ቀጣዩ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ማን ሊሆኑ ይችላሉ? አፍሪካውያንስ አሉ?

(ከግራ ወደ ቀኝ) ካርዲናል ፒተር ኮዶዎ አፒያህ ተርክሰን፣ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፣ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ጎኪም ታግል፣ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, (ከግራ ወደ ቀኝ) ካርዲናል ፒተር ኮዶዎ አፒያህ ተርክሰን፣ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፣ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ጎኪም ታግል፣ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ

ቀጣዩ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሳነ ሊቀ ጳጳስ ማን ሊሆን ይችላል? የሚለው የሚታወቀው የካርዲናሎች ጉባዔ ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 7/2017 ዓ.ም. ድረስ በምስጢር ተሰብስቦ በሚያሳልፈው ውሳኔ ይሆናል።

ጉባዔው ሚያዝያ 29/2017 ዓ.ም. ከቀኑ 10 ሰዓት ከ30 ላይ በ15ኛው ክፈል ዘመን በተገነባው ሲስታይን ቤተ መቅደስ የሚሰበሰብ ይሆናል።

ዕድሜያቸው እስከ 80 ዓመት የሚሆን 133 ካርዲናሎች ቀጣዩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ማን ሊሆን እንደሚገባ ከተወያዩ በኋላ ይሆናል ያሉትን የሚመርጡ ሲሆን፣ ይህም አንድ ተመራጭ የካርዲናሎቹን ሁለት ሦስተኛ ድምጽ እስኪያገኝ ድረስ ይቀጥላል።

የካርዲናሎቹ ምርጫ በመላው ዓለም በሚገኙ 1.4 ቢሊዮን ተከታዮች ዘንድ እና በቤተክርስቲያኒቷ ላይ ተጽዕኗቸው የገዘፈ ነው።

በአሁኑ ምርጫ ከሚሳተፉት 80 በመቶ የሚሆኑት ካርዲናሎች የተመረጡት በሟቹ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የተሾሙ ናቸው። አብዛኞቹም ለመጀመሪያ ጊዜ ሊቀ ጳጳስ የሚመርጡ ሲሆን፣ አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ምልከታም ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በቤተ ክርስቲያኒቷ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጽ የሚሰጡት ከግማሽ ትንሽ ዘለል የሚሉት አውሮፓውያን ናቸው።

ምንም እንኳ የካርዲናሎቹ ስብስብ አብዛኛው በፓፕ ፍራንሲስ በራሳቸው የተሾሙ ቢሆንም "ተራማጅ" ወይንም "ወግ አጥባቂ" አይደሉም።

ካርዲናሎቹ አፍሪካዊ፣ እስያዊ ወይንም አሜሪካዊ አለበለዚያም የቀድሞ የቫቲካን አስተዳዳሪዎችን ይመርጡ ይሆን?

የሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን ይተካሉ ተብለው ከተገመቱ መካከል የጥቂቶቹ ስም እነሆ።

ጣልያናዊው ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን

 ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን

ዝግ ብለው በለስላሳ ድምጽ የሚናገሩት የ70 ዓመቱ ጣልያናዊ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በፖፕ ፍራንሲስ የጵጵስና ዘመን ዋና አማካሪያቸው በመሆን አገልግለዋል።

የቫቲካን ዋና ፀሐፊ በመሆን ያገለገሉት ካርዲናሉ፤ የቤተክርስቲያኒቷ ማዕከላዊ አስተዳደር የሆነው የሮማ ኩሪያ የበላይ ጠባቂም ሆነው ሠርተዋል።

ፊሊፕናዊ ካርዲናል ሊዊስ አንቶኒዮ ጎኪም ታግል

ካርዲናል ሊዊስ አንቶኒዮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ሊዊስ አንቶኒዮ

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በፊሊፒንስ ግዙፍ ተጽዕኖ አላት። የፊሊፒንስ 80 በመቶ ሕዝብ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ሲሆን፣ ቀጣዩን ሊቀ ጳጳስ ለመምረጥ በሚሰበሰቡት ካርዲናሎች ውስጥ አምስቱ ፊሊፒንናውያን ናቸው።

