በየመን የስደኞች ማቆያ ላይ አሜሪካ በፈጸመችው ጥቃት የተገደሉት ሦስቱ ኢትዮጵያውያን የአንድ ቤተሰብ አባላት

ጽሩይ፣ ሕይወት እና መዓርግ
የምስሉ መግለጫ, ጽሩይ፣ ሕይወት እና መዓርግ (ከግራ ወደ ቀኝ)

በቀይ ባሕር ላይ የሚንቀሳቀሱ የምዕራባውያን የንግድ መርከቦች ላይ በሚፈጽሙት ጥቃት ምክንያት በምዕራባውያን የጦር አውሮፕላን ጥቃት እየተፈጸመባት ባለችው የመን ውስጥ ባለፈው ሳምንት በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ስደተኞች ተገድለዋል።

ምዕራባውያኑ የመርከቦቻቸውን ደኅንነት አደጋ ላይ የጣሉትን የየመን ሁቲ ታጣቂዎችን ወታደራዊ እና የኢኮኖሚ ተቋማትን ዒላማ ማድረጋቸውን ሲናገሩ ቆይተዋል። በቅርቡ የተፈጸመው ጥቃት ግን ስደተኞች ተጠልልውበት የነበረ ቦታ መሆኑን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ኢትዮጵያውያን ለስደት መሸጋገሪያነት ከሚመርጧቸው አገራት መካከል አንዷ የሆነችው የመን ውስጥ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም. ማለዳ ላይ የፈጸሙት ጥቃት ስደተኞች ተይዘውበት በነበረ ማቆያ ላይ መሆኑን የየመን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

በጥቃቱ ቢያንስ 68 ሰዎች መገደላቸውን እና ተጨማሪ አብዛኞቹ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው 47 ሰዎች መቁሰላቻውን አል ማሲራህ የተባለው የሁቲ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

ሳዓዳ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ማዕከል ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሞቱት እና የቆሰሉት ሰዎች አፍሪካውያን ስደተኞች ከመሆናቸው ውጪ በትክክል ከየትኞቹ አገራት የመጡ እንደሆኑ የታወቀ ነገር ባይኖርም፤ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ቢቢሲ የመን ውስጥ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አረጋግጧል።

ጥቃቱን ተከትሎ ሮይተርስ በጥቃቱ ከተገደሉት በተጨማሪ አንድ በጥቃቱ ቆሰሎ የተረፈ ኢትዮጵያዊ "እናቴ" እያለ በአማርኛ ሲጣራ መሰማቱን ዘግቧል። ቢቢሲ ያናገራቸው ኢትዮጵያውን እንደሚሉት በጥቃቱ ከተገደሉት እና ከቆሰሉት በርካቶቹ አንዳንዶቹም ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ያምናሉ።

በጥቃቱ ከተገደሉት ኢትዮጵያውያን መካከልም ሦስት የአጎት እና የአክስት ልጆች በአንድ ላይ ሕይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ ከቤተሰቦቻቸው ለመረዳት ችሏል።

'አትጨነቁ ደኅና ነን'

ጽሩይ፣ ሕይወት እና ማዕረግ በተለያዩ ጊዜያት ከሰሜን ኢትዮጵያዋ ክልል ትግራይ የጽራእ ወምበርታ ወረዳ ኢራ ከሚባል ጎጥ ተነስተው ለስደት ወደ የመን ያቀኑት በረሃ እና ባሕር አቋርጠው ነበር።

እነዚህ ሦስት ወጣቶች በፈታኝ ጉዞ ቀይ ባሕርን ተሻግረው የመን ከገቡ በኋላ ራጎ በሚባል አካባቢ ለረዥም ጊዜ ቆይተዋል። ከዚያም ሕገወጥ ስደተኞች ተብለው ተይዘው ለአራት ወራት በእስር ቆይተዋል።

ረዥሙን የእስር ጊዜያቸውን ካሳለፉበት እስር ቤት ጥቃቱ ወደ ተፈጸመባት የሰአዳ ማቆያ ውስጥ ከገቡት ከጥቃቱ ሁለት ሳምንታት በፊት ነው።

