ሁሉንም የሚያስማማ ገለልተኛ መርማሪ አካል ከየት ይገኛል?

ወለጋ ውስጥ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከተፈጸሙ ጥቃቶች በኋላ ተፈናቅለው አማራ ክልል ሐይቅ ከተማ በተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ የሚገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ወለጋ ውስጥ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከተፈጸሙ ጥቃቶች በኋላ ተፈናቅለው አማራ ክልል ሐይቅ ከተማ በተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ የሚገኙ

የእርስ በእርስ ግጭት እና ጦርነት በከፋባት ኢትዮጵያ፣ ፍትሕ ለማስፈን በግንባር ቀደምትነት ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል አንዱ ለተፈጸሙ ጥፋቶች ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ አንድ ጉዳይ መሆኑን የተለያዩ ወገኖች ይናገራሉ።

ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ በሰዎች ላይ እንዲሁም በንብረት ላይ በተፈጸሙ ጥፋቶች ዙሪያ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የተሳተፉ ወገኖች የሚቀርቡባቸውን ክሶች አይቀበሉም።

በተጨማሪም እነዚህ አካላት በተፈጸሙ ጥፋቶች እና ግፎች ዙሪያ ይካሄዱ በሚባሉ ምርመራዎች ላይ ተመሳሳይ አቋም የላቸውም።

በሰሜን ኢትዮጵያ የመንግሥትን ወታደሮች እየተዋጉ ያሉት የህወሓት ኃይሎች፣ በኦሮሚያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እንዲሁም ተቃዋሚዎች ለሚፈጸሙ በደሎች ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ።

መንግሥት በበኩሉ እነዚህን ጥሪዎች በይፋ መቀበሉን ሲገልጽ አይታይም።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በደቡብ እና በምዕራብ ኦሮሚያ እንዲሁም ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ባጋጠሙ ግጭቶችን በተፈጸሙ ጥቃቶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

የተቃዋሚዎች የገለልተኛ መርማሪ ፍላጎት

ህወሓት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳርን በበላይነት በያዘ ጊዜ፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አገሪቱ ውስጥ ተፈጽመዋል። ነገር ግን ገለልተኛ መርማሪዎች አገሪቱ ውስጥ ገብተው እንዲመረምሩ ፈቅዶ አያውቅም።

በአሁኑ ወቅት ከመንግሥት ሠራዊት ጋር እየተዋጋ ያለው ይህ ቡድን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ኮሚሽን ያደረጉትን ምርመራ ከጅምሩ ሲተች ቆይቶ እንደማይቀበል ገልጿል።

የህወሓት ትልቁ ጥያቄ የኢትዯጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ‘ገለልተኛ አይደለም’ የሚል ነው።ኮሚሽኑ ግን ይህንን አይቀበልም።

በኦሮሚያ ውስጥ የህወሓት አጋር የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትም በሰላማዊ ሰዎች ላይ ፈጽሟቸዋል በሚተባሉ ጥቃቶች ዙሪያ ቢሆን ገለልተኛ መርማሪ አካል ምርመራ እንዲያደርግ ከሚጠይቁት መካከል ነው።

በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ይህ ቡድን፣ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን እና በክልሉ የሚኖሩ ሰዎችን ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ይፈጽማል በሚል የሚቀርብበትን ክስ አይቀበልም።

ከታጣቂዎች ውጪም ቢሆን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀርባሉ።

ሁለቱም አካላት ይህንን ጥያቄ እንዲያነሱ ያስገደዳቸው መንግሥት ላይ አመኔታ እንደሌላቸው በመግለጽ ነው።

“የዲሞክራሲ ሥርዓት በሚጠይቀው መልኩ፣ የተመሰረተ መንግሥት የለም” በማለት የኦፌኮ አመራር አቶ ጥሩነት ገምታ ይገልጻሉ።

በእንደዚህ ዓይነት መንግሥት የሚቋቋም ተቋም ደግሞ “ነጻ ሆኖ መርምሮ፣ ነጻ የሆነ ዘገባ ያቀርባል ብለን ሙሉ በሙሉ ስለማናምን እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ አቀረብን” ሲሉ ሃሳባቸውን ለቢቢሲ አካፍለዋል።

