ሁቲዎች በእስራኤል ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት እንደሚቀጥሉ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሁቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ባለስልጣን በየመን የእስራኤል የአየር ጥቃት እየተባባሰ ቢመጣም ቡድኑ ከፍልስጤማውያን ጋር በመቆም እስራኤልን ላይ የከፈተውን ጥቃት ይቀጥላል ሲሉ ተናገሩ።
መሐመድ አል ቡኻይቲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል" እስካልቆመ ድረስ ሁቲዎች "በእስራኤል ወታደራዊ ዒላማ የምናደርሰውን ጥቃት አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።
ሐሙስ እለት የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በየመን ዋና ከተማ ሰነዓ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና በቀይ ባህር ዳርቻ በሚገኙ ወደቦች እና ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ቢያንስ አራት ሰዎችን ገድለዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በኢራን የሚደገፈው ቡድን ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ በሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች በመታገዝ ለፈጸማቸው ጥቃቶች የሚሰጠው ምላሽ ገና መጀመሩ መሆኑን በመጥቀስ አስጠንቅቀዋል።
ለሊቱን ሁቲዎች ባላስቲክ ሚሳኤል ወደ እስራኤል የተኮሱ ሲሆን፣ የእስራኤል ጦር ወደ ግዛቱ ከመድረሱ በፊት ተጠልፎ ነበር ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀኃፊ የተጋጋለው ውጥረት "በጣም አሳስቦኛል" ብለዋል።
በተጨማሪም በአውሮፕላን ማረፊያው እና ወደቦች ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶች "በተለይ አሳሳቢ ናቸው" ካሉ በኋላ፣ ጥቃቱ በጦርነት በምትታመሰው አገር የሚደረገው "ሰብዓዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ አደጋ" እንደሚፈጥር አስጠንቅቀዋል።
ሰሜናዊ ምዕራብ የመንን የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች እ.ኤ.አ ጥቅምት 2023 ላይ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በጋዛ ጦርነት ጀምሮ ብዙ ሳይቆይ በእስራኤል እና በዓለም አቀፍ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀመረዋል።
እስራኤል ከሐምሌ ወር ጀምሮ፣ ከየመን ተወንጭፈዋል ላላቸው 400 ሚሳኤሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት በሚል በሁቲዎች ላይ አራት ዙር የአየር ድብደባ አድርጋለች።
በደቡባዊ ቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ ቡድኑ በርካታ የንግድ መርከቦች ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ እና እንግሊዝ በየመን የአየር ድብደባ ፈፅመዋል።
የሁቲዎች የፖለቲካ ቢሮ አባል መሀመድ አል ቡኻይቲ አርብ ዕለት ለቢቢሲ 'ኒውስ አወር' ፕሮግራም እንደተናገሩት በየመን ለዓመታት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ "መሳሪያዎች" ናቸው ካሏቸው አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና እስራኤል ጋር በቀጥታ ወደ ግጭት መግባታቸውን ተናግረዋል።
ይህ ንግግራቸው እ.ኤ.አ. በ2015 ሁቲዎች ሰንዓን ሲቆጣጠሩ የየመንን መንግሥት በመደገፍ ጣልቃ የገባውን በሳዑዲ የሚመራውን ጥምረት ለማመልከት ይመስላል።
"ጋዛን በመደገፍ ወታደራዊ ዘመቻችንን ለመቀጠል ቆርጠን ተነስተናል እናም የዘር ማጥፋት ወንጀል እና በጋዛ ላይ ያለው ከበባ እስኪቆም ድረስ ጥቃታችንን አናቆምም ። በእስራኤል ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ የምናደርገውን ጥቃት እናጠናክራለን" ብለዋል።
እስራኤል ጦሯ በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመ ነው የሚለውን ውንጀላ ታስተባብላለች።