በየመን ከታሰሩ በኋላ አልፎ አልፎ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ቤተሰቦቻቸው እና በተለይም በሳዑዲ አረቢያ ከሚገኙ እህቶቻቸው ጋር በስልክ ይገናኙ እንደነበር አምለሰት ምሩጽ የተባለች የቅርብ ዘመዳቸው ለቢቢሲ ተናግራለች።

በዚህ ወቅት በሳዑዲ አረቢያ የምትገኘው አምለሰት "በእርግጥ በእስር ቤት ውስጥ ስልክ በቀላሉ አያገኙም ነበር። ነገር ግን አልፎ አልፎ እዚህ ሳዑዲ ውስጥ ከሚገኙ እህቶቻቸው ጋር ይገናኙ ነበር። 'አትጨነቁ፤ ደህና ነን' ይላሉ" ትላለች።

በሳዑዲ የሚገኙ የሟቾቹ እህቶች ሲሆኑ፣ በስልክ ሲያገኟቸው "[በየመን] በመንግሥት እጅ ስላለን አትጨነቁ፤ እዚህ እስር ቤት ውስጥ ደህና ነን" ይሏቸው ነበር።

በጥቃቱ ቆስለው ሆስፒታል ከገቡት መካከል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በጥቃቱ 47 ሰዎች መቁሰላቸውን የየመን ሁቲ ባለሥልጣናት ተናግረዋል

የጥቃቱ ዋዜማ . . .

በአገሪቱ ኃይሎች ተይዘው በእስር ወራትን ያሳለፉት ሦስቱ ወጣቶች የመን ውስጥ ስላለው የደኅንነት ሁኔታ ምንም ዓይነት መረጃም ሆነ እውቀት እንዳልነበራቸው እህታቸው አምለሰት ትናገራለች።

ጥቃቱ በተፈፀመበት ቀን ዋዜማ ሳዑዲ አረቢያ ከሚገኙ እህቶቻቸው ጋር ቀደም ብለው በስልክ ተገናኝተው ስለሌላ ጉዳይ አውርተዋል። በመጨረሻም እንደለመዱት "ደኅና ሁኑ፤ ደኅና ሰንብቱ" ተባብለው ነበር የተለያዩት።

"እሁድ ምሽት በስልክ ሲገናኙ ጥሩ ሲጨዋወቱና ሲሳሳቁ አመሹ። ተቸግረው እንደሆን ጠይቄያቸው 'በመንግሥት እጅ ስላለን ምን እንሆናለን? ስለ እኛ አትጨነቁ' ይሉ ነበር። ከስልክ ግንኙነቱ በኋላ ሰኞ ማለዳ ላይ ጥቃቱ ተፈጸመ" ትላለች።

ትግራይ ውስጥ ካሉ ወላጆቻቸው ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙበት በፋሲካ በዓል ዋዜማ ነበር። እህቶቻቸው ከስልክ ወደ ስልክ በማገናኘት "እንኳን አደረሳችሁ፤ እኛ ደኅና ነን" የሚል መልዕክት ለቤተሰቦቻቸው እንዲያሰሙ አገዘዋቸው ነበር።

ከዚያ በኋላ አሜሪካ በሁቲ ቁጥጥር ሥር በሚገኘው ሰሜን ምዕራብ የየመን ክፍል ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ከሞቱት 68 ስደተኞች መካከል ሦስቱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ይገኙበታል።

የሁቲ ባለሥልጣናት በወቅቱ እንደተናገሩት ቢያንስ 68 አፍሪካውያን ስደተኞች በጥቃቱ መገደላቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች ግን ቁጥሩን ከ100 በላይ ያደርሱታል።

አብዱልራህማን ያሲን የተባለ ዓይን እማኝ ለቢቢሲ እንደተናገረው በጥቃቱ የሞቱት እና የቆሰሉት "በሙሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው ማለት ይቻላል" ሲል በስደተኛ መቆያው ውስጥ የነበሩት ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ገልጿል።

የፈራረሰ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ስደተኞቹ የነበሩበት ቦታ ከጥቃቱ በኋላ