እነዚህ ተቋማት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሚያቀርበውን ምርመራ በሙሉ አይቀበሉም ማለት ግን አይደለም።

አንዳንዶች እነዚህ ተቃዋሚዎች የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያደረጋቸው ምርመራዎች “የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ሲያሟላ ይቀበላሉ፣ አለበለዚያ ይተዋሉ” ሲሉ ይተቿቸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ግን የሚቀርብባቸውን ትችት አይቀበሉም።

የምታለቅስ ሴት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳትን አስከትሏል

መንግሥት ለምን ጥያቄዎችን አይቀበልም?

መንግሥት ገለልተኛ ምርመራዎች በተደጋጋሚ የሚቀርብለትን ጥያቄ ከማይቀበልበት ምክንያት አንዱ ምርመራዎችን የሚያካሄድ ተቋም እንዳለው በመግለጽ ነው።

በጊምቢ በተከሰተው ግድያ እና ከዚያ በኋላ ገለልተኛ ምርመራዎች እንዲካሄዱ ጥያቄ ሲቀርብ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ የሆኑት ቢለኔ ስዩም “ይህ ማለት [ገለልተኛ መርማሪ ጥያቄ መቀበል] ኢትዮጵያ ብቃት ያለው ተቋም የላትም ብሎ ማመን ነው” ሲሉ ለሚዲያ አባላት ተናግረው ነበር።

የሕግ ባለሙያ እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አደም ካሴ (ዶ/ር) “መንግሥት ራሱን አንደ ገለልተኛ እና ብቃት እንዳለው ነው የሚያየው። ከዚህ ውጪ ሌላ አካል የሚገባ ከሆነ መንግሥት ገለልተኛ እንዳልሆነ አምኖ መቀበል ይሆንበታል” ይላሉ።

“ሁለተኛው መንግሥት የሚለውን ሊያፋልስበት ይችላል” በማለት ለምን መንግሥት ሃሳቡን እንደማይቀበል ያስረዳሉ።

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች መንግሥታት በአገራቸው ለተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ገለልተኛ አጣሪ ቡድን እንዲመሰረት ሲጠየቁ አለመቀበላቸው የተለመደ ነው።

ከጀርባቸው የሚታዩ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ወሲባዊ ጥቃት ሁሉም ወገኖች ከሚከሰሱባቸው የመብት ጥሰቶች መካከል አንዱ ነው

መንግሥት ብቻውን መመርመር ይችላል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ገለልተኛ ተቋማት እና ሁሉንም አካላት በእኩል ዐይን የሚያዩ ሊኖሩ ይገባል።

ነገር ግን የእነዚህ ገለልተኛ አካላት እጦት በኢትዮጵያ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የቆየ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ገለልተኛ ተግባራትን ለማከናወን ጥረት ከሚያደርጉ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አንዱ ነው።

ኮሚሽኑ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲሁም ከሕግ አግባብ ውጪ የተፈጸሙ ግድያዎችን አጣርቶ ሪፖርቶችን ይፋ አድርጓል።

ከእነዚህ መካከል የከረዩ የገዳ አባላት በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ ስለመገደላቸው ያደረገውን ምርመራ ተከትሎ ያወጣው ሪፖርት ይጠቀሳል።

በተጨማሪም በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን በጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ ውስጥ የካቲት 24/2014 ዓ.ም በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሲቪል ሰዎች ላይ የተፈፀመ ግድያን የሚመለከተውም ሪፖርት ይጠቀሳል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችንም ተከታትሎ በመመርመር ሪፖርቶችን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። 

