የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት ለምን ለድርድር መቀመጥ አልቻሉም?

የተጨባበጡ እጆች

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ወደ ሰላም ድርድር የሚያደርጉት ጉዞ በእንቅፋት የተሞላ ሆኗል።

ሽምግልናው በማን ይመራ በሚለው ላይ ስምምነት የለም። የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ኦሌሴጉን ኦባሳንጆ ድርድሩን እንዲመሩ ይፈልጋል።

የትግራይ ኃይሎች ደግሞ ተሰናባቹ የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ የድርድሩ መሪ እንዲሆኑ መርጠዋል።

ማዕከላዊው መንግሥት እና የትግራይ አማፂያን ከስምምነት ያልደረሱበት ጉዳይ ይህ ብቻ አይደለም። ከሁሉ ከሁሉ አስቀድሞ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ ማድረግ ወይስ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረስ የሚሉት በእንጥልጥል የቆዩ ናቸው።

እንዲሁም ድርድሩ የት ይካሄድ? እና መቼ ይጀምር የሚሉት ጥያቄዎችና ሌሎችም ግልጽ ምላሽ ያላገኙ ጉዳዮች ሆነው ቆይተዋል።

ከዚህ በሻገር ደግሞ ከሁለቱም በኩል ያሉ ከፍተኛ ባልሥልጣናት በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ እና በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ወቀሳ ሲሰነዛዘሩ መመልከት የተለመደ ሆኗል።

አልፎም ከሰሞኑ ህወሓት የፌዴራል መንግሥቱ ጥቃት እንደሰነዘረበት ሲገልጥ፣ መንግሥት ደግሞ ወቀሳውን በማስተባበል ከሰላም ድርድሩ ለመራቅ የተደረገ ጥረት ነው ብሏል።

ትናንት ረቡዕም፣ የፌደራሉ አና የትግራይ ኃይሎች አንዳቸው ሌላኛቸውን በትግራይ ደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ጥቃት በመክፈት በመወነጃጀል መግለጫ አውጥተዋል።

ለመሆኑ የትግራይ አማፂያን የሰላም ድርድሩን ይፈልጉታል? የኢትዮጵያ መንግሥትስ?

ድርድሩ የት ደረሰ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመረጡት ሰባት የመንግሥት ተወካዮች ባለፈው ሳምንት አዲስ የድርድር ማዕቀፍ ይፋ አድርገዋል።

ይህ አዲሱ ረቂቅ ሦስት ንዑስ ሐሳቦችን ይዟል። አንደኛው ድርድሩ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ይጀመር የሚል ነው።

ሁለተኛው ሐሳብ ድርድሩ ሲጀመር ተኩስ አቁም ላይ እንዲያተኩር እና በሂደት ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ ውይይት ይካሄድ የሚል ነው።

የፌደራሉ መንግሥት ልዑካን በሦስተኛነት ያቀረቡት የመፍትሔ አማራጭ ጉዳዩን በብሔራዊ ውይይት መፍታት ነው።

ኮሚቴው ያለፈው ሳምንት ከመገባደዱ በፊት የመፍትሔ ሐሳቦቹን ለአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦባሳንጆ እንደሚያቀርብ ገልጾ ነበር።

ነገር ግን ተደራዳሪው ኮሚቴ ያቀረበው ሐሳብ በህወሓት ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም።

የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ጌታቸው ረዳ የኮሚቴውን መግለጫ ተከትሎ ቅዋሜያቸውን በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

"በዐቢይ አስተዳደር የተቋቋመው የሰላም የተባለው ኮሚቴ ነገሮችን በማጠላለፍ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማታለል እየሞከረ፣ በሌላ በኩል የመንግሥት ኃይሎች ትንኮሳ እየፈፀሙብን ይገኛሉ” ሲል ባለፈው ሐሙስ ጽፈዋል።

አብዛኛውን ጊዜ ሁለት ተዋጊዎች ወደ ድርድር ሲገቡ መሰል መሰናክሎች ይገጥሟቸዋል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ያሬድ ኃይለማርያም ናቸው።

