ተጨማሪ ምስጢራዊ ሰነድ በባይደን መኖሪያ ቤት መገኘቱን ዋይት ሃውስ አስታወቀ

ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አገራዊ ምስጢር የያዘ ባለ አምስት ገጽ ስነድ ዴልዌር በሚገኘው የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የግል መኖሪያ ቤት መገኘቱን ዋይት ሃውስ አስታወቀ።

የፕሬዝዳንቱ ጠበቃ ሪቻርድ ሱበር ተጨማሪ ሰነዱ እንደተገኘ በፍጥነት ለፍትሕ ቢሮ ማስረከባቸውን አስታውቀዋል።

ጠበቃው ባይደን በኦባማ አስተዳደር ወቅት ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሉ የነበሩ ሰነዶች ናቸው ብለዋል።

በባይደን መኖሪያ ቤት አገራዊ ምስጢር የያዙ ሰነዶች መገኘታቸውን ተከትሎ ምስጢራዊ ሰነድ አያያዛቸውን በተመለከተ ምርመራ የሚያደርግባቸው ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሟል።

ፖለቲከኞቹ ፕሬዝዳንቱ ሆነ ብለው ምስጢራዊ ሰነዶችን በተገቢው መንገድ አልያዙም በማለት እያበጠለጠሏቸው ይገኛሉ።

በተመሳሳይ በቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መኖሪያ ቤትም አገራዊ ምስጢር የያዙ ሰነዶች መገኘታቸውን ተከትሎ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ ይታወቃል።

ትራምፕ ምርመራ የተጀመረባቸው ‘ከባድ ምስጢር’ ያሉትን ጨምሮ ከ300 በላይ ሰነዶች ፍሎሪዳ በሚገኘው ማር-አ-ላጎ መኖሪያ ቤታቸው ከተገኙ በኋላ ነው። ሰነዶቹን የፌደራል ቢሮ መርማሪ ፖሊስ ድንገተኛ ፍተሻ ካደረገ በኋላ ያገኛቸው ናቸው።

በባይደን መኖሪያ ቤት ምስጢራዊ ሰነድ ሲገኝ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ እና ከጥቂት ሳምንታት በፊት በባይደን መስሪያ ቤቶች እና በግል መኖሪያ መኪና ማቆያቸው ውስጥ ሰነዶች ተገኝተው ነበር።

ሰነዶቹ በፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ቤት መገኘታቸው የፖለቲካ ኪሳራ እንደሚያስከትልባቸው ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።

በአሜሪካ ሕግ ‘ጥብቅ የአገር ምስጢር’ የተደረጉ ሰነዶች መቀመጥ የሚችሉት በፌዴራል ቤተ-መዘክር ውስጥ ብቻ ነው።

የባይደን ጠበቃ የፕሬዝዳንቱን ምስጢራዊ ሰነድ አያያዝን በተመለከተ እንዲመረምር ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር ዋይት ሃውስ ተባባሪ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በፕሬዝዳት ጆ ባይደን መኖሪያ ቤት ምስጢራዊ ሰነዶች መገኘታቸውን ተከትሎ የፕሬዝዳንቱ ጎብኝዎችን ዝርዝር የያዘው መዝገብ ምርመራ እንዲደረግ የባይደን ተቀናቃኞች እየጠየቁ ነው።

ሪፐብሊካኑ የምክር ቤት አባላት በባይደን መኖሪያ ቤቶች በአንዱ የተገኘው ሰነድ "ብሔራዊ የደኅንነት አደጋ" ነው ሲሉ የጎብኝዎች ስምና ማንነት የሚሰፍርበት መዝገብ ይፋ እንዲሆን ጠይቀዋል።

ዋይት ሃውስ ግን ይህ የሪፓብሊካኑ ጥያቄ ምላሽ ያገኝ እንደሆነ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።