ይህም የ67 ዓመቱ ካርዲናል ታግል ቀጣዩ ሊቀ ጳጳስ እንዲሆኑ ከፍተኛ የሆነ ቅስቀሳ እና ማግባባት ሊደረግላቸው ያስችላል ተብሎ ተገምቷል።

አሜሪካዊ ካርዲናል ሮበርት ፕሪቮስት

ካርዲናል ሮበርት ፕሪቮስት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ሮበርት ፕሪቮስት

በአሜሪካ ቺካጎ ተወልደው ያደጉት የ69 ዓመቱ ካርዲናል ፕሪቮስት ብዙዎች ለቦታው ይመጥናሉ ሲሉ ተስፋ ጥለውባቸዋል። በፔሩ ጳጳስ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በሚሺነሪነት አገልግለዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የቫቲካን የጳጳሳት አለቃ አድርገው በመሾም ቀጣዩን የጳጳሳት ትውልድ በመምረጥ ውስጥ ቁልፍ ሥልጣን እንዲኖራቸው አድርገዋል።

ሃንጋሪያዊ ካርዲናል ፒተር ኤርዶ

ካርዲናል ፒተር ኤርዶ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ፒተር ኤርዶ

ከ51 ዓመታቸው ጀምሮ ካርዲናል በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት የ72 ዓመቱ ሃንጋሪያዊ ፒተር ኤርዶ በአውሮፓ ባለችው የካቶሊክ ቤተክርስትያን ውስጥ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው።

በአውሮፓውያኑ 2006 እንዲሁም በ2016 የአውሮፓውያን ጳጳሳት ኮንፍረንስን መርተዋል።

ፒተር በአፍሪካውያን ካርዲናሎች ዘንድ ታዋቂ ሲሆኑ፣ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከካቶሊክ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ በቅርበት የሠሩ ናቸው።

ፒተር ኮዶዎ አፒያህ ተርክሰን

ፒተር ኮዶዎ አፒያህ ተርክሰን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ፒተር ኮዶዎ አፒያህ ተርክሰን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የ76 ዓመቱ ጋናዊ ካርዲናል በጓደኞቻቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ ሲሆን፣ ከ1500 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካዊ ርዕሳነ ሊቀ ጳጳስ ይሆናሉ ሲሉ ተስፋ ጥለውባቸዋል።

ልክ እንደ ካርዲናል አምቦንጎ ሁሉ "ለቦታው ብቁ ነኝ ብዬ አላስብም" ሲሉ ለቢቢሲ በአውሮፓውያኑ 2013 ተናግረው ነበር።

በወቅቱ "ማንም ሊቀ ጳጳስ እሆናለሁ ብሎ የሚመኝ አይመስለኝም" ነበር ያሉት።

ቤተክርስቲያኒቱ በአህጉሪቱ እያደገ የመጣውን የአማኞቿን ቁጥር ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ቀጣዩ ሊቀ ጳጳስ ከአፍሪካ ይሆናል ብለው ያምኑ እንደሆን ሲጠየቁ የሊቀ ጳጳስ ምርጫው በቁጥር ላይ ተመሥርቶ እንደማይሆን ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳስ ጆን ፖል ዳግማዊ በመንበረ ጵጵስናው ላይ በነበሩበት ወቅት ካርዲናል ተደርገው ተሹመዋል።

ልክ እንደ ታግል ሁሉ ካርዲናል ተርክሰን ከዚህ በፊት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሲመረጡ፣ እርሳቸው ይሾማሉ ተብሎ ተገምቶ ነበር።

በአንድ ወቅት በሙዚቃ ባንድ ውስጥ ጊታር ይጫወቱ የነበሩት ካርዲናል ተርክሰን፤ በኃይል በተሞላው አቀራረባቸው ይታወቃሉ።

ልክ እንደ ሌሎች አፍሪካዊ ካርዲናሎች አክራሪ ወግ አጥባቂ ባይሆኑም፣ ተርክሰን በጋና እንዲሁም በሌሎች አፍሪካ አገሮች የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ተቃውመዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2023 ጋና ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ላይ ከባድ ቅጣት ለመጣል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ በሚነጋገርበት ወቅት የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት እንደ ወንጀል መቆጠር የለበትም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአውሮፓውያኑ 2012 በቫቲካን በተካሄደ የጳጳሳት ጉባኤ ላይ በአውሮፓ የእስልምና መስፋፋትን በመጥቀስ ፍርሃት የሚነዛ ንግግር አድርገዋል ተብለው የተወቀሱት ተርክሰን በኋላ ላይ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ

ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ

የ65 ዓመቱ ኮንጓዊ ካርዲናል አምቦንጎ ቀጣዩ ሊቀጳጳስ ከአፍሪካ ይሁን ከተባለ ቀዳሚ ተፎካካሪ ይሆናሉ።

ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተገኙት ካርዲናሉ በሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ካርዲናል ሆነው ከመሾማቸው በፊት ለሰባት ዓመታት ያህል በኪንሻሳ በጵጵስና አገልግለዋል።

ወግ አጥባቂ የሆኑት ካርዲናል አምቦንጎ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ጋብቻ መባረክን "የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ሕብረት ከባሕል ጋር የሚጻረር እና በመሠረታዊነት ሃጥያት ነው" ሲሉ ተቃውመዋል።

በኮንጎ ክርስትና ዋና ሃይማኖት ቢሆንም፣ ከታጣቂዎች ጋር ግንኙነት ባላቸው አክራሪ እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ክርስቲያኖች እስራት እና ሞት ይገጥማቸዋል።

ይኹን አንጂ ካርዲናል አምቦንጎ ለቤተክርስቲያኒቷ ወገባቸውን አጥብቀው ተከራካሪ ናቸው።

በ2020 በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ቤተክርስቲያኒቷ ሁሉን እንደ የመልኩ እና እንደ አመጣጡ የምታስተናግድ መሆኗን ሲናገሩ "ፕሮቴስታንቶችም ፕሮቴስታንት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሙስሊሞችም ሙስሊም ይሁኑ። ከእነሱ ጋር አብረን እንሠራለን። ሁሉም የራሱን ማንነት ይዞ መቀጠል አለበት" ብለዋል።

እንዲህ ዓይነት አስተያየት የካቶሊክ ምዕመናን እና አገልጋዮች የቤተክርስቲያኒቱን ቃል ለመላው ዓለም ማሠራጨት አለባቸው የሚለውን በማንሳት ለተወሰኑ ካርዲናሎች ተልዕኳቸውን በሚገባ ተረድተው ይሆን ሲሉ እንዲጠይቁ ሊያደርጋቸው ይችላል።

ካርዲናል ሮበርት ሳራህ

ካርዲናል ሮበርት ሳራህ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ሮበርት ሳራህ

የ79 ዓመቱ ጊኒያዊ ሮበርት ሳራህ በቤተክርስትያኒቱ ውስጥ በወግ አጥባቂነታቸው ነው የሚታወቁት።

ካርዲናል ሳራህ ቀኖና እና ዶግማ እንዲሁም ባሕላዊ አስተምሮ አጥብቀው የሚደግፉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የነበራቸውን የለውጥ ፈላጊነት ዝንባሌ በመቃወም የሚታወቁ ናቸው።

የፍራፍሬ ለቃሚ ልጅ የሆኑት ሳራህ በ34 ዓመታቸው ነው በሊቀ ጳጳስ ጆን ፖል ዳግማዊ የጊኒ ኮንክሪ ጳጳስ ሆነው የተሾሙት።

በ2021 በቫቲካን የካቶሊክ ቤተክርስቲያናት አስተምህሮ የሚከታተለው ቢሮን ከሚመሩበት በጡረታ የተሰናበቱት ካርዲናል ሳራህ ረዥም እና አስደናቂ የአገልግሎት ሕይወትን አሳልፈዋል።

ምንም እንኳ ለሊቀ ጳጳስነቱ ተመራጭ ባይሆኑም በወግ አጥባቂ ካርዲናሎች ዘንድ ድጋፍ አያጡም።

ካርዲናል ማሪዮ ግሬች

ካርዲናል ማሪዮ ግሬች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ማሪዮ ግሬች

የ68 ዓመቱ ማልታዊ ማሪዮ ግሬች ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ አድርገው በ2019 ሾመዋቸዋል።

በዚህ ኃላፊነታቸውም የሊቀ ጳጳሱ ራዕይ የሆነውን የአጠቃላይ በዓለም ላይ የሚገኘው የምዕመናኑን አመለካከት በቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ ማንጸባረቅ የሚለውን በማስፈጸም ረገድ ቁልፍ ሰው ነበሩ።

