ኬንያዊው ፖሊስ ለባለቤቱ ዋስትና የከለከሉትን ዳኛ ፍርድ ቤት ውስጥ ተኩሶ አቆሰለ

ፖሊሱ በፍርድ ቤት ውሳኔ ተበሳጭቶ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኬንያ መዲና ናይሮቢ አንድ የፖሊስ አዛዥ ለባለቤቱ የዋስትና መብት የከለከሉትን ዳኛ ችሎት መሃል ተኩሶ አቆሰለ።

ዳኛዋን ተኩሶ ያቆሰለው የኬንያ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን በስፍራው በነበሩ ሌሎች የፖሊስ አባላት በተከፈተበት ተኩስ ሕይወቱ ማለፉ ተገልጿል።

ዋና ኢንስፔክተሩ ጥቃቱን የፈጸመው የማካዳራ ዋና ዳኛ ሞኒካ ኪቩቲ ከባለቤቱ ጋር የተገናኘ ነው በተባለ ክስ ላይ ብይን ከሰጡ በኋላ ነው።

ባለቤቱ የዋስትና መብት በመከልከሏ ፖሊሱ መበሳጨቱ ተገልጿል።

ይህንን ተከትሎም በምዕራብ ኬንያ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ የሆነው ሳምሶን ኪፕቺርቺር ኪፕሩቶ ሽጉጡን አውጥቶ ዳኛዋን ተኩሶ አቁስሏል።

በፍርድ ቤቱ የነበሩ ሌሎች ፖሊሶች በፍጥነት ምላሽ በመስጠት ፖሊሱን ተኩሰው ገድለውታል።

በነበረው የተኩስ ልውውጥም ሦስት የፖሊስ መኮንኖች ቆስለዋል ሲል የአገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል።

ዳኛዋ እና የተጎዱት የፖሊስ መኮንኖች በሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።

ዳኛዋ “በተደጋጋሚ የፍርድ ቤት ውሳኔን ካለማክበሯም በላይ አጥጋቢ ማብራሪያ አልሰጠችም ላሏት ተከሳሽ ዋስትና ከልክለዋል” ብሏል የአገሪቱ ፍርድ ቤት።

“ይህ ውሳኔ በተነገረበት ቅጽበት አንድ ሰው በዳኛዋ ላይ ተኩሶ አቁስሏታል” ሲል በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

“ተኳሹ ከተጠርጣሪው ጋር ጋብቻ የፈጸመ የፖሊስ መኮንን መሆኑን” የሚያመለክቱ ሪፖርቶችን መመልከቱንም ፍርድ ቤቱ አስታውቋል።

የአገሪቱ ፖሊስ በበኩሉ የፖሊስ መኮንኑ በምን ምክንያት በችሎቱ ላይ ሊገኝ እንደቻለ “እንደማይታወቅ” ገልጿል።

ለዳኛዋእና ለሦስት ፖሊሶች መቁሰል ምክንያት የሆነውን ጥቃት ለማጣራት ምርመራው እንደቀጠለ መሆኑም ተጠቅሷል።

ይህ በፍርድ ቤት ውስጥ በዳኛ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ኬንያውያን አስደንግጧል።

የአገሪቱ ፖሊስ ያለፍርድ ቤት ግድያዎችን በመፈጸም በተደጋጋሚ ቢከሰስም፣ በፍርድ ቤት ውስጥ እንደዚህ ያለ ክስተት ግን አጋጥሞ አያውቅም።

የአገሪቱ የፍትህ ቢሮ የደኅንነት አጠባበቁን እንደሚያጠናክር ገልጾ፣ የፍትህ ሠራተኞች እና ሌሎች የፍርድ ቤት ተገልጋዮች ደኅንነት እንደሚጠበቅም አረጋግጧል።