መራራ የቤተሰብ ሐዘን

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጥቃቱ የተገደሉት ሦስት ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነው የጽሩይ ታላቅ ወንድም የሚገኘው የመን ውስጥ በመሆኑ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የዘመዶቻቸውን አስከሬን ለማግኘት እና ለመለየት ሞክረዋል። በዚህም ሦስቱ ወጣቶች ጥቃቱን ተከትሎ ወዲያውኑ ነበር ሕይወታቸው ያለፈው።

"ሦስቱም ወጣቶች ወንድማማቾች ናቸው። በአንድ ጊዜ የሦስቱም ሞት መርዶ ለቤተሰብ ሲነገር ሁኔታው ከባድ ነበር። ማን ማንን እንደሚያጽናና ከባድ ሆኗል። ሁሉም በሐዘኑ ክፉኛ ነው የተጎዳው" ትላለች አምለሰት።

ከሁሉ ከባዱ ጉዳይ ደግሞ እስካሁን አስከሬናቸውን ወደ አገር ቤት መላክ እንዳልተቻለ በመጥቀስ "እዚያው ይቀበሩ ወይስ ወደ አገር ቤት ይላካሉ የሚለው ግልጽ አይደለም" በተጨማሪም ወደ ቤተሰባቸው ይመለስ ቢባል እንኳን ማጓጓዣው እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል።

አምለሰት ከወንድሞቿ ሞት ባሻገር የሌሎችን ወጣቶች ስቃይና ሞት ለማስቆም አንድ ነገር መደረግ እንዳከበት ታምናለች።

"በአሁኑ ጊዜ በደላሎች እየተታለሉ እና እየተገደዱ እየተሰደዱ ያሉ ብዙ ናቸው፤ ባሕር ተሻግረው ወደ ሳዑዲ አረቢያ መግባት ፍላጎታቸው ቢሆንም መንገድ ላይ እየቀሩ ነው። ስለዚህ ይብቃ መባል አለበት። በአገሪቱ ያሉ ደላሎች ሕዝብ እና መንግሥት ለፍርድ ሊያቀርባቸው ይገባል።"

በአስቸጋሪ እና በአደገኛ ሁኔታ በረሃ እና ባሕርን አቋርጠው የመን ከገቡ ከስምንት ወር እስከ ሦስት ዓመት የሆናቸው የአንድ ቤተሰብ አባላቱ ጽሩይ፣ ሕይወት እና ማዕረግ በሁቲ ፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ለሞት ካባቃቸው እስር ቤት ገመግባታቸው በፊት ከቀን ሥራ እና ሳዑዲ ያሉት እህቶቻቸው በሚልኩላቸው ገንዘብ ነበር ኑሯቸውን የሚመሩት።

ለእራሳቸው እና ለቤተሰባቸው መልካም ሕይወት ሲሉ የመን የገቡት ሦስቱ ወጣቶች መዳራሻቸው የነበረችው ከየመን ሁቲዎች ጋር ፍጥጫ ውስጥ ወዳለችው ሳዑዲ አረቢያ ነበር።

"እንዲሰደዱ ያስገደዳቸው በትግራይ ያለው ሁኔታ ነው። ከየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር ሲሞክሩ ድንበር ጠባቂዎቹ ሊያሳልፏቸው አልቻሉም። ወደ አገራቸው እንዳይመለሱም የሚጠብቃቸው ባሕር ነው። በዚህ ምክንያት የመን ለመቆየት ተገደዱ" ትላለች አምለሰት።

በገጠር የሚገኙትን አርሶ አደር ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ከአገራቸው የተሰደዱት ወጣቶቹ ወደ ሳዑዲ አረቢያ መሻገር ሳይቀናቸው ወይም ወደ አገራቸው ሳይመለሱ እየተንከራተቱ ባለበት ጊዜ በየመን የፀጥታ ኃይሎች ሕገወጥ ስደተኞች ተብለው ለእስር ተዳረጉ።

በእስር ላይ ሳሉም ባላሰቡት እና ባልጠበቁት ሁኔታ በእስር ቤቱ ላይ በተፈጸመው የአየር ጥቃት እንደወጡ ቀሩ።