አነጋጋሪው ኤሎን መስክ ማነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ድሮ የቢል ጌትስ ዘመን ነበር፡፡
አሁን የኤሎን ዘመን ነው፡፡
ለኤሎን መስክ የምድር 'መስክ' ጠባዋለች፡፡ ወደ ሕዋ ያማትር ጀምሯል፡፡
ማማተር ብቻ ሳይሆን የሕዋ ታክሲ ፈጥሯል፡፡
አንድ ቀን የሰው ልጅ ወደ ሕዋ፣ ወደ ጠፈር፣ ወደ ሌሎች ፕላኔቶች ሄዶ እዚያ መኖር መጀመር እንዳለበት ያውጠነጥናል፡፡
መስክ ያሰበውን ሁሉ ሲያሳካ የኖረ የተግባር ሰው ነው፡፡
በጤናው ነው እንዳንል እሱ የሚያስበው ሁሉ ከአእምሮ በላይ ሆነ፡፡
ዝም ብለን ታሪኩን ብንቀጥል ነው የሚሻል፡፡

ሰሞኑን ሥራ በዝቶበታል፡፡ ግዙፉን ትዊተርን የግል ንብረቱ ሊያደርግ ውል በመፈጣጠም ላይ ነው፡፡
የትዊተር ግዢ ሂደቱ ራሱ አስደናቂ ነው፡፡
ከቀናት በፊት የትዊተርን 9 ከመቶ ድርሻ ገዛ ተባለ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ‹ይሄ ትዊተር ግን የሰውን ድምጽ ሳንሱር ያደርጋል› ሲል ተቸ፡፡
'ገዝቼ ልቀይረው እንዴ?' ሲል ቀለደ፡፡
ዓለም በቀልዱ ስቆ ሳይጨርስ በሳምንቱ 43 ቢሊዮን ዶላር አቀረበ፡፡
ሚዲያው ሁሉ ከሰሞኑ 'መስክ መስክ' የሚለው ለዚሁ ነው፡፡
እሱ ይህን ግዢ እስኪፈጣጠም እኛ ልጅነቱን በወፍ በረር አንቃኝም፡፡
በወፍ በረር ሳይሆን በስፔስ-ኤክስ፡፡ ከወፍ ይልቅ ስፔስ-ኤክስ ይፈጥናላ፡፡
ኤሎን አፍሪካዊ ነው?
በጀግና የማይሻማ የለም፡፡ ፑሽኪን የኛ ነው እንላለን፤ የመኒዎች ሳባ የኛ ናት ይላሉ፡፡
አፍሪቃዊያንም በኤሎን መስክ ለመኩራት ይዳዳቸዋል፡፡
መስክ የተወለደው በማዲባ አገር ስለሆነ ነው፡፡ እዚህች ወረድ ብሎ፤ ፕሪቶሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ ነው ውልደቱ፡፡
በነ ኦሊቨር ታምቦ አገር፣ በነ ዴዝሞን ቱቱ አገር፣ ከነ ኔልሰን ማንዴላ ምድር ነው የተገኘው፣ መስክ፡፡ ከነጭ ደቡብ አፍሪካዊ አባቱ እና ደቡብ አፍሪካዊ/ካናዳዊ እናቱ።
ልጅነቱ ምን ይመስል ነበር? ምንም፡፡ ያው የአንድ ነጭ ደቡብ አፍሪካዊ ልጅነትን ነው ያሳለፈው፡፡
እርግጥ ገና በ10 ዓመቱ ከኮምፒውተር ጋር የሙጥኝ ብሎ ነበር፡፡
በ12 ዓመቱ የሆነች ትንሽዬ የኮምፒውተር ጌም ፈጥሮ ነበር፡፡ ኋላ ላይ በ500 ዶላር ሸጣት፡፡
ከዚያ በፊት ደግሞ በየሰፈሩ ጀላቲ እንደሚሸጡ ልጆች እሱም ከወንድሞቹ ጋር ቤት ለቤት እያንኳካ ቼኮሌት ይሸጥ ነበር፡፡
ቢዝነስ የዘለቀው ያን ጊዜ መሆን አለበት፡፡
አባትና እናቱ ሃብታም ነበሩ?
