በሞቃዲሹ በማረፍ ላይ የነበረ አውሮፕላን ባልተለመደ ሁኔታ ተከሰከሰ

የፎቶው ባለመብት, ALI HASSAN ALI
በሶማሊያ ዋና መዲና ሞቃዲሾ ውስጥ በሚገኘው አደን አዴ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ለማረፍ የሞከረ አንድ አውሮፕላን ባለተለመደ ሁኔታ ወድቆ ተከሰከሰ።
ሰኞ ፣ሐምሌ 11/2014 ዓ.ም ጠዋት በአገር ውስጥ በረራ ላይ የነበረው አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ በኋላ ከዚህ በፊት ብዙም ባልታየ ሁኔታ ወደ ላይ ተገልብጦ ታይቷል።
ይሁን እንጂ በዚህ የአውሮፕላን አደጋ ወቅት በውስጡ በነበሩት ከ30 በላይ ሰዎች ላይ የሞት አደጋ እንዳልደረሰ ከሥፍራው የወጣ ዘገባ ያሳያል።
አደጋውን ተከትሎ ከሞቃዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ የተነሱት ምስሎች፣ አውሮፕላኑ ከተከሰከሰበት ቦታ ላይ ጥቁር ጭስ ሲወጣ አሳይተዋል።
ከሥፍራው የወጡ ምስሎች የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳቱን ለማጥፋት ሲረባረቡ ያሳዩ ሲሆን፣ በዚህም ፎከር 50 የተባለው አውሮፕላን ደረቱን ለሰማይ ሰጥቶ በጀርባው ተገልብጦ ታይቷል።
ባለቤትነቱ የጁባ አየር መንገድ የሆነው አውሮፕላኑ በአገር ውስጥ በረራ ላይ የነበረ ሲሆን፣ ከባይዶዋ ከተማ ተነስቶ ወደ ዋና መዲናዋ ሞቃዲሾ እየበረረ ሳለ አደጋው እንዳጋጠመው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
መንገደኞችና እና የበረራ ቡድን አባላትን ከአደጋው መታደግ እንደተቻለም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የአየር መንገዱን ባለሥልጣናት ጠቅሰው ዘግበዋል።
የአደጋው ምክንያት ምን እንደሆነ ግን እስካሁን አልተገለጸም።
አደጋውን ተከትሎ ለተወሰኑ ሰዓታት የአውሮፕላን ማረፊያ ተዘግቶ የነበረ ሲሆን በዚህም መድረሻቸውን ሞቃዲሾ አየር ማረፊያ አድርገው የነበሩ አውሮፕላኖች ወደ ሌሎች አየር ማረፊያዎች እንዲዞሩ ተደርጓል።
የአየር ማረፊያ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት የወደቀውን አውሮፕላን ለማንሳትና መንደርደሪያዎቹን ምቹ ለማድረግ ለጥቂት ሰዓታት ተዘግቶ የነበረው የአውሮፕላን ማረፊያ ተከፍቷል።
ከዚህ በፊት በዚሁ አየር ማረፊያ በአንድ የጭነት አውሮፕላን ላይ የተለያዩ አይነት አደጋዎች ማጋጠማቸው ይታወሳል።
በእርስ በርስ ጦርነት ስትናጥ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በቆየችው ሶማሊያ ውስጥ በአየር ትራንስፖርት አማካይነት የተለያዩ አደጋዎች አጋጥመዋል።
በአገሪቱ ባለው የሽብር ስጋት የተነሳ ታዋቂ አየር መንገዶች ወደ ሶማሊያ የማይጓዙ ሲሆን፣ አስፈላጊ በረራዎች በቻርተርድ አውሮፕላኖች ይደረጋሉ።
በሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው እስላማዊው ታጣቂ ቡድን አልሻባብም አየር ማረፊያውን ኢላማ በማድረግ ጥቃት ለመፈጸም ሙከራ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, ALI HASSAN ALI












