ቻይና በአንድ ወር 60 ሺህ ሰዎች ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ማለፉን አስታወቀች

ቻይና

የፎቶው ባለመብት, WU HAO/EPA-EFE/REX/SHUTTERSTOCK

ቻይና በአራት ሳምንታት ብቻ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ 60 ሺህ ሞት መመዝገቧን ይፋ አደረገች።

ቻይና ያመነችው ይህ ከፍተኛ የሞት ቁጥር የተመዘገበው ጥብቅ የኮቪድ-19 ክልከላዎችን ካነሳች በኋላ ባሉት ሳምንታት ነው።

የበሸታው መነሻ መሆኗ የምትታመነው ቻይና በኮቪድ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎችን ትክክለኛ አሃዝ ይፋ አታደርግም ተብላ በምዕራባውያን ትወቀሳለች።

ቤይጂንግ ግን በበሽታው የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን በተመለከተ የምታወጣው አሃዝ ትክክለኛ መሆኑን ስትገልጽ ቆይታለች።

ቻይና ታኅሣሥ ወር ውስጥ 59 ሺህ 938 ከኮቪድ ጋር የተያያዘ ሞት መመዝገቧን ይፋ አድርጋለች።

ከሟቾቹ መካከል አብዛኛዎቹ ከ80 ዓመት በላይ የሆነችው እና የቀደመ የጤና ቀውስ ያለባቸው ናቸው ተብሏል።

5 ሺህ 503 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ባጋጠመ የመተንፈስ ችግር ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን 54 ሺህ 435 ሰዎች ደግሞ የኮቪድ ሕመም ከዚህ ቀደም ከነበረባቸው በሽታ ጋር ተደራርቦ ሞት አስከትሎባቸዋል ብለዋል የቻይና የጤና ባለስልጣናት።

ይህ የሞት መጠን የተመዘገበው በጤና ተቋማት ብቻ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር አሃዝ ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

ቻይና ከጥቂት ሳምንታት በፊት በቫይረሱ ሕይወታቸውን ያጡ ብላ የምትፈርጀው በኮቪድ-19 ምክንያት የመተንፈሻ ስርዓታቸው መስራት በማቆሙ ሕይወታቸው ያለፈውን ብቻ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ግን ይህ አመዳደብ “እጅግ ጠባብ” ሲል ተቃውሞታል።

የቻይና የጤና ባለስልጣናት በተለይ በአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች በሚያደርጉት የኮቪድ ክትትል እና ቁጥጥር እንዲሁም የበሽታው ስርጭት ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።