የትዊተር የድርሻ ባለቤቶች ኤለን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር እንዲገዛ ፈቀዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትዊተር የድርሻ ባለቤቶች ኤለን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር እንዲገዛ መፍቀዳቸው ተገለጸ።
ሳን ፍራንሲስኮ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት የትዊተር ኢንቨስተሮች ባካሄዱት የስልክ ውይይት ነው ውሳኔው የተላለፈው።
በዚህ ውሳኔ መሠረት ኤለን መስክ ትዊተርን እንዲገዛው የድርሻ ባለቤቶቹ በፍርድ ቤት ለማስገደድ ይሞክራሉ ማለት ነው።
የቀድሞው የትዊተር የደኅንነት ኃላፊ በአሜሪካ ምክር ቤት አስደንጋጭ ምስክርነት ከሰጠ በኋላ ነው የትዊተር ውሳኔ የተሰማው።
ሚያዝያ ላይ ትዊተር ድርጅቱን ለዓለማችን ቁጥር አንድ ሀብታም ኤለን መስክ ለመሸጥ ተስማምቶ እንደነበር ይታወሳል።
ትዊተር እንደሚለው፣ በየቀኑ ገጹን ከሚጠቀሙና ማስታወቂያዎችንም ከሚመለከቱ ተጠቃሚዎች መካከል አምስት በመቶው በሰው ሳይሆን በማሽን እየተመሩ አንዳች አጀንዳን ለማራመድ የሚውሉ ገጾች ናቸው።
ኤለን መስክ በበኩሉ ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ያለ እንደሆነ ይከራከራል።
መጀመሪያ ላይ ትዊተርን ለመግዛት ኤለን መስክ ያቀረበው 44 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ አሁን ላይ የትዊተር የገበያ ዋጋ 32 ቢሊዮን ዶላር ነው።
የትዊተር የድርሻ ባለቤቶች ያሳለፉት ውሳኔ ድርጅቱ ኤለን መስክን ወደ ፍርድ ቤት እንዲወስድ የሚያስችል ይሆናል።
የፊታችን ጥቅምት በዳላዌር በሚገኝ ፍርድ ቤት ክርክሩ የሚጀምር ሲሆን፣ ኤለን መስክ ትዊተርን መግዛት አለበት ወይስ የለበትም የሚለውን ዳኛ ይወስናል።
የቀድሞው የትዊተር ሠራተኛና የአሁኑ መረጃ አጋላጭ ፒይተር ዛትኮ፣ በምክር ቤት ተገኝቶ ትዊተር የደኅንነት ክፍተቶች እንዳሉበት ምስክርነት ሰጥቷል።
ትዊተር ገጹ ምን ያህል ደኅንነቱ የተጠበቀ እንደሆነ “ሕዝቡን እያደናገረ ነው” ብሏል።
ደኅንነትን ለመጠበቅ የሚወሰዱ እርምጃዎችን በመተግበር ረገድ ትዊተር “ኋላ ቀር ነው” ሲልም ምስክርነቱን ሰጥቷል።
ትዊተር በበኩሉ የቀድሞው የደኅንነት ሠራተኛው ከሥራው እንደተሰናበተ ገልጾ፣ ስለ ተቋሙ የሰጠው ምስክርነትም የተዛባ እንደሆነ ገልጿል።
የቀድሞው የትዊተር ሠራተኛ፣ ትዊተር ላይ ያሉት ሐሰተኛ ገጾች (spam) ወይም በሰው ሳይሆን በማሽን እየተመሩ አንዳች አጀንዳን ለማራመድ የሚውሉ ገጾች (bot accounts) ኤለን መስክ እንዳለው ከፍተኛ ቁጥር እንዳላቸው ከዚህ ቀደም ተናግሯል።
የትዊተር የቀድሞ ሠራተኛ በምክር ቤት ተገኝቶ የሰጠውም ምስክርነት የኤለን መስክ ጠበቆች በፍርድ ቤት ሲከራከሩ እንደ ማስረጃነት መጠቀም እንደሚችሉ አንድ ዳኛ ወስነዋል።