አብረዋቸው እንደሠሩት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሁሉ ግሬችም በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ ተብሎ ይታመናል።

ካርዲናሎች የሊቀ ጳጳሱን ግቦች የሚያሰፈጽም፣ ታች ላሉ የቤተክርስቲያኒቱ ምዕመናን እና አገልጋዮች ላይ ኃላፊነትን ለመስጠት የሚያስቡ ከሆነ ካርዲናል ግሬች ተመራጭ ይሆናሉ።

ካርዲናል ማቲዮ ዙፒ

ካርዲናል ማቲዮ ዙፒ

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ማቲዮ ዙፒ

የ69 ዓመቱ ጣልያናዊ ካርዲናል ማቲዮ ዙፒ በሞዛምቢክ ለ15 ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት በአውሮፓውያኑ 1990 እንዲያበቃ ያሸማገሉ ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ በጓቲማላ እና ቡሩንዲ በተመሳሳይ የማሸማገል ሥራ ሰርተዋል።

የቦሎኛ ጳጳስ የሆኑት እና በሮም ያደጉት ካርዲናሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለድሆች እና ለተገለሉ ማኅበረሰቦች የሚሠራ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ በሰፊው ይሳተፋሉ።

በ2019 ካርዲናል ሆነው የተሾሙት ማቲዮ ዙፒ ወደ ኪየቭ እና ሞስኮ በመጓዝ ወደ ሩሲያ የተወሰዱ 19 ሺህ ዩክሬናውያን ሕጻናት እንዲመለሱ አድርገዋል።

ካርዲናል ጆሴፍ ቶቢን

ካርዲናል ጆሴፍ ቶቢን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ጆሴፍ ቶቢን

አሜሪካዊው የ73 ዓመት አዛውንት ካርዲናል ጆሴፍ ቶቢን የተወለዱት ዲትሮይት ሲሆን፣ በካርዲናሎች ዘንድ እጅግ በጣም ታዋቂ ናቸው።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የተሻለ አካታች እና ሁሉንም ተቀባይ እንድትሆን የሚለው የሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሃሳብ ታማኝ ደጋፊ የነበሩ ቢሆንም ሁሉንም አንድ የሚያደርጉ ተደርገው ይታያሉ።

በኢንዲያናፖሊስ ጳጳስ የነበሩት ቶቢን ካርዲናል ተደርገው የተሾሙት በሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ነው።

ካርዲናል አንጄሎ ስኮላ

ካርዲናል አንጄሎ ስኮላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል አንጄሎ ስኮላ

ጣልያናዊው ካርዲናል አንጄሎ ስኮላ ዕድሜያቸው 83 ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2013 ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሲመረጡ ዋነኛ ተፎካካሪ ነበሩ።

ካርዲናል አንጄሎ ስኮላ በዚህ ዕድሜያቸው መጽሐፍ ጽፈው በማሳተማቸው ቀጣዩን ሊቀጳጳስ ለመምረጥ ምሥጢራዊ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ስማቸው እየተነሳ ነው።

ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሆስፒታል ከመግባታቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ለመጽሐፋቸው "ሞት የሁሉም ነገር መጨረሻ አይደለም፣ ነገር ግን የሆነ ነገር መጀመሪያ ነው" ሲሉ መግቢያው ላይ ጽፈውላቸዋል።

ካርዲናል ሬይን ሀርድ ማርክስ

ካርዲናል ሬይን ሀርድ ማርክስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ሬይን ሀርድ ማርክስ

የ71 ዓመቱ ጀርመናዊ ካርዲናል በሙኒክ ጳጳስ የነበሩ ሲሆን፣ የሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ አማካሪ በመሆን በአውሮፓውያኑ 2013 ተሾመው ነበር።

ለ10 ዓመት ያህል ሊቀ ጳጳሱን በቤተክርስቲያኒቱ ተሃድሶ ላይ ያማከሩ ሲሆን፣ አሁንም የቫቲካንን የፋይናንስ ተሃድሶ በበላይነት ይቆጣጠራሉ።

የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ወይንም ፆታቸውን የቀየሩ ሰዎችን በተመለከተ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን በአስተምህሮቷ ውስጥ አካታች የሆነ አቀራረብ እንድትከተል በመወትወት ይታወቃሉ።

ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ

ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ

ጣልያናዊው የ60 ዓመቱ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በ25 ዓመታቸው በሮም የተቀቡ ሲሆን፣ ወዲያውኑ ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ኑሯቸውን በዚያ አድርገዋል።

ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ከአምስት ዓመት በፊት የኢየሩሳሌም ላቲን ፓትርያርክ አድርገው የሾሟቸው ሲሆን፣ በኋላም ካርዲናል ሆነዋል።

ፒዛባላ ኢየሩሳሌምን "የዚህ ዓለም ሕይወት ልብ" ሲሉ ይጠሯታል።

ካርዲናል ማርክ ኦውሌት

ካርዲናል ማርክ ኦውሌት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ማርክ ኦውሌት

የ80 ዓመቱ ካናዳዊ ካርዲናል ማርክ ኦውሌት በአውሮፓውያኑ 2005 እንዲሁም በ2013 ሊቀ ጳጳስ ይሆናሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ለበርካታ ዓመታት በቫቲካን በመላው ዓለም የሚሾሙ ኤጲስ ቆጶሳትን በሚመርጠው የጳጳሳት ጉባዔ ላይ ያሳለፉት ካርዲናል ኦውሌት የወደፊቱን የካቶሊክ አመራር በመምረጥ እና በማደራጀት ቁልፍ ሰው ናቸው።

ካርዲናል ዢን ማርክ አቬላይን

ካርዲናል ዢን ማርክ አቬላይን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ዢን ማርክ አቬላይን

ፈረንሳዊው የ69 ዓመቱ ካርዲናል ዢን ማርክ አቬላይን የተወለዱት በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በነበረችው አልጄሪያ ነው።

በፈረንሳይ ሁለተኛ ከተማ ማርሴይ ያደጉት ካርዲናል አቬላይን ጳጳስ ሆነው የተሾሙትም እዚያ ነው።

ግሪጎሪ 11ኛ በ1378 ከሞቱ ወዲህ ፈረንሳዊ ሊቀ ጳጳስ ተሾሞ አያውቅም።

"ስደተኞችም በወንጀል መቅጣት የሃጥያት መነሻ ነው" በማለት የሚናገሩት ካርዲናሉ፣ ፈረንሳይ ስደተኞች ላይ ትኩረት በማድረግ እንድትሠራ በመወትወት ይታወቃሉ።

ካርዲናል ቻርለን ማኡንግ ቦ

ካርዲናል ቻርለን ማኡንግ ቦ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ቻርለን ማኡንግ ቦ

የ76 ዓመቱ የምያንማር ዜጋ ካርዲናል ቻርለን ማኡንግ ቦ በእናታቸው ያደጉ ሲሆን፣ ራሳቸውን በጦርነት የምትታመሰው ምያንማር አገልጋይ አድርገው ነው የሚቆጥሩት።

ለሁለት የሥልጣን ዘመን ያህል የእስያን ጳጳሳት የመሩት ካርዲናል ቦ የፍራንሲስ የቅርብ ወዳጅ ነበሩ ይባላል።

ካርዲናል ማይክል ቸርኒ

ካርዲናል ማይክል ቸርኒ

የፎቶው ባለመብት, Shutterstock

የምስሉ መግለጫ, ካርዲናል ማይክል ቸርኒ

የ78 ዓመቱ ካርዲናል ማይክል ቸርኒ ካናዳዊ ናቸው።

ካርዲናል ቸርኒ በሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ካርዲናል ተደርገው የተሾሙ ሲሆን፣ የቤተክርስቲያኒቱ በጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ በመሥራት ይታወቃሉ።

በቀድሞዋ ቼኮዝላቫኪያ የተወለዱት እና ሁለት ዓመት ሲሆናቸው ቤተሰባቸው ወደ ካናዳ ያቀናው ቸርኒ፣ በላቲን አሜሪካ እንዲሁም በአፍሪካ አገልግለዋል።

አፍሪካን ጄስዊት ኤይድስ ኔትወርክን የመሠረቱ ሲሆን በኬንያም አስተምረዋል።