እስራኤል በየመን ወደቦች እና የኃይል ማመንጫ ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች

ጋላክሲ ሊደር መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Mohammed Hamoud/Getty Images

እስራኤል በየመን ሁቲዎች በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሶስት ወደቦች እና የኃይል ማመንጫ ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች።

እስራኤል በሁዳይዳህ፣ ራስ ኢሳ እና ሳይፍ ወደቦች ላይ የፈጸመቻቸውን ጥቃቶች ተከትሎ፤ ሁለት ሚሳኤሎች ከየመን መወንጨፋቸውን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ገልጿል።

በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የየመን ዜጎች የምግብ እና ሌሎች ሰብዓዊ እርዳታዎች ዋና መግቢያ የሆነችው ሁዳይዳህ የወደብ ከተማ ባለፈው ዓመት የእስራኤል በርካታ ጥቃቶች ኢላማ ሆናለች።

የእስራኤል የባህር ኃይል መርከቦች በግንቦት እና ሰኔ ወራት በሁዳይዳህ ጥቃቶችን ፈጽመው ነበር።

ኢብና እና ታይዝ ለተሰኙት ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያቀርበው ራስ ካናቲብ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ በእስራኤል ጥቃት ተፈጽሞበታል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ጥቃት ከፈጸሙባቸው ኢላማዎች መካከል ጋላክሲ ሊደር የተሰኘችው መርከብ እንደምትገኝበት አረጋግጠዋል።

መርከቧ ከሁለት ዓመት በፊት በሁቲዎች ቁጥጥር ስር እንደዋለች እና በአለም አቀፍ ውሃ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ያገለግል እንደነበር ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሰፊ የየመንን ግዛት የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች ቃለ አቀባይ ጥቃቱን ተከትሎ በርካታ በአገር ውስጥ በሚመረቱ ከምድር ወደ አየር ላይ በሚወነጨፉ ሚሳኤሎችን" ወደ እስራኤል ማስወንጨፋቸውን አስረድተዋል።

በተለያዩ የእስራኤል አካባቢዎች የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያዎች የተሰሙ ሲሆን፤ የእስራኤል መከላከያ የከሸፉ ሚሳኤሎችን በተመለከተ "ግምገማ ላይ መሆኑንም" አስታውቋል።

በእስራኤል ጥቃት ሁዳይዳህ ወደብ መመታቱን የየመን ሚዲያ የዘገበ ሲሆን ስለ ጉዳቱ ወይም ሞት ተከስቶ ስለመሆኑ ዝርዝር መረጃ አልተገኘም።

ሚኒስትሩ ጥቃቱ "የጥቁር ባንዲራ ዘመቻ" [ኦፕሬሽን ብላክ ፍላግ] አካል መሆኑን ገልጸው ሁቲዎች "ለድርጊታቸው ከፍተኛ ዋጋ እንደሚከፍሉ" አስጠንቅቀዋል።

"የየመን እጣ ፈንታ ከቴህራ እጣ ፈንታ ጋር ተመሳሳይ ነው። እስራኤልን ለመጉዳት የሚሞክር ሁሉ ይጎዳል፤ በእስራኤል ላይ እጁን ያነሳ ሁሉ እጁን ይቆረጣል" ሲሉ ሚኒስትሩ በኤከስ ገጻቸው አስፍረዋል።

የጋዛ ጦርነት ከጀመረ ወዲህ የሁቲ አማጺያን በጋዛ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን በመወገን ሚሳኤሎች ወደ እስራኤል ከማስወንጨፍ በተጨማሪ እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመችው ያለችውን ጥቃት እንድታቆም በማስጠንቀቅ በቀይ ባህር የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።

የእስራኤል አየር ኃይል በበኩሉ በየመን ወደቦች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ሁቲዎች በእስራኤል እና በዜጎቿ ላይ ላደረሱት ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምላሽ ነው ብሏል።

ኢላማ የተደረገባቸው ወደቦች በእስራኤል እና አጋሮቿ ላይ "የሽብር እቅዶችን ለመፈጸም ከኢራን መንግሥት የጦር መሳሪያ የሚጓጓዝበት" ነው ብሏል።

ከጥቃቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሁቲዎች የአየር መከላከያዎቻቸው የእስራኤልን ጥቃት በሚሳኤሎች መጋፈጣቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።