ትራምፕ ራሳቸውን እንደ ካቶሊክ ጳጳስ አድርጎ የሚያሳይ የኤአይ ምስል ማጋራታቸው ቁጣ ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, X/White House
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተሰራ እና የካቶሊክ ጳጳስ አድርጎ የሚያሳያቸውን ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ ማጋራታቸው ከካቶሊክ እምነት ተከታዮች ዘንድ ነቀፌታ አስከተለባቸው።
ይህ ምስል በዋይት ሐውስ ይፋዊ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተጋራው የካቶሊክ እምነት ተከታዮች በሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሞት ሐዘናቸውን እየገለፁ ባለበት ወቅት እና ቀጣዩን ሊቀ ጳጳስ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ እያሉ ነው።
በኒው ዮርክ የሚገኘው የካቶሊክ ጉባዔ ትራምፕ በእምነቱ ላይ እየቀለዱ ነው ሲል ቅሬታውን ገልጿል።
ይህ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፍ የተጋራው ዶናልድ ትራምፕ ለጋዜጠኞች "ጳጳስ መሆን እፈልጋለሁ" ብለው ከቀለዱ በኋላ ነው።
ትራምፕ በካቶሊክ እምነት ላይ እያፌዙ ነው ተብለው የተተቹ የመጀመርያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አይደሉም።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከዓመታት በፊት በታምፓ ፍሎሪዳ የጽንስ ማቋረጥን በሚደግፉ ግለሰቦች በተዘጋጀ ሠልፍ ላይ የመስቀል ምልክት ሲሰሩ ወይንም ሲያማትቡ መታየታቸው ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።
የቫቲካን ቃል አቀባይ ማቲዮ ብሩኒ ቅዳሜ ዕለት ትራምፕ ስላጋሩት ምስል የቤተክርስትያኒቷ አቋም ምን እንደሆነ ተጠይቀው ከመመለስ ተቆጥበዋል።
ቫቲካን ከሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ ቀጣዩን ሊቀ ጳጳስ ለመምረጥ የሚሰየሙ ጳጳሳትን ለመቀበል በዝግጅት ላይ ናት።
አርብ ማታ በትራምፕ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋራው ይህ ምስል ጳጳሳት የሚለብሱትን ነጭ ልብሰ ተክህኖ እና ቆብን አድርገው ይታያል።
በኤአይ በተሰራው በዚህ ምስል ላይ ትራምፕ በአንገታቸው ላይ ትልቅ መስቀል ያደረጉ ሲሆን የቀኝ እጃቸውን ጣት ቀስረዋል። ፊታቸው ላይም ጥሞና ይነበባል።
ምስሉ መጋራቱን ተከትሎም የኒው ዮርክን ጳጳስ የሚወክለው የኒው ዮርክ ግዛት የካቶሊክ ጉባዔ ቅሬታውን ለኤክስ ማስገባቱን አስታውቋል።
"ክቡር ፕሬዝዳንት በዚህ ምስል ላይ ምንም ዓይነት ጥበብ ወይንም የሚያስቅ ነገር የለም" ሲል ቡድኑ ጽፏል።
"ተወዳጁን አባታችንን ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን ገና መቅበራችን ነው፤ እንዲሁም የካቶሊክ የእምነት አባቶች ቀጣዩን ሊቀ ጳጳስ ለመምረጥ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስትያን የጽሞና ጊዜ ሊጀምሩ ነው። አያላግጡብን።" ብሏል ቡድኑ በመግለጫው።
የጣልያን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ሬንዚ፣ ዶናልድ ትራምፕ ምስሉን በማጋራታቸው ኮንነዋቸዋል።
ሬንዚ "ይህ ምዕመኑን የሚያስቆጣ፣ ተቋሙን የሚሳደብ እንዲሁም የቀኝ ዘመም ዓለም መሪዎች በማላገጥ ደስታን እንደሚያገኙ የሚያሳይ ምስል ነው" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ዋይት ሐውስ ግን የሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንት በጵጵስናው እና በጳጳሱ ላይ እያላገጡ ነው የሚለውን አስተያየት ውድቅ አድርጎታል።
"ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ለመግለጽ እና በቀብራቸው ላይ ለመገኘት ሮም ድረስ መሄዳቸው ይታወሳል። እንዲሁም ለካቶሊኮች እና ለሃይማኖት ነጻነት ታማኝ ደጋፊ መሆናቸው ይታወቃል" ሲሉ የፕሬስ ሴክረተሪዋ ካሮላይን ሌቪት ተናግረዋል።












