከፈተባቸው ተናግረው ነበር።
አቶ ጌታቸውም በትዊተር ገጻቸው ለሰብአዊነት ሲባል ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሷል ብለው ነበር።
የፌደራል መንግሥቱ ቃል አቀባይ ግን “የሰላም ስምምነቱ ሳይዘገይ በትግራይ መሠረታዊ አገልግሎት እንዲጀመር ለማድረግ የደኅንት ሁኔታ መመቻቸት ስላለበት ቅድሚያ የፖለቲካ ውይይት ማድረግን የአፍሪካ ኅብረት እንዲያጠናክር እያደረገ” እንደሚገኝ ጠቅሰው ህወሓት ግን “የሰላም አማራጭን ለመከተል ስላልፈለገ” መንግሥት “ተኩስ አቁሙን አፍርሷል” ማለቱን ኮንነዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ያለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 12/2014 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ኃይሎች ላይ ተኩስ ከፍቷል መባሉ “ሐሰት ነው” ብለዋል።
የትግራይ ኃይሎች ረቡዕ ነሐሴ 11/2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ የፌደራል መንግሥቱ ጦር “በምዕራብ ትግራይ በኩል በከባድ መሣሪያ የታገዘ ጥቃት ፈጽሟል” ማለታቸው አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ደደቢት አካባቢ ባሉ የትግራይ ኃይሎች ላይ በከባድ መሣሪያ ለአንድ ሰዓት የቆየ ድብደባ አድርሷል ሲልም ከትግራይ ወታደራዊ ዕዝ የወጣው መግለጫ ይጠቁማል።
በዚህም ለወራት ታውጆ የነበረው የሰብአዊ እርዳታ የተኩስ አቁም አዋጅ ተጥሷል ብሏል መግለጫው።
ይህን መግለጫ ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ፣ በትግራይ ኃይሎች የተሰነዘረው ክስ “ከሰላም ንግግር ለመሸሽ እንደ ምክንያት የቀረበ ነው” ብለዋል።
በተያየዥ ዜና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትላንት ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሠራዊቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ “የመዘገብ ወይም የማራገብ አሉታዊ ሙከራዎች በአስቸኳይ ይቁሙ” ሲል አሳስቧል።
በመግለጫው “አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘገባዎች እና መረጃዎች አፍራሽ ውንጀላን ባልተገባ መልኩ እየተቀባበሉት መሆኑን አስተውለናል” ብሏል።
“ጠላት በዚህ ገባ፣ በዚህ ወጣ፤ የወገን ሠራዊት በዚህ ገባ፣ በዚህ ወጣ የሚለው ወሬ በፍፁም ዜና እና የዜና ትንታኔ ሊሆን አይችልም” ብሏል አገር መከላከያ በመግለጫው።