ቡኻይቲ አጋሮቻቸው ሃማስ እና ሔዝቦላህ ከእስራኤል ጋር ላለፉት 14 ወራት ባደረጉት ጦርነት ውድመት ሲደርስባቸው የተመለከቱ ቢሆንም፣ ሁቲዎች የኢራንን ድጋፍ እንደማያስፈልጋቸው ይናገራሉ።
"ብቻችንም ብንሆን እንኳ፣ ይህንን ጦርነት ለማድረግ በቂ ወታደራዊ፣ የኢኮኖሚ እና የሕዝብ ድጋፍ አቅም አለን" ሲሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ወር ስልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ሁቲዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ተባብሶ እንደሚቀጥል ያላቸውን ግምት ተናግረው "ጦሱ የከፋ ይሆናል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሙስ ማምሻውን እንደተናገሩት አገራቸው "የመቤዠት ጦርነት" ሲሉ በጠሩት እርምጃ "በሁቲ አሸባሪ ድርጅት ዒላማዎች ላይ ጥቃት አድርሳለች" ብለዋል።
ቤንያሚን ኔታንያሁ "ይህን የኢራንን የክፋት የሽብር ክንድ ለመቁረጥ ቆርጠን ተነስተናል። ስራችንን እስክንጨርስ ድረስ እንቀጥላለን" ሲሉ ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትስ፣ እስራኤል በሃማስ እና በሂዝቦላ መሪዎች ላይ እንዳደረገችው ሁሉ የሁቲ መሪዎችን ሁሉ እንደምታደን አስጠንቅቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ትሬምሌይ፣ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "በቀጣናው ሊፈጠር የሚችለውን የከፋ አደጋ በእጅጉ አሳስቧቸዋል፤ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ወታደራዊ እርምጃዎችን እንዲያቆሙ እና በከፍተኛ ሁኔታ ከማንኛውም ነገር እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበዋል" ብለዋል።
የእስራኤል ጦር የአየር ጥቃቱ በሰነአ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ በሄዝያዝ እና ራስ ካናቲብ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እንዲሁም በቀይ ባህር በሁዳይዳህ፣ ሳሊፍ እና ራስ ካናቲብ የቀይ ባህር ወደቦች ላይ በሚገኙ ሁቲዎች ከኢራን የወታደራዊ መሳርያዎችን የሚያስገቡባቸው "ወታደራዊ መሠረተ ልማቶች" ላይ ያነጣጠረ ነው ይላል።
የሁቲዎች ወታደራዊ ቃል አቀባይ በበኩላቸው የአየር ጥቃቱ ዒላማ ያደረጉት የሲቪል ተቋማትን ሲሆን ይህም ለሰላማዊ ሰዎች ሞት እና ቁሳዊ ውድመት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
በሁቲ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የሳባ የዜና ወኪል እንደዘገበው በሰነአ አውሮፕላን ማረፊያ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ በሁዳይዳ ግዛት መገደላቸውን ዘግቧል።
ሆኖም በሁቲ ቁጥጥር ስር በሚገኘው የመን የመንግሥት የትራንስፖርት ሚኒስትር ያህያ አል ሳያኒ አርብ እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሟቾችን ቁጥር አራት አድርሰውታል።
አክለውም በጥቃቱ የሰነአ አውሮፕላን ማረፊያ የተለያዩ ክፍሎችመጎዳታቸውን ዘርዝረው፣ እስራኤል ዓለም አቀፍ ሕግንና የአቪዬሽን ደንቦችን ጥላለች ሲሉ ከስሰዋል።
የእስራኤል አየር ድብደባ ሲደርስ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ አየር አገልግሎት (UNHAS) አውሮፕላን ሊሳፈሩ ነበር።
በጥቃቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አውሮፕላን ሠራተኛ ከባድ ጉዳት ደርሶበት አርብ ዕለት በአካባቢው በሚገኝ ሆስፒታል ቀዶ ጥገና ከተደረገለት በኋላ ወደ ዮርዳኖስ መወሰዱን ዶክተር ቴድሮስ ተናግረዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈረቱት መልዕክት ላይ "በሲቪሎች እና በሰብዓዊ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በሁሉም ቦታ መቆም አለበት" ብለዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ዶ/ር ቴድሮስ በእስር ላይ ያሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች እንዲፈቱ የመደራደር እና በየመን ያለውን የጤና ሰብዓዊ ሁኔታ የገመገመው ተልዕኳቸው አጠናቅቀው አውሮፕላኑ ሊሳፈሩ ሲሉ ነበር።