እናቱ ነጭ ካናዳዊት ናት፡፡ ሞዴል፡፡ ሜይ ትባላለች፡፡
አባቱ ነጭ ደቡብ አፍሪካዊ። እሳት የላሰ ነጋዴ፡፡
ተራ ነጋዴ አይደለም ታዲያ፡፡ ምጡቅ አእምሮ የነበረው ነጋዴ እንጂ፡፡
በዚያ ላይ የኤሌክትሮመካኒካል መሐንዲስ፣ መርከበኛና ፓይለት ነበር፡፡ ስሙ ኤሮል መስክ ይባላል፡፡
መስክ እንደሚለው አባቱ ‹የእኩይ ባህሪያት ሁሉ ወደብ› ነው፡፡ በተለይ እናቱን ለብዙ ስቃይ ዳርጓታል፡፡
አባቱና እናቱ ሲለያዩ ታናሽ ወንድሙና እህቱ ወደ እናታቸው አዘነበሉ፡፡ እሱ የበኹር ልጅ እንደመሆኑ ለአባቱ አደላ፡፡
በኋላ ግን በውሳኔው ተጸጸተ፡፡ ‹አባቴን በክፋት የሚያህለው የለም፤ አእምሮው ምጡቅና የክፋት መሐንዲስ ነበር› ይላል፡፡ ከአባቱ ጋር ጥሩ ጊዜ አላሳለፈም፡፡
በ17 ዓመቱ ወደ እናቱ ሄደ፡፡ ወደ ካናዳ፡፡ አባቱ እንዲህ አለው፤ 'በሦስት ወርህ ተንከራተህ ተመልሰህ ትመጣለህ፡፡ ወይ ደግሞ እንደተንከራተትክ ትቀራለህ፡፡'
ኤሎን መስክ በካናዳ ኩዊንስ ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡
ከዚያ ደግሞ ወደ አሜሪካ ገባ፡፡ ከካናዳ በዝውውር ወደ ፔንስልቬኒያ ዩኒቨርስቲ ተሻገረ፡፡ በዚያም ሁለት ዲግሪ ሠራ፡፡ አንድ በፊዚክስ ሌላ ደግሞ በቢዝነስ፡፡
የሁለቱ ዲግሪዎች ጥምረት አሁንም ድረስ ኤሎን መስክን ይከተሉታል፡፡ በፊዚክስ ዕውቀቱ የፈጠራ ልህቀቱን ያሳየናል፣ በቢዝነስ ዲግሪው ይነግዳል፣ ይበለጽጋል፡፡
በትክክልም ኤሎን መስክ ዲግሪዎቹን የሚመስል ሰው ነው፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዕድሜው 24 ሲደርስ ደግሞ ወደ ካሊፎርኒያ መጣ፡፡
ሳት ብሎት በስታፈንድር ዩኒቨርስቲ ፒኤችዲ በአፕላይድ ፊዚክስ ለመማር ተዘገበ፡፡ ከዚያ ግን ምን እንደነካው አይታወቅም ወዲያኑ ጥሎ ወጣ፡፡ አልተመለሰም፡፡
ከዩኒቨርስቲ ጥለው የሚወጡ ሰዎች የሚሳካለቸው ግን ለምን ይሆን?
ኤሎን መስክ አግብቷል?
አዎ! ያውም በተደጋጋሚ፡፡
የመጀመርያ ሚስቱ ጀስቲን መስክ ደራሲ ናት፡፡ ኮሌጅ እያሉ ነው የተዋደዱት፡፡
‹መስክ በፍጹም እጅ የሚሰጥ ሰው አይደለም፡፡› ትላለች፡፡
‹ያሰበውን ሳያሳካ እንቅልፍ አይወስደውም፡፡ ፍጹም የበላይ መሆንን ይሻል› ካለች በኋላ በሰርጋቸው ዕለት እየደነሱ ሳለ ወደ ጆሮዋ ጠጋ ብሎ የተናገራትን መቼም አትረሳውም፡፡
‹‹በዚህ ትዳር ውስጥ የበላይ አዛዡ እኔ ነኝ፡፡››
ኤለን መስክ ቢሊዮን ዶላር ከየት አመጣ?
