እስራኤል እሁድ ለተፈጸመባት ጥቃት በሁቲዎች ላይ የአጸፋ እርምጃ ወሰደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የየመን ሁቲዎች በዴቪድ ቤን ጎሪዮን አየር ማረፊያ ላይ ለፈጸሙት የሚሳዔል ጥቃት አጸፋ የመን ውስጥ የሚገኙ የቡድኑ ዒላማዎች መምታቱን የእስራኤል ጦር አስታወቀ።
የእስራኤል የመከላከያ ኃይል ጥቃት የተፈጸማባቸው ስፍራዎች በየመን ሁዳይዳህ ወደብ ላይ እና በከተማዋ በሚገኝ የሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ ሲሆን እነዚህም "የሁቲ ኃይሎች የአቅርቦት ማዕከል" ናቸው ብሏል።
ሁቲዎች እሁድ ዕለት በእስራኤል የአየር ማረፊያ ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ፣ እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ ለማስፋፋት ላወጣችው ዕቅድ ምላሽ አየር ማረፊያዎቿን ዒላማ በማድረግ "አጠቃላይ የአየር እንቅስቃሴዎቿን እናቅባለን" ብለዋል።
የአየር ጥቃቱን "የአሜሪካ እና የእስራኤል የጋራ ወረራ" ነው ያለው በኢራን የሚደረገፈው ሁቲ እስራኤል ሰኞ ዕለት በፈጸመችው ጥቃት 21 ሰዎች ቆስለዋል ብሏል። አሜሪካ ግን በጥቃቱ ተሳትፎ እንደሌላት አስተባብላለች።
የእስራኤል የመከላከያ ኃይል የተፈጸመው ጥቃት "በወደብ ላይ የቆሙ መርከቦችን ለመከላከል የተወሰደ ግልጽ እርምጃ" ነው ብሏል።
ጥቃት የተፈጸመበት የሲሚንቶ ፋብሪካ የቡድኑ "ወሳኝ የገንዘብ ምንጭ" መሆኑን እና ከመሬት በታች መተላለፊያዎችን እንዲሁም መሠረተልማቶችን ለመገንባት የሚየገለግል ነው። በተጨማሪም ወደቡም "ከኢራን የሚመጡ የጦር መሳሪያዎች መተላለፊያ ነው" በሚል ዒላማ ሆኗል።
ጥቃት የተፈጸመበት ወደብ የመን ካሏት የባሕር በሮች መካከል ሁለተኛው ትልቁ ሲሆን፣ ወደ አገሪቱ ከሚገባው ምግብ 80 በመቶው በዚሁ ወደብ በኩል ነው።
የተለያዩ በወደብ ከተማዋ የሚኖሩ ምንጮች ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት ከ10 በላይ ጥቃቶች በሁዳይዳህ ወደብ እና በሌሎች የከተማዋ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ ስፍራዎች ተመትተዋል፤ ሌሎች አራት ጥቃቶች ደግሞ የሲሚንቶ ፋብሪካውን ዒላማ አድርገዋል።
በሁቲ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አኒስ አል-አስባሂ፣ ቢያንስ 21 ሰዎች በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ሁቲዎች ጥቃቱ የተፈጸመው በአሜሪካ እና በእስራኤል የጋራ ጥምረት ነው ሲሉ ከሰዋል። ነገር ግን አንድ አሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣን ለፈረንሳይ ኤና ወኪል ኤኤፍፒ ኃይሎቻቸው "እስራኤል [ሰኞ] በፈጸመችው የአየር ጥቃት አልተሳተፉም" በማለት አስተባብለዋል።
ባለፈው እሁድ ሁቲዎች ተኩሰው ከቴል አቪቭ አቅራቢያ ቤን ጎሪዮን አየር ማረፊያ ወደ ዋነኛው የመንገደኞች ማስተናገጃ በሚወስደው መግቢያ መንገድ ላይ ወድቆ ነበር። በፍንዳታው አራት ሰዎች መቁሰላቸውን እና ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ ወደ መደበቂያ ቦታ ሲያመሩ ቆስለዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጥቃቱን ተከትሎ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱ "ከዚህ በፊትም ጥቃት ፈጽመናል፣ ወደፊትም ጥቃት መፈጸማችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።
ሁቲዎች በእስራኤል አየር ማረፊያ ላይ የፈጸሙትን ጥቃት በተመለከተ ኢራን እጇ እንደሌለበት ቡድኑ "ጥቃቱን በራሷ ውሳኔ ያደረሰው ነው" ብላለች።
አሜሪካ በየመን ሁቲዎች ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃቶችን ስትፈጽም ቆይታለች።
የድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በሁቲ ኃይሎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ያዘዙ ሲሆን፣ ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣኑን ከተረከቡ በኋላም ጥቃቱ ቀጥሏል።
ባለፈው ሳምንት አሜሪካ በሰሜን ምዕራብ የመን ውስጥ በሚገኘው የስደተኞች ማቆያ ማዕከል ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማ ቢያንስ 68 ሰዎች መገደላቸውን ሁቲዎች አስታውቀው ነበር።