አቶ ያሬድ እንደሚሉት ሁለቱም ወገኖች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በሌሎችም ግጭቶችም የተለመዱ ናቸው።

“አደራዳሪው ማን ይሁን? የት ቦታ ይሁን? በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ እንደራደር? የሚሉት ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም። አንዳንድ ጊዜ ሰበብም ይሆናል። ሌላ ጊዜ ምክንያቶቹ ትክክለኛ ሊሆኑ ይችላሉ።”

ትግራይ ውስጥ የስልክ፣ የባንክ፣ የቴሌኮም፣ የትራንስፖርት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች አገልግሎት ከተቋረጠ ሰንብቷል።

ህወሓት እኒህ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ እሻለሁ ይላል፤ የፌዴራል መንግሥቱ ደግሞ ዋነኛው እንቅፋት ለጥገና የሚሰማሩ ሠራተኞች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ነው ይላል።

ባለፈው ነሐሴ የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት ደብረፂዮን ገብረሚካዔል ለጥገና የሚመጡ ሠራተኞች ደኅንነታቸው ይጠበቃል ማለታቸው ይታወሳል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ህወሓት ለንግግር እንዲቀመጥ ጫና ማድረግ አለበት ብለዋል።

አቶ ያሬድ እንደሚሉት ግን ሁለቱም ወገኖች ሰላምና እርቅ የሚፈልጉ ከሆነ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መደራደር በራሱ ድርድሩ እንደተጀመረ ያስቆጥረዋል።

“እነዚህ ጥያቄዎች የሂደት ጥያቄዎች ናቸው። ድርድሩ ላይ ከሚነሱት ሐሳቦች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ የሚባሉ ናቸው። ሆኖም አንደኛው ወገን ከዚህ ሲያፈነግጥ ከመነሻውም የሰላም ፍላጎት አልነበረውም ማለት የሚለውን ያሳያል።”

“ብዙ ጊዜ እርቅ የሚኖር ሁለት ጨዋ ሲጣላ ነው ይባላል” የሚሉት አቶ ያሬድ፣ “ከተደራዳሪዎቹ መካከል አንዱ እንኳን ከቅን ልቡና ውጭ ከሆነ፣ እነዚህ ጥያቄዎች ቢመለሱ እንኳ በሌላ ምክንያት ችግር መፈጠሩ አይቀርም።”

የኢትዮጵያ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሁለቱ ወገኖች ዳግም ወደ ለየለት ጦርነት ይገቡ ይሆን?

ህወሓት እና የፌዴራል መንግሥት ወደ ድርድሩ ከመግባታቸው በፊት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይደርሱ እንደሚችሉ ይነገራል።

“በጣም ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮች ለመደራደሪያ እንደ ቅደመ ሁኔታ መቀመጥ የለባቸውም። እነዚህ ጥያቄዎች አሁን ከተመለሱ ድርድሩ ምን ላይ ሊሆን ነው? ጥያቄዎቹ ከተመለሱ ድርድሩ ለምን ያስፈልጋል? የፀቡ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች የድርድሩም ጉዳዮች ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች የድርድሩን ሂደት ለማደናቀፍ በቂ ምክንያቶች ናቸው።”

ተንታኙ እንደሚሉት እነዚህ ጥያቄዎች የፖለቲካ አንድምታቸው በጣም ከፍተኛ የሆነ ቁልፍ የድርድር ሐሳቦች ናቸው። እነዚህን ሐሳቦች እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ፣ አሊያም ደግሞ ቀድሞ ላለመስማማት መወሰን የሰላም ውይይቱን ያፈርሰዋል ባይ ናቸው።

ያሬድ እንደሚሰጉት ድርድሩ በተለያዩ ምክንያቶች መጓተቱ “በሁለቱም ወገን የታጠቀ፣ በቋፍ ላይ ያለ ኃይል ስላለ ምናልባትም ከመጀመሪያው የከፋ ግጭት ልናይ እንችላለን” የሚል ፍርሃት አላቸው።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዚሁ ጉዳይ ላይ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡት የምሥራቅ አፍሪካ እና የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ተንታኙ አብዱልራህማን ሰኢድ፣ “ሁለቱም ኃይሎች ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ አረፍ አሉ እንጂ ለድርድር የሚሆን ዝግጅት አላደረጉም” ብለው ነበር።