ኤሎን መስክ እርግጥ አባቱ እንደ ማንኛውም ነጭ ደቡብ አፍሪካዊ የናጠጠ ሃብታም ነው፡፡ ከማዕድን እስከ ሪልስቴት ያልገባበት የንግድ ዘርፍ የለም፡፡
የኤሎን መስክ ሃብት ግን ከዚያ የሚመዘዝ ስለመሆኑ ተጨባጭ መረጃ አልተገኘም፡፡
ይልቅ ከስታንፈርድ ዩኒቨርስቲ ፒኤች ዲ ጥሎ እንደወጣ ሁለት ነገር ሞከረ፡፡
አንዱ የድረ-ገጽ መተግበሪያ የሚሰራ ትንሽ ኩባንያ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የበይነ መረብ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ኩባንያ ነበር፡፡
ከዚያ በፊት ግን ከወንድሙ ጋር ዚፕ2 የሚባል ሶፍትዌር ሠርተው ነበር፡፡ ጽሑፍን ከጋዜጣ ወደ ዲጂታል የሚቀይር ነው፡፡
ከብዙ መከራ በኋላ ድርጅቱን ሸጡት፡፡
ከዚያ በኋላ ነው ሁለት ሌሎች ድርጅቶችን የሞከረው፡፡
ከሁለቱ አንዱ ፍሬ አፈራ፡፡ ይሄም የበይነ መረብ የባንክ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ በኋላ ፔይፓል (PayPal) በሚል የምናውቀው ክፍያን የሚያቀላጥፈው ኩባንያ፡፡
ብዙ ሰው ፔይፓልን ከፈጠሩት መካከል አንዱ ኤለን መስክ እንደሆነ አያውቅም፡፡
እንዲያውም ጠቀም ያለ ዶላር ያመጣለት ይህ ኩባንያ ነው፡፡ የኋላ ኋላ ለኢቤይ ኩባንያ ሸጠው፡፡ 1.5 ቢሊዮን ዶላር አስገኘለት፡፡
ይሄን ገንዘብ ይዞ ሌላ ነገር ማሰብ ጀመረ፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከምድር ወደ ሕዋ አማተረ፡፡ ናሳ ወደ ሕዋ በሚያደርገው ጉዞ ብዙ ወጪ እንደሚያወጣ ተገነዘበ፡፡ አንዴ የበረረች መንኮራኮር ዳግም አግልግሎት እንደማትሰጥ ተረዳ፡፡
ይህ የስፔስኤክስ ሐሳብን ወለደ፡፡ ወደ ሕዋ የምታደርስ፣ አድርሳ የምትመልስ ዘላቂ ታክሲ ሠራ፡፡
ወጪና ነዳጅ ቆጣቢ መኪናዎችም በምድር ላይ መፈጠር አለባቸው ብሎ ተነሳ፡፡ ቴስላን ፈጠረ፡፡
"ለራሱ የተጋነነ አመለካከት ያለው ቢሊየነር"
በ2015 አሽሊ ቫንስ የተባለ ሰው መጽሐፍ ጻፈ፡፡ መጽሐፉ ኤለን መስክ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
ከብዙ ጥናት በኋላ ይህ ደራሲ ኤለን መስክን ሲገለጸው በሦስት ሐረግ ነው፡፡
"ተጋፋጭ፣ ሁሉን አውቃለሁ ባይ፣ እንዲሁም ስለራሱ የተጋነነ አመለካከት ያለው፡፡"
ኤለን መስክ ቅጣምባሩ የጠፋበት ዳንስ እንደሚደንስ ይኸው ደራሲ ጠቆም አድርጎን ያልፋል፡፡
እኛ ከዳንሱ ምናገባን፡፡ ወደ ባህሪው እንመለስ፡፡
ኤለን መስክ ይህ ተጋፋጭነት ባህሪው፤ ሁሉን አውቃለሁ-ለኔ ተዉት ባይነቱ፣ በተለይም ስለ ራሱ የተጋነነ አመለካከት መያዙ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው፡፡
አንዳንድ የሕይወቱ ሰበዞችም ይህን ይመሰክራል፡፡
ለምሳሌ ሦስት ጊዜ አግብቶ ፈቷል፡፡ ከአንደኛዋ ጋር ሁለት ጊዜ፡፡
መስክ ሲናገር ለነገ አይልም፡፡ በትዊተር ሰሌዳው ድንገቴ የሆኑ ሐሳቦችን እየጻፈ ዓለምን ያንጫጫል፡፡
ለማሪዋና ዕጽ ያለውን ፍቅር ደብቆ አያውቅም፡፡
በቅርብ ጊዜ በቴድቶክ ባደረገው አነቃቂ ንግግር ይህን ወጣ ያለ ባህሪውን እሱም አምኖ ተቀብሏል፡፡
‹‹ሐጢአቶቼን መቁጠር ከጀመራችሁ በምድር ላይ እንደኔ መጥፎ ሰው የለም፡፡ ነገር ግን በጎ ተግባሬን መቁጠር ስትጀምሩ ሐጢአቶቼን የሚያስተሰርዩ ኾነው ታገኟቸኋላችሁ፡፡›› ብሎ ነበር፡፡
ኤሎን መስክ ሃብቱ ስንት ደረሰ?
