የሁቲ አማጽያን በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለተኛውን የቀይ ባህር የጭነት መርከብ አሰጠሙ

ኤተርኒቲ ሲ መርከብ ሲሰጥም የሚያሳይ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የየመን ሁቲዎች በጉዞ ላይ የነበረ የጭነት መርከብ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ እና መርከቡ ቀይ ባህር ውስጥ ከሰጠመ በኋላ ስድስት መርከበኞች መትረፋቸውን እና ቢያንስ ሦስት ሌሎች ሰዎች መሞታቸውን የአውሮፓ የባህር ኃይል ተልዕኮ አስታወቀ።

የላይቤሪያን ባንዲራ የሚያውለበልበው እና በግሪክ የሚንቀሳቀሰው 'ኤተርኒቲ ሲ' የተባለው የጭነት መርከብ 25 ሠራተኞችን ይዞ እየተጓዘ ነበር።

መርከቡ ሰኞ ዕለት ከትንሽ ጀልባዎች በተተኮሱ የሮኬት ቦምቦች ከተመታ በኋላ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በዚህም የመንቀሳቀስ አቅሙን እንዳጣ የእንግሊዝ የባሕር ንግድ ሥራዎች ኤጀንሲ (UKMTO) ገልጿል።

ጥቃቱ ማክሰኞ ዕለትም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን መርከበኞቹን የማዳን ሥራ የተጀመረው ሌሊት ላይ ነው።

በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች፤ ኤተርኒቲ ሲ ላይ ጥቃት የፈጸሙት ወደ እስራኤል እየተጓዘ ስለነበረ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ቁጥራቸው ያልታወቀ ሠራተኞችንም "ደህንነቱ ወደ የተጠበቀ ቦታ" እንደወሰዱ ተናግረዋል።

በየመን የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሁቲዎች "በሕይወት የተረፉ የቡድን አባላትን አፍነው መውሰዳቸውን" ገልጾ፤ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርቧል።

የፊሊፒንስ ባለስልጣናት ከቡድኑ አባላት ውስጥ 21 ያህሉ ዜጎቻቸው እንደሆኑ ተናግረዋል።

ከቀሪዎቹ መካከል አንዱ የሩስያ ዜግነት ያለው እንደሆነ እና በጥቃቱ በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት እግሩን እንዳጣም ተገልጿል።

ሁቲዎች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይህንን ዓይነቱን ጥቃት ሲፈጽሙ ይህ ሁለተኛቸው ነው።

አማጺ ቡድኑ እሁድ ዕለት 'ማሲክ ሲስ' በተባለ ሌላ የላይቤሪያን ባንዲራ የሚያውለበልብ የግሪክ የጭነት መርከብ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

የእሁዱን ጥቃት የፈጸሙት መርከቡ፤ "በተወረረው የፍልስጤም ግዛት ውስጥ በሚገኙ ወደቦች ላይ የተጣለውን የጉዞ ክልከላ የጣሰ ኩባንያ ንብረት በመሆኑ" ነው ብለዋል።

ሁቲዎች ማክሰኞ ዕለት የለቀቁት ቪድዮ፤ የታጠቁ ሰዎች መርከቡን ሲሳፈሩ እና መርከቡ እንሰጥም ያደረጉትን ተከታታይ ፍንዳታዎች ሲፈጽሙ አሳይቷል። በማጂክ ሲስ ላይ የነበሩት 22ቱ መርከበኞች በአካባቢው ሲያልፍ ነነበረ የንግድ መርከብ አማካኝነት ተርፈዋል።

እ.አ.አ ከኅዳር 2023 ጀምሮ ሁቲዎች በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ ሲጓዙ የነበሩ 70 ገደማ የንግድ መርከቦችን፤ በሚሳኤል፣ በድሮኖች እና በትንሽ ጀልባዎች የተሰነዘሩ ጥቃቶች ዒላማ አድርገዋል።

አሁን ደግሞ አራት መርከቦችን አሰጥመዋል፣ አምስተኛውን መርከብ አግተዋል፣ ቢያንስ ሰባት መርከበኞችን ገድለዋል።

ቡድኑ እነዚህ ድርጊቶች የሚፈጽመው ጋዛ ውስጥ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በሚደረገው ጦርነት ውስጥ ለፍልስጤማውያንን ያለውን ድጋፍ ለማሳየት እንደሆነ ይገልጻል።

