በብራዚል ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሌዲ ጋጋን ኮንሰርት በነጻ ታደሙ

ሌዲ ጋጋ የሙዚቃ ሥራዎቿን ስታቀርብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሮ ካፓካባና የባሕር ዳርቻ የሌዲ ጋጋን የሙዚቃ ድግስ በነጻ መታደማቸውን የከተማዋ ኃላፊዎች ገለፁ።

የድምጻዊቷ ግዙፍ የሙዚቃ ድግስ ነበር የተባለው የዚህ ኮንሰርት ወጪ የተሸፈነው "የሪዮን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት" በሚል በከተማዋ አስተዳደር ነው።

እንደ ባለስልጣናቱ ከሆነ ኮንሰርቱ 100 ሚሊዮን ዶላር የአገር ውስጥ ገቢን ያስገኛል ተብሎ ተገምቷል።

ሌዲ ጋጋ ቅዳሜ ዕለት በሪዮ ዲ ጄኔሮ ያቀረበችው የሙዚቃ ድግስ ስምንተኛውን አልበሟን የማስተዋወቅ አካል ነው።

ሜይሄም (Mayhem) በሚል የሚጠራው አዲሱ የሙዚቃ ሰንዱቋ፣ 'አብራካዳብራ' እንዲሁም 'ዳይ ዊዝ ኤ ስማይል' የተሰኙ ሙዚቃዎች የተካቱበት ነው።

ሌዲ ጋጋ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 በብራዚል ዝግጅቷን አቅርባ ነበር።

ራሳቸውን "ሊትል ሞንስተርስ" ሲሉ የሚጠሩት አድናቂዎቿ የሙዚቃ ድግሱ በሚቀርብበት የባሕር ዳርቻ መሰለፍ የጀመሩት አስቀድመው ነበር።

በዝግጅቱ ላይ የሚታደሙትን ለመጠበቅም 5000 ፖሊሶች የተመደቡ ሲሆን ጥብቅ ፍተሻ እንደነበርም ተገልጿል።

የከተማይቱ ባለስልጣናት የፖሊስን ሥራ ለማገዝ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ፊትን የሚለይ ካሜራ ጥቅም ላይ አውለዋል።

ሌዲ ጋጋ በሪዮ በነጻ የሙዚቃ ድግሷን በማቅረብ የመጀመርያዋ አይደለችም።

ማዶና ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ወጪው በከተማዋ አስተዳደር ተሸፍኖ በካፓካባና የባሕር ዳርቻ የሙዚቃ ድግሷን በነጻ አቅርባለች።

ሚሊዮኖች ተሳተፉበት የሙዚቃ ድግስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሮ ካፓካባና የባሕር ዳርቻ የሌዲ ጋጋን የሙዚቃ ድግስ በነጻ ታድመዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሌዲ ጋጋ የሙዚቃ ድግሷን ለመታደም ለተገኙት አድናቂዎቿ የብራዚል ባንዲራን እያውለበለበች "እስካሁን ጠበቃችሁኝ፣ ከ10 ዓመት በላይ ጠበቃችሁኝ" ስትል በስሜት ተሞልታ ተናግራለች።

አክላም "ብራዚል፣ ዝግጁ ነኝ። ያለኝን ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ" ብላለች።

ድምጻዊቷ የተወሰኑ ሙዚቃዎቿን ስትጫወት ከብራዚል የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኑ ማሊያ ጋር የሚመሳሰል አልባሳትን የለበሰች ሲሆን፣ አገሪቷን የሚያንጸባርቁ አልባሳት በመድረኩ ላይ ጎልተው ታይተዋል።

አሊሃንድሮ፣ ፖከር ፌስ እንዲሁም አብራካዳብራ የተሰኙት ሙዚቃዎቿን አድናቂዎቿ አብረዋት ዘፍነዋል።

በባሕር ዳርቻው በሙዚቃ ድግሱ ላይ ለመገኘት ከመላው አገሪቱ ክፍል ረዥም ርቀት ተጉዘው የመጡ ሰዎች ነበሩ።

የ28 ዓመቱ ሉአን ሜሲያስ ከሳኦ ፖሎ ግዛት ሙሉ ለሊት ተጉዞ የሌዲ ጋጋን ሙዚቃ ለመታደም መምጣቱን ተናግሯል።

የ22 ዓመቷ አሊሻ ዱአርቴ ለኤኤፍፒ እንደተናገረችው እኩለ ሌሊት ሰባት ሰዓት ላይ በሙዚቃ ድግሱ ላይ ለመታደም ሠልፍ መያዟን ተናግራለች።

"ሌዲ ጋጋ ይገባታል፤ በጣም ይጨናነቃል፤ ነገር ግን እንቋቋመዋለን" ብላለች።

ሌላዋ አድናቂዋ ፓውላ ኦሊቩይራ በሙዚቃ ድግሱ ለምን ደስተኛ እንደሆነች ተናግራለች።

"ራሳችንን እንድንሆን ትነግረናለች፤ የተለየን መሆን እንደምንችል እና ያ ደግሞ መልካም መሆኑን ትነግረናለች" ስትል ለሮይተርስ አስረድታለች።

ላኢ ቦርጌስ ለሮይተርስ የዜና ወኪል "ፈጽሞ የማይረሳ ትርዒት ነው የሚሆነው" ካለች በኋላ "በጣም ስሜታዊ ነው የሚያደርገኝ እና ብዙ የማለቅስ ይመስለኛል" ብላ ነበር ወደ ሙዚቃ ድግሱ እያመራች።

ሌዲ ጋጋ የሙዚቃ ድግሷ ማጠናቀቂያ ላይ አድናቂዎቿን በስማቸው ጠርታ "እኛ ሞንስተሮች ነን፤ ሞንስትሮች ደግሞ በጭራሽ አይሞቱም" ብላለች።

በስተመጨረሻም ባድ ሮማንስ የተሰኘውን ተወዳጅ ሙዚቃዋን አቅርባ ዝግጅቷን አጠናቅቃለች።