ፎርብስና ብሉምበርግ እንጀራ ሆኖባቸው ከቢሊየኖች ሥር ከሥር እየሄዱ የሰው አዱኛ ይቆጥራሉ፡፡
በቅርብ ጊዜ ነው ኤሎን መስክ የዓለም ሃብታሙ ሰው ነው ብለው ያወጁለት፡፡
አንጡራ ሃብቱ፣ የሚዳሰስም የማይዳሰስም ተጨምሮ፣ 250 ቢሊዮን ዶላር ደርሶለታል፡፡
ለዓመታት ቁጥር አንድ የነበረውን የአማዞኑን ጄፍ ቤዞስ በብዙ ቢሊዮኖች ነው ጥሎት የበረረው፡፡
የኤሎን መስክ ሃብት ታዲያ በአብዛኛው በቴስላ የአክሲዮን ድርሻ ባልተጠበቀና የጤና በማይመስል ሁኔታ መመንደጉን ተከትሎ የመጣ ነው፡፡
እሱ የቴስላ ኩባንያን 17 ከመቶ ድርሻ ይዟል፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእብድ የሚመስሉት ሐሳቦቹ
ብዙ ሰው ኤሎን መስክ ሲያስብ፣ ቴስላና ስፔስ ኤክስ ናቸው ወደ አእምሮው የሚመጡበት፡፡
ሰውየው ግን ብዙ የዕብድ የሚመስሉ ሐሳቦችን ጀማምሯል፡፡
ከነዚህ መሀል አንዱ ሶላር ሲቲ ነው፡፡ ሁሉንም የኃይል ፍላጎታችንን ከፀሐይ ብርሃን ማግኘት አለብን ብሎ ተነስቷል፡፡
ግድብ፣ ኒክሊየር፣ ጋዝ አያስፈልጉም፡፡ በቃ አንድን ከተማ ሙሉ በሙሉ ከፀሐይ ብርሃን ኃይል እንዲያገኝ አድርገን መገንባት እንችላለን ብሎ ያምናል፡፡
ከፍሪጅ እስከ ምድጃ፣ ከሻወር ማሞቅያ እስከ ከፍተኛ ፋብሪካ ድረስ ኃይልን ከፀሐይ እንዲያገኝ አድርገን መፍጠር እንችላለን ይላል፡፡
አያደርገውም አይባልም፡፡
ሌሎች ኩባንያዎችም አሉት፡፡ የሚቃዥባቸው፡፡ በዲጂታል ግብይት ውስጥ ቀስበቀስ እጁን እያስገባ ነው፡፡ ኮምፒውተሮች የሰው ልጅን ሊበልጡት እንደሚቸሉ ይገምታል፡፡
አንድ ‹‹ቦሪንግ›› የሚባል ኩባንያ ደግሞ አለው፡፡ የዚህ ኩባንያ ሥራው ዋሻ መቆፈር ነው፡፡
ኤሎን መስክ ከሚያበሳጩት ነገሮች አንዱ የትራፊክ መጨናነቅ ነው፡፡
የሰው ልጅ ወይ በአየር እንደ አእዋፍ መብረር አለበት፤ ወይ ደግሞ በዋሻ ውስጥ እንደ ወራጅ ዉሃ መፍሰስ አለበት ብሎ ያምናል፡፡
ይህ ‹‹ቦሪንግ›› የተሰኘው ኩባንያውም ይህን ለማሳካት የተመሠረተ ነው፡፡
ሉፕ በሚባል የማግኔቲክ ቴክኖሎጂ ሰዎች ልክ እንደ ፍሳሽ ውሃ ከመሬት በታች ምንም የትራፊክ መብራት ሳያቆማቸው መጓጓዝ አለባቸው ይላል፡፡
ምክንያቱም በከተሞች ሕዝብ እየጨመረ ነው፡፡
በአስፋልት መጓጓዝ አንጀት ነው፡፡ ልብ አውልቅ ነው፡፡ ልብ አውልቅ ብቻ ሳይሆን ኋላ ቀርነት ነው፡፡ ማንኛውም መጓጓዥ ወደ ዋሻ መግባት አለበት ይላል፡፡
ይህንን ሐሳቡን በላስቬጋስ እየሞከረው ነው፡፡
በሰዓት 600 ማይል የሚፈጥኑ ናቸው የዋሻ ውስጥ ታክሲዎቹ፡፡ ይህ ወደ 900 ኪሎ ሜትር በሰዓት መክነፍ ማለት ነው፡፡
ምሳ አዲስ አበባ በልቶ ማክያቶ አስመራ ለመጠጣት መሄድ ማለት ነው፡፡
ኤለን መስክ በፖለቲካው የማን ደጋፊ ነው?