ይህም ሆኖ ግን በኮሚሽኑ ላይ አሁንም ትችታቸውን የሚሰነዝሩ ወገኖች አሉ። ነገር ግን ኢሰመኮ አስካሁን ባከናወናቸው ተግባራት ከተለያዩ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ተቋማት እውቅናን አግኝቷል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ከዚህ ቀደም ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ “የመንግሥት ጫና የለብንም። ከመጣም አንቀበልም” ሲሉ መልሰው ነበር።

“ሥራችን ሙሉ በሙሉ ነጻ እንደሆነ እናምናለን። በሥራችንም ይህ ነገር እየታየ አይደለም፤ የመንግሥት ተቋማት ከዚህ ቀደም ነጻ ስላልነበሩ ሰዎች እንደዚህ ዓይነት ጥርጣሬ ስለተሰማቸው ብዙም አይገርመኝም” ሲሉም መልሰዋል።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች እንደሚሉት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ካሉት ትልቅ ችግሮች መካከል አንዱ አለመተማመን ነው።

“ከፍተኛ በደሎች ናቸው እየተፈፀሙት ያሉት” የሚሉት ዶ/ር አደም፣ “እነዚህ በደሎች በግጭት መካከል የሚከሰቱ ስለሆኑ መንግሥት በራሱ ተጠርጣሪ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ።

“አንደኛው ተጠርጣሪ ብቻውን መርማሪ ነው ብሎ ማሰብ ትክክል ላይሆን ይችላል” ብለዋል።

የከረዩ አባ ገዳ ከድር ሃዋስ ቦሩ

የፎቶው ባለመብት, social media

የምስሉ መግለጫ, ኢሰመኮ ምርመራ አድርጎ ይፋ ባደረገው ሪፖርት በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ከተገደሉት መካከል አንዱ የሆኑት የከረዩ አባ ገዳ ከድር ሃዋስ ቦሩ

ማን ገለልተኛ መርመሪ ሊሆን ይችላል?

የፖለቲካ ተንታኙ አደም ካሴ (ዶ/ር) ገለልተኛ መርማሪ የሚለው “በምክክር የሚፈታ” መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ይህም ማን ገለልተኛ መርማሪ እንደሚሆን የሚወስነው ምክክር ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት የሚስማሙበት ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

“ይህ አካል ከውጭ ሊሆን ይችላል፤ ከውስጥ እና ከውጭም ሊሆን ይችላል። ከውስጥ ብቻም ሊሆን ይችላል። ትልቁ ነገር ያ አካል ቢያንስ ቢያንስ በአብዛኞቹ ወገኖች ተቀባይነት እና ብቃትም ሊኖረው ይገባል። በሕዝቡ በኩልም ተዓማኒነት ሊኖረው ይገባል” ሲሉ ይገልጻሉ።

ገለልተኛ መርመራዎች በውጭ አካላት፣ በሲቪክ ማኅበራት እና በሕብረተሰቡ ጫና የሚፈጠሩ ናቸው። ለገለልተኛ ምርመራዎች ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል አንዱ ደግሞ የሰላም መኖር ነው።

“ሰላም ከሌለ ምርመራዎችን ማካሄድ አይቻልም። ግጭቶች በቀጠሉ ቁጥር ፍትሕ ይሰፍናል ብሎ ማሰብም አይቻልም። . . . ቢያንስ ቢያንስ ትንሽ ሰላም ሊኖር ይገባል” ይላሉ ዶ/ር አደም።

አክለውም ፍትሕ እንዴት መስፈን እንዳለበት በቅድሚያ መታሰብ አለበት። እንደ ዶ/ር አደም ሃሳብ ግጭቶች ቀጥለው ባሉበት ፍትሕን ማስፈን አዳጋች ነው።

“ፍትሕ የሰላም ቅድመ ሁኔታ ሳይሆን፣ የሰላም ሂደቱ አካል ነው መሆን ያለበት” ይላሉ።