ሁቲዎች ያስወነጨፉት ሚሳዔል የእስራኤል ዋና አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ወደቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከየመን የተወነጨፈ ሚሳኤል በእስራኤል ቤን ጉርዮን አየር ማረፊያ ዋና ተርሚናል አቅራቢያ መውደቁን የእስራኤል ባለስልጣናት ተናገሩ።
ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ እና በኦንላየን ላይ የተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምሰል ላይ እንደሚታየው አሽከርካሪዎች ሚሳዔሉ በአቅራቢያቸው ሲያርፍ ለመሸሸግ ሲሯሯጡ ይታያል።
ከቴልአቪቭ መውጪያ ላይ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ያረፈው ሚሳዔል አካባቢውን በጥቁር ጭስ ሸፍኖታል።
አራት ሰዎች በፍንዳታው የተጎዱ ሲሆን ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ ወደ መሸሸጊያዎች በሚያመሩበት ወቅት ጉዳት እንደደረሰባቸው የእስራኤል ሚዲያ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ በመግለጫቸው ላይ "ያጠቃን ማንም ቢሆን ሰባት እጥፍ መልሰን እናጠቃዋለን" ሲሉ ዝተዋል።
የሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ የእስራኤል አየር ማረፊያ "ከአሁን በኋላ ለአየር ጉዞ ደኅንነቱ የተጠበቀ አይደለም" ብለዋል።
አየር ማረፊያው ለአጭር ጊዜ በረራዎችን ያቋረጠ ቢሆንም ተመልሶ ሥራ ጀምሯል።
የሁቲ አማፂያን ያስወነጨፉት ሚሳዔል በእስራኤል ሰማይ ላይ ሲደርስ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የአደጋ ጊዜ ደውሎች መጮህ ጀምረዋል።
የእስራኤል አየር ኃይል የተወነጨፈውን ሚሳዔል ማክሸፍ ያልቻለበት ምክንያት ላይ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የተለቀቁ ምስሎች እንደሚያሳዩት ሚሳዔሉ ያረፈበት አካባቢ ትልቅ ጉድጓድ ተፈጥሯል።
በኢራን መንግሥት የሚደገፉት እና መቀመጫቸውን የመን ያደረጉት ሁቲዎች ለሃማስ ያላቸውን ወገንተኝነት ለማሳየት ወደ እስራኤል በተደጋጋሚ ሚሳዔል ያስወነጭፋሉ።
ነገር ግን የእስራኤል መከላከያን አልፈው የሚያርፉት ጥቂቶቹ ናቸው።
ከሕዳር 2023 ጀምሮ ሁቲዎች በቀይባሕር ላይ የሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ።
አሜሪካ የአማፂያኑን ተግባር ለማስቆም በዋናነት የአየር ጥቃት የምትፈጽም ሲሆን ዩኬም ዘመቻውን ተቀላቅላለች።