ይህ ጥያቄ መነሳት የጀመረው ትዊተርን ለመግዛት ፍላጎት ያሳየበትን ምክንያት ከተናገረ በኋላ ነው፡፡
ድምጾች ምንም ይሁን ምን መታፈን የለባቸውም የሚል እምነት አለው፡፡
በዩክሬን አሁን ኢንተርኔትን በሳተላይት እያቀረበ ያለው እሱ ነው፡፡
ዳያስፖራ ኤርትራዊያንም ተመሳሳይ ነገር በኤርትራ እንዲጀምር ተማጽነውት ነበር፡፡
ኤለን መስክ የአሜሪካ ዜጋ የሆነው በ2002 ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ግማሽ ዲሞክራት፣ ግማሽ ሪፐብሊካን እያሉ ይጠሩታል፡፡
እሱ ግን እኔ ነጻና ገለልተኛ ነኝ ይላል፡፡ ከመንግሥት ጋር በመላተም ይታወቃል፡፡
ከካሊፎርኒያ ወደ ቴክሳስ ድርጅቱን የወሰደው የካሊፎርኒያ ግብርን በመቃወም ነበር፡፡ ከሰራተኛ ማኅበራቱም ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡
የኮሮናቫይረስ የእንቅስቃሴ ገደብ ደግሞ አበሳጭቶት ነበር፡፡ ገደቡን ፋሺስታዊ ሲል እስከመጥራት ደርሶ ነበር፡፡
ኤሎን መስክ ዶናልድ ትራምፕ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት ለመውጣት ሲወስኑ ቁጣውን ያሰማ የመጀመርያው ባለሀብት ነው፡፡ ክፉኛ ተችቷቸዋል፡፡
ይሁንና ጆ ባይደንም አይስማሙትም፡፡
ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚለግሰው ገንዘብ ከሱ ሃብት ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም ለኦባማና ለሂላሪ ለግሷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለሪፐብሊካኑ እየሰጠ ነው፡፡
በበጎ አድራጎት ረገድ እምብዛምም ስሙ አይነሳም፡፡ እሱ ግን የኔ ቢዝነሶች እኮ በራሳቸው በጎ አድራጎት ናቸው ሲል ይከራከራል፡፡
ይህን የሚለው ብዙዎቹ ፈጠራዎቹ ታዳሽ ኃይልን መሠረት ያደረጉና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቀንሱ በመሆናቸው ነው፡፡
ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራም ለቢሊየነሮች ጥሪ አድርጎ ነበር፡፡
የዓለም ቢሊየነሮች ሆይ! አንድ ጊዜ ከፍተኛ እርዳታ ስጡና በ43 አገሮች የተራቡ 40 ሚሊዮን ረሃብተኞች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታደጉ የሚል፡፡
ኤለን መስክን ለምላሽ የቀደመው የለም፡፡ በገንዘብ ሳይሆን በቃላት፡፡
እንዲህ አለ፡-
‹‹እንደምትሉት ረሃብን ከዓለም ለማጥፋት 6 ቢሊዮን ዶላር በቂ ነው የምትሉ ከሆነ እቅዳችሁን ይዛችሁ ኑ፣ አሳምኑኝ፤ እኔ የቴስላን አክሲዮን ሽጬም ቢኾን 6 ቢሊዮን ዶላር ልስጣችሁ፡፡››
የዓለም ረሃብና መከራ ብሶበት ቀጥሏል፡፡ የኤለን መስክ አዱኛም ይመነደግ ይዟል፡፡












