ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ የሁቲ አማፂያን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ልታቆም ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በየመን የሁቲ አማፂያን ላይ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባ ልታቆም መሆኑን ገለፁ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት የሁቲ አማፂያን "ጥቃት መፈፀም በማቆማቸው" መሆኑን ተናግረዋል።
ኦማን በበኩሏ በኢራን በሚደገፉት አማፂያን በቀይ ባሕር ላይ በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ላለመፈጸም መስማማታቸውን አስታውቃለች።
ዶናልድ ትራምፕ ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በዋሺንግተን በተገናኙበት ወቅት "[ሁቲዎች] መዋጋት አይፍልጉም፤ እኛ ደግሞ ያንን እናከብራለን፤ እናም የአየር ድብደባ ማካሄዳችንን እናቆማለን፤ ስለዚህ እነሱም ጥቃት ማድረሳቸውን አቁመዋል" ብለዋል።
የኦማን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሁለቱም ወገኖች አንደኛቸው ሌላኛቸው ላይ ጥቃት ላለመሰንዘር መስማማታቸውን ገልጸዋል።
"በባሕሩ ላይ በሰላም የመቅዘፍ ነጻነትን ለማረጋገጥ እና የዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች ፍሰት የተሳለጠ እንዲሆን" ስምምነት መደረጉን የዶናልድ ትራምፕ ንግግርን ተከትሎ የኦማን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ላይ ለጥፏል።
ሁቲዎች እስካሁን ድረስ ተደረሰ ስለተባለው ስምምነት ያሉት ነገር የለም።
በመጋቢት ወር አሜሪካ በሁቲዎች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላ፣ በየመን 1,000 ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የመከላከያ ኃይሉ አስታውቋል።
ዶናልድ ትራምፕ ከኦቫል ኦፊስ እንደተናገሩት "ሁቲዎች ከአሁን በኋላ መርከቦች ላይ አይተኩሱም"
"ሁቲዎች እንዳስታወቁት፣ ወይንም ቢያንስ ለእኛ እንደገለፁልን፣ ከአሁን በኋላ አይዋጉም. . . ነገር ግን የበለጠ ጠቃሚው ነገር ቃላቸውን አምነን መቀበላችን ነው።"
የኦማን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አል ቡሳይዲ ውጥረቶች እንዲረግቡ አገራቸው ማሸማገሏን ተናግረዋል።
"ወደፊት ሁለቱም ወገኖች አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ጥቃት አይፈጽሙም፤ በቀይ ባሕርም ሆነ በባብ አል መንደብ የአሜሪካ መርከቦቸን ጨምሮ ሌሎች የዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች በነጻነት እንዲቀዝፉ እንዲሁም የተሳለጠ ፍሰትን ለመረጋገጥ ተስማምተዋል" ብለዋል።
ሁቲዎች በቀይ ባህር ላይ የሚቀዝፉ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸም የጀመሩት እ.አ.አ ከጥቅምት 2023 ጀምሮ የእስራኤል መከላከያ ኃይል በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ በፍልስጤማውያን ላይ መክፈቱን ተከትሎ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት በሚል ነው።
በንግድ መርከቦች ላይ በርካታ ሚሳዔሎችን ያስወነጨፉት እና የድሮን ጥቃት የፈጸሙት ሁቲዎች ሁለት መርከቦችን ሲያሰምጡ ሦስተኛውን በቁጥጥር ስር አውለው አራት የመርከቡን ሠራተኞች ገድለዋል።
ጥቃቱ ትልልቅ የመርከብ ድርጅቶች 15 በመቶ የዓለም የንግድ መርከቦች ከሚተላለፉበት ቀይ ባሕር አቅጣጠጫቸውን ቀይረው ረዥም የጉዞ መስመርን እንዲመርጡ አስገድዷል።
በአሜሪካ የተመራው የባሕር ኃይል በርከታ የሁቲ ጥቃቶችን ያከሸፈ ሲሆን በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የተጀመረው የአየር ጥቃት በዶናልድ ትራምፕ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ባለፈው ሳምንት ሁቲዎች አሜሪካ በሰሜን ምዕራብ የመን በሚገኝ የስደተኞች ማቆያ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 68 አፍሪካዊ ስደተኞች መገደላቸውን ገልጸዋል።
ሁቲዎች ወደ እስራኤል ሚሳዔል ማስወንጨፋቸውን የቀጠሉም ሲሆን እሁድ ዕለት የእስራኤል ዋና አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናልን መምታታቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም ማክሰኞ ዕለት እስራኤል ለጥቃቱ በሰንአ የሚገኘውን የየመን ዋና አውሮፕላን ማረፊያን በማትቃት ምላሽ ሰጥታለች።
ኤኤፍፒ ባለስልጣናትን ጠቅሶ አውሮፕላን ማረፊያው በጥቃቱ "ሙሉ በሙሉ መውደሙን" ዘግቧል።
በሌላ የእስራል ጥቃት የኤሌትሪክ ኃይል ማከፋፈያ እና የሲሚኒቶ ፋብሪካ ወድሟል።
ሰኞ ዕለት እስራኤል፣ በየመን ሁዳያዳ የሚገኝ የወደብ ተቋም እና ሌላ በከተማው የሚገኝ የሲሚንቶ ፋብሪካን ደብድባለች።












