በደቡብ ሱዳን በሆስፒታል እና በገበያ ቦታ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት ሰባት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

በእሳት የተያያዘው የሆስፒታል ክፍል

የፎቶው ባለመብት, Médecins Sans Frontières/Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኤምኤስኤፍ የሆስፒታሉ ክፍል በእሳት መያያዙን የሚያሳይ ምስል አጋርቷል።

በደቡብ ሱዳን በሆስፒታል እና በገበያ ሥፍራ ላይ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት ቢያንስ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት ገለጸ።

ይህ ጥቃት የተፈፀመው አገሪቷ ወደ የእርስ በርስ ጦርነት ትገባለች የሚል ስጋት ባየለበት ወቅት ነው።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) እንዳለው መሣሪያ የታጠቀች ሔሊኮፕተር በጆንግሌ ግዛት፣ ኦልድ ፋንጋክ በሚገኝ ሆስፒታል መድሃኒት ቤት ላይ ቦምብ የጣለች ሲሆን በዚህም መድሃኒት ቤቱ ሙሉ በሙሉ ወድሟል። ከዚያም ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በአካባቢው ያለ የገበያ ሥፍራ ላይ ቦምብ መጣሏን ኤምኤስኤፍ ገልጿል።

ጥቃት የተፈፀመበት ሆስፒታሉ ከ110 ሺህ በላይ ሕዝብ በሚኖርበት ፋንጋክ ግዛት የሚገኝ ብቸኛው ሆስፒታል ሲሆን ሁሉም የሕክምና ቁሳቁሶች መውደማቸውን ኤምኤስኤፍ አስታውቋል።

ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ከሞቱት በተጨማሪ 20 ሰዎችን ለጉዳት የዳረገውን ጥቃት " ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ ሕግ በግልጽ የጣሰ" ብሎታል።

የኤምኤስኤፍ ቃል አቀባይ ማማን ሙስጠፋ፣ ድርጅቱ መረጃዎችን ገና እያደራጀ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ነገር ግን የዓይን እማኞች አውሮፕላኗ "የመንግሥት ኃይሎች ሔሊኮፕተር" እንደሆነች መናገራቸውን ለቢቢሲ ኒውስአዎር ፕሮግራም አስረድተዋል ።

" ሆስፒታሉ በግልጽ የተሰቀለ መለያ አለው። መገኛ መለያችንን ለሁሉም ተፋላሚ ወገኖች አሳውቀናል፤ በመሆኑም ሆስፒታሉ የት እንደሚገኝ በሁሉም ወገኖች ዘንድ መታወቅ ነበረበት" ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ጥቃቱን በተመለከተ ቢቢሲ የአገሪቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጠየቀ ቢሆንም ወዲያውኑ የተሰጠ ምላሽ የለም።

በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ መሪ ኒኮላስ ሃይሶም አገሪቷ ወደ ሙሉ የእርስ በርስ ጦርነት ለመግባት ጫፍ ላይ ነው የምትገኘው ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።

ይህ ስጋት የተፈጠረው በፕሬዚደንት ሳል ቫኪር እና በምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል ያለው አለመግባባት እየተባባሰ በመምጣቱ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከቦምብ ጥቃቱ ቀደም ብሎ የአገሪቷ ጦር አዛዥ ፖል ማጆክ ናንግ፣ በርካታ ጀልባዎች ከተጠለፉ በኋላ የአፀፋ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተው ነበር።

የጦር አዛዡ ለጥቃቱ ከምክትል ፕሬዚደንቱ ማቻር ጋር ግንኙነት ያላቸውን ታጣቂዎች ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፤ ማቻር ግን ለቀረበባቸው ክስ ምላሽ አልሰጡም።

ማቻር መጋቢት ወር ላይ "አመጽ ለመቀስቀስ ሞክረዋል" በሚል ከበርካታ አጋሮቻቸው ጋር ታስረው ነበር።

በቅርቡም መንግሥት ከማቻር ጋር የሚያብሩ ያሏቸውን ግዛቶች ዘርዝሯል።ይህም አገሪቷ ሁለት ትላልቅ ብሔረሰቦችን ወዳሳተፈ ሌላ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚለውን ስጋት ጨምሮታል።

ደቡብ ሱዳን ከሱዳን በመገንጠል ነጻነቷን ያገኘችው እንደ አውሮፓውያን 2011 ነበር።

ሆኖም ከሁለት ዓመት በኋላ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር 'መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አቀነባብረዋል' በሚል ማቻርን ከምክትል ፕሬዚደንትነት ማንሳታቸውን ተከትሎ የእርስ በርስ ጦርነት ተቀስቅሷል።

በሁለቱ መሪዎች ደጋፊዎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ለ400 ሺህ ሰዎች ሞት እና ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

ከዚያም እንደ አውሮፓውያኑ 2018 የሰላም ስምምነት ላይ ደርሰው ሁለቱ ወገኖች የተሳተፉበት የአንድነት መንግሥት ተቋቁሟል። በሰላም ስምምነቱ መሰረት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ ዜጎች መሪያቸውን ይመርጣሉ ተብሎ ቢታሰብም እስካሁን በአገሪቱ ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም።

ከዚህም በተጨማሪ ሁሉንም ሚሊሻዎች ወደ አንድ በማምጣት እና አንድ የተባበረ ጦር ለመመስረት ታስቦ የነበረ ቢሆንም እንደታሰበው አልሆነም።

አሁንም በርካታ የታጠቁ ቡድኖች ለተለያዩ ፖለቲከኞች ታማኞች ናቸው።

አሁን ላይ የተፈጠረው ቀውስ የተቀሰቀሰው ከወራት በፊት ሲሆን በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት ከማቻር ጋር ተሰልፈው የነበሩ ዋይት አርሚይ ታጣቂዎች በላይኛው የናይል ግዛት ከሚገኙ ወታደሮች ጋር በመጋጨታቸው እና በናስር የሚገኘውን የጦር ሰፈር ከወረሩ በኋላ ነበር።

ከዚያም መጋቢት ወር ላይ ከጦር ሰፈሩ ወታደሮችን ለማስወጣት ስትሞክር የነበረች የተባበሩት መንግሥታት ሔሊኮፕተር በጥይት ተመትታ ከፍተኛ የጦር ጀነራሎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ሞተዋል።

የመብት ተሟጋች ቡድኖችም ጦሩ በሰላማዊ አካባቢዎች እና መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መፈፀሙን እንዲያቆም እየጠየቁ ነው።