ቡድኑ ዒላማ የሚያደርገው ከእስራኤል፣ ከአሜሪካ ወይም ከእንግሊዝ ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች እንደሆነ ብዙ ጊዜ ይናገራል።

እነዚህን የሁቲ ጥቃቶች ተከትሎ አገራቱ የመን ላይ የአየር ድብደባዎችን ፈጽመዋል።

መንሳፈፊያ የለበሰ ግለሰብ ውሃ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Diaplous/Handout via Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ረቡዕ ዕለት በቀይ ባህር የሚገኘው እና 'ኦፕሬሽን አስፓይድስ' የተባለው የአውሮፓ ኅብረት የባህር ኃይል ተልዕኮ፤ በኤተርኒቲ ሲ ላይ ለተፈፀመው ጥቃት እየተሰጠ ባለው ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ሥራ ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ገልጿል።

ተልዕኮው፤ "በአሁኑ ሰዓት ባህር ውስጥ ሲንሳፈፉ የነበሩ ስድስት መርከበኞችን መታደግ እንደተቻለ" ጠቅሷል።

አንድ የአስፓይድስ ባለስልጣን፤ ከተረፉት መርከበኞች ውስጥ አምስቱ ፊሊፒናውያን፤ አንዱ ደግሞ ሕንዳዊ እንደሆኑ፤ እንዲሁም ሌሎች 19 ሰዎች አሁንም እንዳልተገኙ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

በግሪክ የሚገኝ ዲያፕሎስ የተባለ የባህር ላይ ደህንነት ድርጅት ረቡዕ ዕለት የለቀቀው አንድ ቪድዮ ቢያንስ አምስት ሰዎችን ለማዳን የተደረገውን ጥረት ያሳየ ሲሆን ለነፍስ አድን ስራው ከ24 ሰዓት በላይ በውሃ ላይ ማሳለፉን እንደገለጸ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ዲያፕሎስ፤ "የቀሩትን መርከበኞች ለማግኘት የምናደርገውን ፍለጋ እስከመጨረሻዋ ብርሃን ድረስ እንቀጥላለን" ብሏል።

በተጨማሪም ሮይተርስ፤ የባህር ላይ ደህንነት ኩባንያዎችን በመጥቀስ የሟቾች ቁጥር አራት መሆኑን ዘግቧል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማጂክ ሲስ እና በኤተርኒቲ ሲ መርከቦች ላይ የተፈፀሙትን ጥቃቶች አውግዟል።

ጥቃቶቹ "በኢራን የሚደገፉ የሁቲ አማጽያን በመርከብ ነጻነት እንዲሁም በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ እና የባህር ደህንነት ላይ የደቀኑትን ቀጣይነት ያለው አደጋ ያሳያል" ብሏል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ "አሜሪካ ግልጽ ሆና ቆይታለች፤ የመርከብ እና የንግድ መርከቦችን ነጻነት ከሁቲ የሽብር ጥቃቶች ለመጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዳችንን እንቀጥላለን፤ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት [እነዚህ ጥቃቶች] ሊኮንኑ ይገባል" ሲል አቋሙን አሳውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር የአገሪቱ አየር ኃይል ከየመን የተተኮሰን ሚሳኤል ማክሸፉን ሐሙስ ዕለት ገልጿል።

ሁቲዎች በዓለም አቀፍ መርከብ ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ ለሰባት ሳምንታት በየመን ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ግንቦት ላይ ከዋሽንግተን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ፈጽመው ነበር።

ይሁን እንጂ ስምምነቱ፤ በየመን ላይ በርካታ የመልሶ ማጥቃት ጥቃቶችን በፈጸመችው በእስራኤል ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ማቆምን እንደማይጨምር ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ የባሕር ድርጅት ዋና ፀሀፊ፤ ሰሞነኛዎቹን ተከታታይ ጥቃቶች ተከትሎ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እንዲያጠናከሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ዋና ፀሀፊው አርሴኒዮ ዶሚንጌ፤ "ከበርካታ ወራት መረጋጋት በኋላ በቀይ ባህር ላይ የሚፈፀሙ አሳዛኝ ጥቃቶች ዳግም መጀመራቸው የዓለም አቀፍ ህግ እና የመርከብ ነጻነትን በድጋሚ የጣሰ ተግባር ነው" ብለዋል።

"የእነዚህ ጥቃቶች እና የሚፈጥሩት ብክለት ዋነኛ ሰለባዎች ንጹኅን መርከበኞች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።