ሕንድ በፓኪስታን እና በፓኪስታን ቁጥጥር ስር በሚገኘው ካሽሚር ግዛት የአየር ድብደባ ፈጸመች

ሕንድ የአየር ጥቃት በፈጸመችበት ወቅት ስፍራዎቹ ከርቀት ሲታዩ

በሕንድ ቁጥጥር ስር በሚገኘው ካሽሚር ግዛት በአገር ውስጥ ጎብኚዎች ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሕንድ በፓኪስታን እና በፓኪስታን ቁጥጥር ስር በሚገኘው ካሽሚር ግዛት ላይ ተከታታይ ጥቃቶችን ሰነዘረች።

ሕንድ በፓኪስታን እና በፓኪስታን ቁጥጥር ስር በሚገኘው ካሽሚር ዘጠኝ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚሳዔል ጥቃት መሰንዘሯን አስታውቃለች።

የፓኪስታን መከላከያ ኃይል በበኩሉ ሦስት ቦታዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን ገልጾ ስምንት ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን አስታውቋል።

የአገሪቱ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ስምንት ሰላማዊ ዜጎች መሞታቸውን አረጋግጦ 35 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።

ፓኪስታን ኢዝላማባድ "በመረጠችው ጊዜ ምላሽ ትሰጣለች" ስትል ስለ ጥቃቱ ተናግራለች።

የሕንድ መከላከያ ሚኒስቴር ጥቃቱን "ኦፕሬሽን ሲንዶር" ሲል የጠራው ሲሆን፣ ይህ ዘመቻ ሚያዝያ 14 2017 ዓ.ም. 22 ሕንዳውያን እና አንድ ኔፓላዊ የገደሉትን "ተጠያቂ" ለማድረግ የተካሄደ መሆኑን ገልጿል።

ፓኪስታን ሕንዳውያን ጎብኚዎችን በቀጠፈው ጥቃት ላይ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላት ገልጻ የሕንድ የሚሳዔል ጥቃት "ምንም ትንኮሳ ሳይደረግ" የተፈጸመ መሆኑን ገልጻለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሸሪፍ "ይህ አስጸያፊ ትንኮሳ ምላሽ ሳይሰጠው የሚታለፍ አይደለም" ብለዋል።

ሕንድ ረቡዕ ማለዳ በዘጠኝ የተለያዩ ስፍራዎች በፓኪስታን የሚተዳደረውን ካሽሚርን እና ፓኪስታንን ዒላማ በማድረግ ጥቃት መፈፀሟን ተናግራለች።

ዴልሂ ዒላማ ያደረገቻቸው ስፍራዎች "የሽብርተኛ መሰረተ ልማቶች" ናቸው ያለች ሲሆን፤ ጥቃት የተፈፀመባቸው ስፍራዎች "የታቀደባቸው እና ዒላማ የተደረገባቸው" መሆናቸውን አስታውቃለች።

ሕንድ ምንም የፓኪስታን ወታደራዊ ተቋማትን አለመምታቷን ገልጻ "የተፈጸሙት ጥቃቶች ዒላማ የተደረገባቸው፣ በአግባቡ የተሰሉ እና በተፈጥሯቸው ወደ ሌላ ግጭት የማይስፋፉ" መሆናቸውን አብራርታለች።

ፓኪስታን በበኩሏ ሦስት የተለያዩ ስፍራዎች ላይ ጥቃት መድረሱን ተናግራለች።

የፓኪስታን መከላከያ ሚኒስትር ካሃዋጃ አሲፍ ለጂዮቲቪ በሰጡት ቃለ ምልልስ በጥቃቱ የሰላማዊ ዜጎች መኖርያ አካባቢ መመታቱን ተናግረው ሕንድ "ዒላማ የተደረጉት የሽብርተኞች ካምፖች ናቸው" የምትለው ሐሰት ነው ብለዋል።

የፓኪስታን መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በጥቃቱ ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የፓኪስታን መከላከያ ቃል አቀባይ አምስት የሕንድ ተዋጊ ጀቶችን እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች መትተው መጣላቸውን ተናግረዋል።

ሕንድ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ድረስ ይፋዊ ምላሽ አልሰጠችም።

ሚያዝያ 14 በተፈጸመው እና የ26 ሰዎችን ሕይወት ከቀጠፈው ጥቃት የተረፉ ሰዎች ግድያው ሂንዲዎችን በመለየት የተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥቃቱ ከሁለት አስተርት ዓመታት ወዲህ የተፈጸመ እና በርካታ ሕንዳውያን የተገደሉበት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ተጠርጣሪዎቹን "እስከ ምድር ጥግ ድረስ ተጉዘን" እናድናቸዋለን ሲሉ ዝተዋል።

አክለውም ግድያውን የፈጸሙት ደግሞ "ከሚገምቱት በላይ ቅጣት ይደርስባቸዋል" ብለዋል።

ይኹን እንጂ ሕንድ ጥቃቱን የፈፀመው ቡድን የትኛው እንደሆነ በይፋ ያልተናገረች ሲሆን እስካሁን ድረስ ከጥቃቱ ጀርባ ያለው ማን እንደሆነ ግልጽ አልሆነም።

የሕንድ ፖሊስ ግን ከአራቱ ጥቃት ፈጻሚዎች ሁለቱ ፓኪስታናውያን መሆናቸውን ገልጿል።

የሕንድ መንግሥት በፓኪስታን የሚደገፉ አማፂያንን ተጠያቂ ቢያደርግም ኢዝላማባድ ግን ውንጀላውን ውድቅ አድርጋለች።

ሕንድ እና ፓኪስታን የካሽሚር ግዛትን ይገባኛል ቢሉም ሁለቱም አገራት ነጻነታቸውን ካገኙ ጊዜ ጀምሮ ግዛቲቱን በከፊል ብቻ ያስተዳድራሉ።

ሁለቱ አገራት ሁለት ጊዜ በይገባኛል የተነሳ ጦር ተማዝዘዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአማፂያን የሚፈጸሙ ጥቃቶች ብቻ ሁለቱን አገራት ወደ ፍጥቻ አምጥቷቸዋል