“ጦርነቱ በአንደኛው ኃይል አሸናፊነት ስላልተቋጨ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እየበረታ የመጣውን ጫና ተከትሎ ነው ወደ ድርድር ለመግባት የወሰኑት እንጂ ወደው የገቡበት አይመስለኝም።”

አብዱልራህማን “ሁለቱም ወገኖች ለሰላም ያላቸው ዝግጁነት ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጠው ነበር።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ያሬድም በተመሳሳይ “ስጋት አለኝ” ይላሉ።

“ግን ደግሞ አይሆንምም ለማለት አልደፍርም። የትግራይ ሕዝብ በዚህ ጦርነት ምክንያት ስቃይ ውስጥ ነው ያለው። ምናልባት እንደው የቀረች ትንሽ ቀዳዳ ካለች በዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ተፅዕኖ ሁለቱ አካላት የመደራደር ዕድል ይኖራቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።”

ነገር ግን. . . ባለፉት ጥቂት ቀናት የታየው የጦርነት አታሞ ጉሰማ እና መወቃቀስ በጣም አስፈሪ ምልክቶች እንሆኑ የሚናገሩት አቶ ያሬድ። በማንኛውም ጊዜ እና ሁኔታ ወደለየለት ጦርነት የመግባት መጥፎ አጋጣሚ እንደሚኖር ይሰጋሉ።

ቢሆንም አደራዳሪዎች የሚኖራቸው ተፅዕኖን ተከትሎ ቀላልና በአጭር ጊዜ የሚያልቅ ባይሆንም፣ ለአጭር ጊዜ የታየውን ሰላም ተንተርሶ ድርድሩ ሊጀመር የሚችልበትም ዕድል እንዳለ ተስፋ ያደርጋሉ።

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ያለው ያለመተማመን ትልቁ ተግዳሮት ነው የሚሉት ደግሞ በናይሮቢ አፍሪካ ሰላም ኃላፊ፤ የናይሮቢ ዩኒቨርሲቲው ምሑር ፕሮፌሰር ፒተር ካግዋንጃ ናቸው።

ፕሮፌሰሩ የትግራይ ጦርነት በባሕሪው የተለየ ነው፤ ምክንያቱም አሁን ጦርነት ላይ ያሉት አካላት በአንድ ወቅት አጋር የነበሩ ናቸው ሲሉ ይተነትናሉ።

“ዐቢይ አሕመድ ለ30 ዓመታት ሥልጣን ላይ በነበሩ የህወሓት አመራሮች የሰለጠነ መሪ ነው። ስለዚህ ግጭቱ በመጠራጠር፣ ቀና ባልሆነ ፍላጎት እና በታጠፈ እምነት የተሞላ ነው። ሁለቱም ወገኖች በአንድ ነገር ስምምነት ላይ መድረስ የሚያስችላቸውን መተማመን ለመገንባት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል።”

የህወሓት ተዋጊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኬንያ ፖለቲካዊ ለውጥ ድርድሩ ላይ የሚኖረው አንድምታ

ህወሓት ከፌዴራል መንግሥቱ ወታደራዊ ትንኮሳ እየደረሰብኝ ነው የሚል ወቀሳ እያሰማ ሳለ የፌደራል መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ድርድሩን እንዲያስጀምር ጠይቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ኮሚቴ ውይይቱ ንግግሩ በፍጥነት እንዲጀምር ከአፍሪካ ሕብረት ጋር እየሠራሁ ነው ይላል።

ህወሓት የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሌሴጉን ኦባሳንጆ ላይ እምነት የለንም ይላል፤ በምትኩ የናይሮቢ መንግሥት እንዲያሸማግለው ይፈልጋል።

የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ “ኦባሳንጆ ላይ እንደ ሰው ምንም ችግር የለብንም፤ አዎንታዊ ሚና ቢጫወቱ ደስ ይለናል። ግን ፍኖተ ካርታ የላቸውም” ሲሉ ተናግረው ነበር።

ኬንያ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት አባል በመሆኗ ግጭቱን ለመፍታት ትልቅ ሚና እንዲኖራት አድርጓታል ይላሉ ፕሮፌሰር ፒተር ካግዋንጃ።

“ጦርነቱ እንደተጀመረ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መጀመሪያ ያቀኑት ወደ ኬንያ ነበር። ከዚያ በኋላም በተደጋጋሚ ልዑካን እየመጡ ሁኔታውን ሲያስረዱ ቆይተዋል። ኬንያ ለጦርነቱ አዲስ አይደለችም።”

ፕሮፌሰር ፒተር እንደሚሉት የኡሁሩ ኬንያታ መንግሥት ከአፍሪካ አገራት እና ከምዕራባዊያን ጋር ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ አቅም ፈጥሯል።

“ኬንያታ፤ በቡሩንዲ የነበረውን የሰላም ድርድር በመምራት፣ በኮንጎ ውስጥ በነበረው የሰላም ሂደትም ተሳትፎ በማድረግ አገሪቱ ምርጫ እንድታካሂድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል” ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ ሁለቱም ወገኖች ኬንያ ላይ እምነት ስላላቸውና ኬንያታም ሆኑ ተመራጩ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት መልካም ስለሆነ ናይሮቢ ድርድሩን የማስተናገድ አቅም እንዳላት ለቢቢሲ ይናገራሉ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ያሬድ በበኩላቸው ኬንያ ምርጫ ከማድረጓ በፊት በዚህ ጦርነት ውስጥ የነበራት ሚና እንደ አገር ነው ወይስ የኡሁሩ ኬንያታ [ተሰናባቹ ፕሬዝደንት] የግል ጥረት ነው? የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ነው ባይ ናቸው።

“ምዕራባዊያን አገራት በዚህ በግጭቱ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ናይሮቢ ጎራ ሳይሉ አያልፉም። ምዕራባዊያኑ በተለይ አሜሪካ፣ ኬንያ በዚህ በቀጣናው በአንፃራዊነት የተረጋጋ ሰላም ስላላት ወደዚህ ወደ ድርድሩ ስበው ያመጧት ይመስለኛል።”

ኬንያ እንደ አገር ከሆነ ይህን ሚና ስታጫወት የነበረው፤ ጥረቱ በአዲሱም ፕሬዝደንት ሊቀጥል ይችላል የሚል ግምት አላቸው።

ፕሮፌሰር ፒተር ደግሞ ኬንያ አዲስ ፕሬዝደንት መምረጧ “በእኔ እምነት የሚቀይረው ነገር የለም” ይላሉ።

ያሬድ በበኩላቸው ህወሓት አዲስ የመጡትን ሰው እንዴት ነው የሚያያቸው የሚለው ወሳኝ ነው ሲሉ ይተነትናሉ።

“ግን ደግሞ ህወሓት ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአዲሱ ፕሬዝደንት ጋር ያላቸው ግንኙነት ወሳኝ ነው። ነገር ግን ህወሓት አዲሱ ፕሬዝደንት በጦርነት ወቅት ምን ብለዋል? ለአንደኛው ወገን አድልተዋል ወይ? ብለው ሊያጠኑ ይችላሉ።”

ፕሮፌሰር ፒተር፤ ላለፉት 10 ዓመታት የኡሁሩ ኬንያታ ምክትል ሆነው ያገለገሉት ተመራጩ ፕሬዝደንት የውጭ ጉዳይ ለውጥ ያደርጋሉ የሚል ግምት የላቸውም።

ነገር ግን ዊሊያም ሩቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቅርብ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ኬንያ አደራዳሪ ልትሆን እንደምትችል ይገምታሉ።

ፕሮፌሰሩ የኬንያ ምርጫ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አምርቶ ድጋሚ ምርጫ የሚደረግ ከሆነ የሰላም ድርድሩ ሊጓተት እንደሚችል ይጠረጥራሉ።